“በእኔ ሥም አይሆንም!”

0
1406

ቁምላቸው አበበ የአሜሪካውያኖችን “በእኛ ሥም አይሆንም!” ሕዝባዊ ንቅናቄ መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ለውጥ መጣ በተባለበት ማግሥት፥ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን፣ ግጭቶን፣ መፈናቀሎች፣ የደቦ ፍርዶችና ሌሎች የተፈጸሙ ዘርፈ ብዙ ወንጀሎችና የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች በእኛ ሥም አይሆንም ብለን ማስቆም አለብን ሲሉ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

“በእኛ ሥም አይሆንም!” በአሜሪካ በመስከረም 1/1993 በተለምዶ ‘9/11’ ላይ አልቃይዳ በአሜሪካ ላይ የሽብር ጥቃት መፈፅሙን ተከትሎ አሜሪካ አፍጋኒስታንን ጨምሮ በኢራቅና በቀጣናው ያወጀችውን ጦርነት ዜጎች በመቃወም በየካቲት 23/2002 (እ.ኤ.አ) የተቋቋመ ሕዝባዊ ንቅናቄ ነው። ቻርሊ ሀደን የተባለ ታዋቂ አቀንቃኝ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሊየር ኢራቅ ላይ ለፈጸሙት ወረራ ለፍርድ ይቅረቡ የሚል መልዕክት ያለው “Not In Our Name” የተሰኘ የዘፈን ሲዲ መልቀቁንም አስታውሳለሁ።

በአገራችን በተለይ ካለፈው አንድ ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት እዚህም እዚያም በዘውግ፣ በማንነት፣ በጎሳ ሥም ዜጎች እየተገደሉ፣ እየተፈናቀሉ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት እየተዘረፈ፣ የዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት የመንቀሳቀስ መብት እየተገደበ፣ የአገር የግዛት አንድነት አደጋ ላይ እየወደቀ፣ የሕግ የበላይነት እየተደፈቀ ከፍ ሲልም እንደ አገር የመቀጠል ጉዳይ ጥያቄ ላይ እየወደቀ ነው። በሶማሊያና በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ፣ በአማራና በቤኒሻንጉል፣ በአማራና በትግራይ፣ በጉጂና በጌዲዎ፣ በቅማንትና በአማራ ወዘተ የተከሰቱ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በአብነት ማንሳት ይቻላል። በጅግጅጋና በምዕራብ ኦሮሚያ የአገሪቱን የግዛት አንድነትና ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣሉ፣ ለመስማት የሚዘገንኑ የሰብኣዊ መብት ጥቃቶችና ማንነትን መሰረት ያደረጉ የጅምላ ግድያዎችን ዛሬ ድረስ የምናስታውሳቸው ዋና ዋና ሰቆቃዎች ናቸው።

ሆኖም እነዚህን ሁሉ ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ጭፍጨፋዎችና ዘረፋዎች በእኛ ሥም ጥቂት ፅንፈኞች የፈጸሟቸው ናቸው። አዎ! በእኛ በኢትዮጵያውያን (በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በትግራዋይ፣ በሶማሌ፣ በሲዳማ፣ በጌዲዖ፣ በጉጂ፣ በጉምዝ፣ በበርታ፣ በቅማንት፣ በሸካ ወዘተ) ሥም የተፈፀሙ ናቸው። የእኛን የብዙኀኑን ይሁንታ፣ ድጋፍ ሳያገኙ በእኛ ሥም ሲፈፀሙ “በእኛ ሥም አይሆንም!” አይደረግም፤ አላልንም። ይህ ዝምታ፣ ቸልታ ነገ በፍትሕ አደባባይ ባያስጠይቀንም በትውልድና በታሪክ ማስጠየቁ አይቀርም።

ትላንት ክልሌን ለቀህ ውጣ ተብሎ የመጀመሪያው ወገናችን ሲፈናቀል እኛ ብዙኀኖች “በእኛ ሥም አይሆንም!” አፈናቃዩ እኛን አይወክልም ብለን ከጅምሩ አምርረን አቋማችንን ብናሳውቅና ብንታገል ኖሮ ኋላ ላይ ሚሊዮኖች ባልተፈናቀሉ፣ ወሰኔን ገፍተሀል በሚል የአንድ ክልል ሚሊሺያ ከሌላው ጦርነት ገጥሞ ንፁሐን ሲገደሉ፣ ሲቆስሉና ሲፈናቀሉ “በእኔ ሥም አይሆንም!” ብንል እስከ ዛሬ በመቶዎች አልያም በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ባልተገደሉ፤ ከመፈናቀል ከመገዳደል በላይ በወገኖቻችን መሐል መጠራጠርና ቂም ባልሰፈነ፤ ከዚህ ከፍ ሲልም እንደ አገር የመቀጠል ያለመቀጠል የማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት የሥጋት ዳመና በአገራችን ሰማይ ባላንዣበበ፤ እንዲህ ማጣፊያው ባላጠረን፤ ስለሆነም በአንድም በሌላ በኩል በአገራችን ለተስተዋሉ ችግሮችና ለተደቀኑ አደጋዎች እጃችን አለበት። በትውልድም በታሪክም ተጠያቂ ነን።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች የጥላቻ፣ የጎሰኝነት፣ የቂም በቀል መርዘኛ ፍላፃዎች በሥማችን ሲንበለበሉ ከፍ ሲልም የግጭት፣ የጦርነት፣ የመገንጠል ነጋሪቶች በሥማችን፣ በማንነታችን በፌስ ቡክ ሲጎሸሙ “በእኛ ሥም አይሆንም!” ብለን በአደባባይ ባለመጮሀችን በሀፍረት አንገታችን የሚያስደፉ ነውሮች ተፈፅመዋል፤ እየተፈፀሙም ነው። በሥማችን፣ በማንነታችን የሚነዛ የበሬ ወለደ ሐሰተኛ የተዛባ መረጃን፤ የደባ፣ የሴራ ፖለቲካን “በእኔ ሥም አይሆንም!” ለማለት አንደበታችንን ማን ሸበበው? ብዕራችንን ማን አዶሎደመው? የሥልኮቻችንን፣ የኮምፒውተሮቻችን ኪቦርድ ማን ቆለፈው? የቅስም ቀውሱን፣ ድንዛዜውን ማን አጋባብን? አንገታችንን ማን አደነደነው? ልባችንን ማን ደፈነው? ይሔ ሁሉ ኬሬዳሽነት ከየት መጣ? ስንል ቆመን የምናስብበት ወደቀልባችን የምንመለስበት ወሳኝ ሰዓት ላይ እንገኛለን። ጥቂቶች ሥማችንን ማንነታችንን ነጥቀው በሥማችና በማንነታችን የሚፈጸሙትን ግፍ ወንጀል በድፍረት ከአሁን በኋላ በቃ! (Enough is Enough!) “በእኛ ሥም አይሆንም!” በማለት የተነጠቅነውን ሥማችንን ማንነታችንን ምርኳችን ካላስመለስን እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ የተደቀነብንን አደጋ በቀላሉ መሻገር ይቸግረናል።
እንዲሁም በፌደራል፣ በክልል በግልና በድርጅት መደበኛ ሚዲያ ማለትም በኅትመትና በኤሌክትሮኒክስ (በጋዜጣ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን) በማንነታችን በሥማችን ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከእርቅ ይልቅ ጥል፣ ከመተባበር ይልቅ መፎካከር፣ ከመነጋገር መኳረፍ፣ ከመቀባበል መገፋፋት፤ ሲቀነቀን ሲለፈፍ ሰምተን እንዳልሰማን ዓይተን እንዳላየን አንብበን እንዳላነበብን ያለፍነው፤ የማንነት የዘውግና የጎሳ አሰላለፍ ዛሬ በአገራችን ለተቀለሱት የጭፍን ጥላቻ፣ የቂም፣ የዘውጌያዊነት፣ የደባ ፖለቲካ፣ የመጠራጠር፣ የመጠላለፍ፣ መሪን የመብላት፤ ጎጆዎች ዋልታና ማገር አቀብለዋል።

አስራት ቲቪ፣ ድምፀ ወያኔ፣ ኦኤምኤን፣ በረራ ያጤኗል! እነዚህን ሚዲያዎች የሚደግፉ ግለሰቦችና ተቋማት መኖራቸው ደግሞ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል “በእኛ ሥም አይሆንም!” ማለቱ ቀረና ደጋፊ አጋር እስከ መሆን መደረሱ የአደጋውን አሳሳቢነት ይጠቁማል። በማንነታችን በሥማችን ፈር የለቀቁ አገርን ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎችን በወቅቱ በአንድነት ድምፃችንን ከፍ አድርገን “በእኛ ሥም አይሆንም!” ባለማለታችን በማርፈዳችን፤ ዛሬ ተቋማዊ መዋቅራዊ ፈተናዎች ሆነዋል። ስለዚህ “በእኛ ሥም አይሆንም!” ከማለት ጎን ለጎን ተቋማዊ ጥረትን ምላሽን ይጠይቃሉ።

ሰኔ 15/2011 መጀመሪያ በባሕር ዳር በኋላ በአዲስ አበባ የተፈጸመው ጀብደኛ ግድያ፤ የዝምታችን፣ የድንዛዜያችን፣ የግዴለሽነታችን፣ የእንዝህላልነታችን ከፍታ፣ ጡዘት ማረጋገጫ፣ ማሳያ ነው። የቀጣይ አካሔዳችን፣ የታሪካችን ወሳኝ መታጠፊያ ነው። ከእያንዳንዱ የግጭት መካረር፣ ጡዘት በኋላ የሁኔታዎች መቀየር የግድ መሆኑን መቀበል ተፈጥሮአዊም፣ ሰዋዊም ነው። ድምጻችን ከፍ አድርገን “በእኛ ሥም አይሆንም!” የምንልበት ቀን አፍጥጦ ደጃችን ላይ ቆሟል። ቀኑን በአግባቡ መጠቀምም ዘመኑን የሚመጥን የሚዋጅ እርምት በጊዜ የለም ስሜት መውሰድ ደግሞ የቀረን ብቸኛ ካርድ ነው። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በሥማችን በማንነታችን የሚነዙ የጥላቻ መርዞች፣ የደባ ፖለቲካ ሴራዎች፣ የሚንበለበሉ የቂም ፍላጻዎች በጊዜ ባለመመከታቸው ዛሬ ጎልምሰው ተቋማዊ፣ ስርዓታዊ፣ መዋቅራዊ ሆነዋል። ስለሆነም የሚመጥን ሕጋዊና ተቋማዊ እርምጃ የመውሰጃ ትክክለኛው ጊዜ ላይ ደርሰናል።

አሜሪካውያን መብታቸውን ተጠቅመው በድምጻቸው የሾሙት መንግሥት እንኳን ከአንዴም ኹለት ሦስቴ ያሰመሩለትን ቀይ መስመር ጥሷል ብለው ባመኑ ጊዜ አደባባይ ወጥተው “በሥማችን አይሆንም!” ብለውታል። አሜሪካ ተገድጄ ገባሁበት በምትለው ኹለተኛው የዓለም ጦርነት በጃፓን የሔሮሽማና ነጋሳኪ ከተሞች የመጀመሪያውን የአቶሚክ ቦንብ ጥቃት ሲፈፅም፤ በአሜሪካ የሚገኙ ጃፓናውያንንና ትውልደ ጃፓን አሜሪካውያንን ለደኅንነቴ ያሰጉኛል በማለት በማጎሪያዎች ሰብስቦ ሲያጉር፤ ቬትናምን ሲወር፤ የመስከርም 11 የአልቃይዳ የሽብር ጥቃት ተከትሎ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ

“ከእኛ ጎን ትቆማላችሁ አልያም በእኛ ላይ ተነስታችኋል፤ በማለት ኢራቅን አፍጋኒስታንን በወረሩ ወቅት፤ አብዛኛው አሜሪካዊ አደባባይ በመውጣት ድምፁን ከፍ አድርጎ “በእኛ ሥም አይሆንም!” በማለት በመንግሥታቸው ላይ ጫና በመፍጠር ለውጥ አምጥተዋል።

ወደ አገራችን ስንመጣ በእኛ ላይ ራሳቸውን በጎበዝ አለቅነት የሾሙ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች፣ የመብት ወትዋቾች፣ ጦማሪያን፣ ሚዲያ ተብዬዎች፤ በኢትዮጵያዊነታችን አልያም በማንነታችን ሥም ትርምስ፣ ቀውስ፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ ጦርነት፣ ዕልቂት ሲደግሱልን ዝምታን በመምረጥ የጥፈታቸው ተባባሪ እየሆን ነው። ትላንት በባሕር ዳርና በአዲስ አበባ፣ ከዚያ በፊት በጅግጅጋ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ በሥማችን ለተፈፀመው ግፍ፣ ሞት፣ መቁሰል፣ መነቀል በዝምታ ስለተመለከትን ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን፤ አዎ! ወደድንም ጠላን ከግፈኞች ይልቅ ግፉ ሲፈፀም አይተው እንዳላዩ፤ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነው ዝምታን የመረጡም ተጠያቂዎች ናቸው እንደሚባለው ፤ ከላይ እንዳልሁት በቀጣይ ትውልድ ታሪክ ይጠይቀናል።

እንደ መላ
ዛሬ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ከእነፈተናዎቹ እየደገፈው ያለ ሕዝብ ብዙኀኑ ቢሆንም ድጋፉን በአደባባይ፣ በማኅበራዊ እና መደበኛ ሚዲያዎች የብዛቱን ያህል ድምፁን ከፍ አድርጎ ስለማያሰማ ለውጡን በሚያጠለሸው፣ በሚያጣጥለው፣ በሚቃወመው ሕዳጣን፣ ሕዳጣን ጩኸት ተውጧል፤ ጩኸቱን ተቀምቷል። ጥቂቶች ማኅበራዊ ሚዲያውን ተቆጣጥረው የሚነዙት ሐሰተኛ ዜና እና የተዛባ መረጃ እንዲሁም የደባ የሴራ ፖለቲካ፤ ፖለቲካዊ ምኅዳሩን ተቆጣጥረውታል ማለት ይቻላል። በዚህም በኀይለኛ የባሕር ማዕበል እንደምትናወጥ ጀልባ ምትክ የሌላትን አገራችንን እያላጓት ነው። ማዕበሉን በአንድነት ካልገሰጽነው ጀልባዋ አደጋ ላይ መውደቋ አይቀርም፤ ሰሞኑን ስለ ሰኔ 15ቱ “መፈንቅለ መንግሥት!” እየተራገበ ያለው የበሬ ወለደ ወሬ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ስለሆነም ዝም ያለው ብዙኀን ዝምታውን ሰብሮ “በእኛ ሥም አይሆንም!” የብዛቱን ያህል ተቀናጅቶና ተደራጅቶ ድምፁን ከፍ አድርጎ በመጮህ አናሳዎች የነጠቁትን ብኩርና ድምፅ ሊያስመልስ ይገባል። ነጮች ፀጥ ያለው ብዙኀን (the silent majority) የሚሉት አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በተለያዩ ምክንያቶች ዝምታን፣ ዳር ቆሞ መመልከትን በመምረጡ፤ ጥቂቶች ለውጡን በመቀልበስ አገሪቱን መቀመቅ ለማውረድ ተቃርበዋል። ድንዛዜው፣ ድባቴው፣ አርምሞው በዚህ ከቀጠለ እንደ ትላንት ከትላንት በስቲያው ብዙኀኑ በአገሩ ጉዳይም ዳግም ባይተዋር መሆኑ አይቀርም ።

ስለዚህ ዝምታውን ሰብሮ ቸልታውን ወደጎን ትቶ በአገሩ ዕጣ ፈንታም ሆነ በልጆቹ ኢትዮጵያ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን በጋራ ድምፅ “በእኛ ሥም አይሆንም!” በማለት ነገ ዛሬ ሳይል በድፍረት ፖለቲካዊ ምህዳሩን ከጥቂቶች መዳፍ ፈልቅቆ በእጁ ማስገባት ይጠበቅበታል። ሰኔ 15/2011 በመጀመሪያ በባሕር ዳር በኋላ በአዲስ አበባ በጀብደኝነት የተፈፀመው ግድያም ሆነ የከሸፈው “መፈንቅለ መንግሥት” በእኔ ሥም አይሆንም!” ብያለሁ። “እናንተስ!?”

በቁምላቸው አበባ ይማም (ሞሼ ዳያን) በጋዜጠኝነት ሙያ የተሰማሩ ባለሙያ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው fenote1971@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here