በሶማሌ ክልል ከዚህ ቀደም ተከስቶ በነበረው ግጭት ከቀያቸው ተፈናቅለው ለነበሩ ወገኖች የሥነ አዕምሮና የሥነ ልቦና ድጋፍ አገልግሎት ከክልሉ በሰለጠኑ ባለሙያዎች አማካይነት በኮሎጂ የተፈናቃዮች ካምፕ እየተሰጠ መሆኑን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ተፈናቃይና ተመላሽ ወገኖች በሚገኙባቸው ወረዳዎች ወረርሽኞች እንዳይከሰቱም የቅድመ መከላከል ተግባራት ማለትም የበሽታዎች ቅኝትና አሰሳ ተጠናክረው እየተከናወኑ እንደሚገኙም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።
እንደ ኢንስቲትዩቱ ገለጻ ከግንቦት 24 – ሰኔ 30/2011 ድረስ ከ9 ሺሕ በላይ በሽተኞች የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። እንዲሁም ከ2 ሺሕ በላይ እናቶችና ሕጻናት እንዲሁም ሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት አግኝተዋል።
በአጠቃላይ ለተፈናቀሉና ለተመላሽ ወገኖች እንዲሁም ለተከሰቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት ለመድኀኒትና የሕክምና ቁሳቁሶች አቅርቦት፣ ለተመደቡ የሰው ኀይልና ለተሸከርካሪዎች ወጪ፣ እንዲሁም ለክልሎች የሥራ ማስኬጂያ ድጋፍ ከሚያዝያ 23/2011 እስከ አሁን ድረስ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኗል።
ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011


