የሰብኣዊ መብት ኮሚሽነር የትርፍ ጊዜ ሥራ እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸው ተቃውሞ አስነሳ

0
328

ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 ሹመታቸው የጸደቀው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የኮሚሽኑን አዋጅ መሰረት አድርገው ከዋና ኀላፊነታቸው ጎን ለጎን ተጨማሪ የትርፍ ጊዜ ሥራዎችን እንዲሠሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸው በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ተቃውሞ ቀረበበት።

የኮሚሽነሩ ሹመት በአብላጫ ደምፅ በጸደቀበት ዕለት አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት የትርፍ ጊዜ ሥራን መሥራት በተመለከከተ የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ ሥራው ሙሉ ጊዜንና አቅምን የሚጠይቅ በመሆኑ ጥያቄው ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተቃውመዋል። ታደሰ መሰሉ የተባሉት የምክር ቤቱ አባል “ከዚህ ቀድም ሥራው ላይ ቆይተው የነበረ ከሆነ ይነገረን” በማለት “ይህ ካልሆነ ግን የሥራ አፈፃፀማቸውን እያየን ቢፈቀድላቸው ይሻላል” የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።

በሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ኮሚሽነሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጥያቄ በማቅረብ የትርፍ ጊዜ ሥራዎችን መሥራት እንደሚችል የሚደነግግ ሲሆን የተወሰኑ አባላትም አንቀጹን በመጥቀስ እኛ ጋር ሳይደርስ በቢሮ በኩል ከአፈ ጉባኤው ጋር በመሆን መጨረስ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜናም የኮሚሽነሩ ሹመት ጋር ከተለያዩ የምክር ቤቱ አባለት አስተዳደራዊ ልምድ የላቸውም የሚል ቅሬታ የቀረበባቸው ሲሆን ተሿሚው ለሰብኣዊ መብት በመሟገት እና በአማካሪነት እንጂ አስተዳደራዊ ልምድ እንደሌላቸው እየታወቀ ለዋና ኮሚሽነርነት መታጨታቸው በምን መርህ እንደሆነ ይብራራልን ሲሉም ጥያቄያ አንስተዋል።

በእጩነት የቀረቡትን የዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሥራ ልምድ በመጥቀስ የተቃውሞ ሐሳብ በሰነዘሩት የምክር ቤት አባላት ላይ ሰብኣዊ መብት እጩ ኮሚሽነር አቅራቢ ኮሚቴ ጸሀፊ ተመስገን ባይሳ (ዶ/ር) እጩዎችን የመለየትና የማጣራት ሥራ የተሠራበትን መንገድ በማብራራት ጀምረዋል።

ለዋና ኮሚሽነርነት የተጠቆሙትን ግለሰቦች 73 ወንድ እና 15 ሴት እጩዎች የትምህርት ማስረጃቸውን እና የሥራ ልምዳቸውን በመገምገም ዳንኤል በቀለ ባላቸው የሥራ ልምድና የላቀ የትምህርት ዝግጅት በአንደኝነት እንዲመረጡ መደረጉን አብራርተዋል።

ዳንኤል በቀለም ከሕዝብ እንደራሴዎቹ የተነሳውን ተቃውሞ በተመለከተ ለአዲስ ማለዳ ማብራሪያ ሲሰጡ አስተዳደራዊ ልምድ ማነስ በሚለው እምብዛም የሚቀበሉት እንዳልሆነና በርካታ አስተዳደራዊ ልምድ እንዳካበቱ አስረድተዋል። የተመረጡበት መንገድ ገለልተኛ በሆኑ አጣሪ ኮሚቴዎች የተወዳዳሪዎች የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት አጥንተው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዋና ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በዓለም ዐቀፍ ሕግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸው የተገለፀ ሲሆን በተለያዩ ዘመናት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና በሂውማን ራይትስ ዎች በአማካሪነት እና አድቮኬተር ሆነው አገልግለዋል። ከሕዳር 2010 እስከ ተሾሙበት ዕለት ድረስም በሰብኣዊ መብቶችና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ልማት ተመራማሪነትና አማካሪነት በማገልገል ላይ ይገኙ ነበር። ሰኔ 15/ 2011 ለሕዝብ እንደራሴው የቀረበው የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሹመት በአንድ ድምፀ ታዕቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here