የባንክ ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ ኹለት ግለሰቦች በፀጥታ ኀይሎች ተገደሉ

0
1021

ከኹለት ሳምንታት በፊት ሰኞ፣ ሰኔ 17 ጠዋት 2 ሰዓት አካባቢ በተለምዶ ብስራተ ገብረኤል ተብሎ በሚጠራው አካበቢ አንድ የንግድ ባንክ የቢዝነስ ሥራ አስኪያጅ እና ሞተረኛ ጓደኛቸው እስከአሁን ባልታወቀ ምክንያት መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካትሪን ሃምሊን ቅርጫፍ የቢዝነስ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሟች ኢሳያስ ታደሰ ላይ ግድያው የተፈጸመው ተከራይተው ከሚኖሩበት ቤት ወደ መሥሪያ ቤታቸው የቅርብ ጓደኛቸው ከሆኑት ሞተረኛ ጋር በመሆን በመሔድ ላይ በነበሩበት ወቅት መሆኑን የሟች ጓደኞች ተናግረዋል።

የ33 ዓመቱ ኢሳያስ ተወልደው ያደጉት በተለምዶ ሰባ ደረጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን የወጣቶች እድር ሰብሳቢ እና በተለያዩ የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ ስለሚያደርጉ ተወዳጅ እንደነበሩ አብሮ አደጋቸው ሮቤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከወራት በፊትም በሕመም ምክንያት ሕይወታቸው ያለፉ የሰፈሩን ኹለት ልጆች አስመልክቶ ከውጪ አገር እንዲሁም ከአገር ውስጥ 50 ሺሕ ብር ገደማ ያሰባሰቡት ኢሳያስ ለሟች ወላጆች ገንዘቡን ማስረከባቸውንም ሮቤል በሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው አስታውሰዋል። በተጨማሪም ለሟች ወንድማማቾች ታናሽ እህትም በሚሠሩበት ቅርንጫፍ የባንክ ደብተር በመክፈት 10 ሺሕ ብር እንዲቀመጥ ማድረጋቸውንም ጨምረው አስታውሰዋል።

የኢሳያስ ሥራ ባልደረቦችም ጓደኛቸው የሚቀመጥበትን የመሐል ወንበር በመጠቆም ከካፒታል ሆቴል ፊት ለፊት ከአንድ ወር በፊት በተከፈተው ቅርጫፍ ውስጥ ባላቸው ተግባቢነት እና ተጫዋችነት ተወዳጅ እንደነበሩም ይናገራሉ። ሟች እጅግ ተግባቢ ነበሩ ያሉት ባልደረቦቻቸው ሕልፈታቸው እንዳሳዘናቸውና ምናልባትም እንደቢዝነስ ሥራ አስኪያጅነታቸው መግባት ከነበረባቸው ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል በማርፈዳቸው ምክንያት ችኮላ ላይ ሆነው ይሆን በሚል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የሟች እህት ለአዲስ ማለዳ እንዳሳወቁትም ሽንጣቸው አካበቢ በአንድ ጥይት መመታታቸውንና ወላጅ አባታቸውም በሆስፒታል ተገኝተው ያረጋገጡ ሲሆን የሞተረኛ ጓደኛቸው አስከሬን ያለመመልከታቸውን የሚናገሩት የሟች እህት እሳቸውም በጥይት መመታታቸውን መስማታቸውን ግን ተናግረዋል፡፡

ከሐዘኑ በኋላም ጉዳቱን ያደረሰው የፀጥታ አካል በቁጥጥር ሥር ውሎ ይገኝበታል ወደ ተባለው የንፋስ ሥልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መሔዳቸውን የሚናገሩት ገነት ጉዳዩ ወደ ማዕከለዊ ተመርቷል ተብለው መሔዳቸውንም ተናግረዋል። “በማዕከላዊም በኢሳያስ ሥም ምንም ፋይል እንዳልተከፈተ ተነግሮን መልሰን ወደ ላፍቶ ብንመራም ምንም ባለማግኘታችን በማዕከላዊ ፋይል ክፍቱ ስላሉ ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 አዲስ የክስ ፋይል ከፍተን መልስ እየተጠባበቅን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የሟች ኢሳያስ ቤተሰቦችም ሆኑ ጓደኞች እንደሚሉት ጉዳቱን ያደረሱት የፀጥታ አካለት መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም የአዲስ አበባ ፖሊስ ይሁኑ አይሁኑ እንደማያውቁ ነገር ግን ከፀጥታ ሃይሎች መኪና ላይ በተተኮሰ ጥይት የኹለቱም ወጣቶች ሕይወት ሊያልፍ መቻሉን ከዓይን እማኞች መስማታቸውን ይናገራሉ።

በወቅቱ በቦታው ላይ የነበረ አንድ ትራፊክ ፖሊስም ከቅርብ ርቀት ሲመቱ እንዳየ ለወዳጆቹ ሲያጫውት መስማታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፕሬስ ሴክሪታሪያት ጽህፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት በረከት ስለጉዳዩ መስማታቸውን እና ባደረጉት ማጣራትም የከተማ አስተዳደሩ ፖሊሶች ድርጊቱን አለመፈፀማቸውን አረጋግጠው ማን ነው የሚለውን እንደማያውቁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኢሳያስ የቀብር ሥነ ስርዓት ሕይወታቸው ባለፈ ማግስት ሰኔ 18 2011 ከቀኑ ስምንት ሰዓት በየካ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል። በተመሳሳይም የሟች ጓደኛቸው የቀብር ሥነ ስርዓት በቀጨኔ መድኀኒ ዓለም የተካሔደ ሲሆን ከቅዳሴ በኋላ 9 ሰዓት ላይ መከናወኑን ሮቤል ተናግረዋል።

“በአብዛኛው ሰው አብረው እንዲቀበሩ ፍላጎት ቢኖረውም የአካበቢው ወጣቶች ለቀብር የመጣውን ሰው ቁጥር በመመልከት ከ10 ሺሕ በመብለጡ እና በወጣቱ ውስጥ የነበረው ቁጭት እና እልህ ወደ ሌላ ነገር እንዳይለወጥ በሚል ቀብራቸው ተለያይቷል” ሲል እዮብ ተናግሯል። ኹለቱም ወጣቶች በነበራቸው መልካም የማኅበራዊ ግንኙነት ምክንያት ቁጥሩ ቀላል የማይባል ወዳጅ እንደነበራቸውም አክለው ገልፀዋል።

በሞተር ሥራ የሚተዳደሩት እና በወቅቱ ኢሳያስ ቤት አድረው በጠዋት ወደሚሠሩበት ቦታ ለመሸኘት ሲጓዙ የነበሩት ወጣት ቤተሰቦች አዲስ ማለዳ ለጊዜው አግኝታ ማነጋገር ባትችልም ለእናታቸው ብቸኛ ልጅ እንደነበሩ እና እናታቸውም ሌላ ዘመድ እንደሌላቸው ጋዜጣችን ያነጋገረቻቸው በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ የአካበቢው ሰዎች ተናግረዋል።

ጋዜጣችን የፍትሕና የፀጥታ ግብረ ኀይል በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመጠየቅ ባደረገችው ጥረት ለግዜው መልስ መስጠት የሚችለው አካል ማን እንደሆነ ያለመለየቱ ተገልፆ ማብራሪያ ለማግኘት ሳትችል ቀርታለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here