አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምሥራቅ 525 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ሐረርን በሥራ ጉዳይ ጎራ ባለችበት ወቅት አጠቃላይ ቅኝት በማድረግ ስለክልሉ ከዚህ በፊት ይሰሙ የነበሩት ጉዳዮች በቅርበት ለመታዘብ ዕድሉን አግኝታለች። በዚህ የጋዜጣችን ዕትም ላይ ሐረርን ማዕከል ያደረጉ ዘገባ፣ ትንታኔና ከአንድ የክልሉ ቢሮ ኀላፊ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ በማካተት ተደራሲዎቻችን ስለክልሉ አጠቃላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የበኩሏን ጥረት አድርጋለች። በተለይ የፌደራል መንግሥቱም ልዩ ትኩረት አድርጎ ከክልሉ መንግሥት ጋር በጋራ መሥራት እንዲችል የዚህ ዕትም ርዕሰ አንቀጽ ከዚህ በፊት በነበሩ ዕትሞቻችን በተለየ ሁኔታ በአንድ ክልል ላይ ትኩረት አድርጓል። ይህም የሆነበት ምክንያት ክልሉ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ከመመኘት ጭምር መሆኑን ውድ አንባቢያን እንዲረዱልን እንፈልጋለን።
መጋቢት 2010 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው የለውጥ ኀይል የፌደራል መንግሥቱን መንበር ከያዘ በኋላ በተለያዩ ክልሎች ከለውጡ ጋር በተያያዘ ከሰላምና ደኅንነት እንዲሁም፣ የሕግ ልዕልናን ከማስጠበቅ አንጻር ከባድ ተግዳሮቶች ገጥመው እንደነበር ይታወሳል። አገሪቷ ውስጥ ከተካሔደው ለውጥ ጋር በተያያዘ በዋነኛነት ግጭቶች ጎልተው ከተከሰቱባቸው መካከል ሐረር በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ እንደሆነች ከማንም የተሰወረ አይደለም።
በሐረሪ ክልል በተለይ በሐረር ከተማ የጎበዝ አለቆች የተበራከቱበትና ስርዓት አልበኝነት በሰፊው የሰፈነበት ለመሆኑ የመገናኛ ብዙኀን ሰፊ ዘገባ ይታወሳል፤ አሁንም ቢሆን ክልሉ ሙሉ ለሙሉ ከዚህ ሥጋት ነፃ ነው ማለት አይቻልም። አዲስ ማለዳ ተዟዙራ እንደታዘበችውና ከክልሉ አመራሮች ባገኘችው መረጃ መሰረት ክልሉ ከፍተኛ ስርዓት አልበኝነት አስተናግዷል።
ለአብነትም በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 650 ሔክታር መሬት ተዘርፏል። መምህራንና ሌሎች የኅበረተሰብ ክፍሎች ይኖሩበት ከነበረው ቤታቸው በኀይል ተፈናቅለዋል፤ በእርሻ ቦታ ላይ የደረሱ ሰብሎችና ፍራፍሬዎች ማሳ ላይ እንዳሉ ዘረፋ ተካሒዶባቸዋል። በጎበዝ አለቆች የሐረር ከተማ የውሃ አቅርቦት እንዲስተጓጎል ተደርጎ ኅብረተሰቡ ለስቃይ ተዳርጓል፤ ቤተ እምነቶች በተለይም ቤተክርስቲያናትና መስጊዶችም የጥቃትና ዘረፋው ዒላማ ተደርገው ብዙ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከላይ በጥቂቱ ለማንሳት በተሞከሩትና ሌሎች መሰል ሕገወጥ ድርጊቶች፣ የክልሉ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ መላሸቅ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውስ ለማስተናገድ ተገዷል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎችም የሚታየው የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ማሻቀብ የሐረርም ራስ ምታት ነው። የክልሉ ገጽታ ይህ በሆነበት ሁኔታ፣ የክልሉ መንግሥት ስርዓት ማስጠበቅና በአግባቡ ሕዝቡን ማስተዳደር ባለመቻሉ እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱም ቢሆን በአጠቃላይ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሕግ የበላይነትን ማስከበር አለመቻሉና በስርዓት አልበኞች ላይ እየወሰደ ያለው የመለሳለስ እርምጃ ሐረርን ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል።
በተለይ ደግሞ ሐረር ከተማ ከኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከል ትመደባለች። ክልሉ ገቢ ከሚያገኝባቸውና ምጣኔ ሀብቱን ከሚያግዙት መካከል ይኸው የቱሪዝም ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ስርዓት አልበኝነት ከቱሪስቶች (ከጎብኚዎች) ፍሰት ጋር ደግሞ ዓይንና ናጫ ናቸው፤ ሰላምና ደኅንነት ከቱሪስት ፍሰት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ በመሆናቸው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሰላምና መረጋጋት የራቃት ሐረር የዛሬን አይድርገውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም፣ በመቻቻል፣ በመፈቃቀር እና በልማት ከተማነት ዓለም ዐቀፍ ሽልማት እና ዕውቅናን አግኝታለች። ይህም የተለያየ እምነት፣ ባሕል እና ቋንቋ ያላቸው ሕዝቦች ለዘመናት በሰላም እና በፍቅር የኖሩባት ከተማ በመሆኗ የተቀዳጀችው ክብር እና ዕውቅና ነው። አሁን ግን በምድር ላይ ያለው እውነት ይሔ አይደለም፤ በብዙ ርቀት ወደ ኋላ ተጉዛለች።
የታሪክ መዛግብት ከትበው እንዳስቀመጡት ሐረር ከፍተኛ የሥልጣኔ ዕድገት ደረጃ ላይ በደረሰችበት በ16ኛው ክፍለ ዘመን በምሥራቅ አፍሪካ የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት እና የንግድ ማዕከል ሆናም አገልግላለች። ይህም የበርካታ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ቅርሶች ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል።
ከእነዚህም መካከል የጀጎል ግንብ የሐረሪ ሕዝብ የኪነ ሕንፃ ችሎታውን የሚያስመሰክር የታሪክ እና የጥበብ መዘክር ነው። ይህ ግንብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በአሚር ኑር አማካኝነት መገንባቱ በታሪክ ተመዝግቧል። በውስጡም 82 መስጊዶች እና 102 የመቃብር ቦታዎች አሉዋት። የጀጎል ግንብ ሃይማኖታዊ መሰረቱን ሳይለቅ የኢትዮጵያ ኢስላማዊ ኪነ ሕንጻና ባሕል ማሳያ ኅያው ምስክር መሆኑም ይታመናል። በተለይ በእስልምና ሃይማኖት ሐረር “4ኛዋ የተቀደሰች ቦታ” በመባልም ትታወቃለች። የጀጎል ግንብ ከ1998 ጀምሮ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ እንደሚገኝም ይታወቃል።
ይህን የመሰለ የአገር ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ቅርስ አደጋ ላይ መውደቁን ምናልባት ከዓለም ቅርስነት መዝገብ ሊሰረዝ የሚችልበት ዕድል መኖሩን አዲስ ማለዳ በአካል ተዘዋውራ ለመታዘብ ችላለች። በዋናነት ቅርሱን አደጋ ላይ የጣሉት ደግሞ ሕገወጥ የቤት ግንባታዎች ናቸው።
በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመተባበርና በመቀናጀት በፍጥነት የጀጎል ግንብን መታደግ ይገባቸዋል ስትል አዲስ ማለዳ ጥሪዋን ታስተላልፋለች። በተለይ የቅርስ ጥናትና ምርምር ባለሥልጣን ቅርሶች በታሪክ ምስክርነታቸው ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ፣ ሳይንሳዊ ምዝገባና ቁጥጥር ማከናወን፣ ቅርሶችን ከሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች መከላከል፣ ከቅርሶቹ የሚገኙ ጥቅሞች ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማቶች እገዛ እንዲያደርጉ ማስቻል፣ ቅርሶች ማግኘትና ማጥናት የሚሉ ዐበይት ዓላማዎችን እንዲይዝ ተደርጎ የተቋቋመው ተቋም ኀላፊነት ድርብ መሆኑን አዲስ ማለዳ አበክራ ትገልፃለች።
በአጠቃላይ በሐረሪ ክልል ለተንሰራፋው ስርዓት አልበኝነትም ሆነ የጀጎል ግንብ ከዓለም ቅርስነት መዝገብ ለመሰረዝ መቃረብን በተመለከተ የክልሉ መንግሥት በራሱ እንዲሁም ከፌደራል መንግሥት ጋር በቅንጅት በልዩ ትኩረት መሥራት አለበት በማለት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011


