እገዳ የተጣለባቸው ቡና ላኪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ

ከወራት በፊት በተለያዩ ምክንያቶች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዳይገበያዩ እገዳ የተጣለባቸው 81 የሚደርሱ ቡና ላኪዎች ጉዳያቸው ታይቶ ፈቃዳቸው የተመለሰ ቢሆንም እስካሁን ንግዳችንን በአግባቡ መምራት አልቻልንም ያሉ ከ50 በላይ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን ገለፁ። ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም 81 ቡና ላኪዎች ሲታገዱ በወር ውስጥ 22 ለሚሆኑ ላኪዎች ፈቃዳቸው ተመልሶላቸው እንደነበር ጠቁመው፥ ሌሎቻችን በምን ምክንያት እገዳው ሳይነሳልን እንደቆየ አናውቅም ሲሉ ገልፀዋል።

ውል በገቡበት ጊዜ ገደብ የቡና ምርታቸውን ለዓለም ዐቀፍ ገበያ ወይም ለውጭ ተቀባዮቻቸው አላደረሱም በሚል እና ዓለም ዐቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ሳያገኙ ሲልኩ ነበር ያላቸውን 81 ቡና ላኪዎች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዳይገበያዩ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ማገዱ የሚታወስ ሲሆን፤ ከኻያ የሚልቁትን ጉዳያቸውን አጣርቶ ወደ ሥራ መልሷቸው ነበር። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት ከ50 በላይ የሚሆኑት ላኪዎች ፈቃዳቸው ከተመለሰላቸው ድርጅቶች የተለየን ባለመሆኑ እገዳው ሊነሳልን ይባገባል ሲሉ ቢጠይቁም ጉዳያቸውን የሚያይላቸው አካል አለማግኘታቸውን በሚመለከት ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን የሥራ ኀላፊዎችን ባነጋገረችበት ወቅት ጉዳያቸውን በአግባቡ እየታየ እንደሚገኝ እና በየጊዜው አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ እና እርማት እንዲወስዱ ተደርጎ ፈቃዳቸው እየተመለሰላቸው እንደሚገኙ ገልፀው፥ ከግማሽ በላይ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲገበያዩ እንደተፈቀዳለው እና ቅሬታ አቅራቢዎች የሚያቀርቡት ቁጥር እጅግ የተጋነነ ነው ብለዋል። በቡና እና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክተር ትዕዛዙ ኢዶሳ ለአዲስ ማለዳ ሲገልፁ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ሥራውን በአግባቡ እየሠራ እንደሚገኝ እና ፈቃዳቸው ያልተመለሰላቸው ድርጅቶችም በቅርቡ እንደሚመለሱ ጠቁመዋል።

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፤ በተደጋጋሚ ፊርማዎችን አሰባስበው ወደ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቢሮ ቢመላለሱም እልባት የሚሰጣቸው ባለማግኘታቸው ትርፉ ድካም ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል። አያይዘውም በኢትዮጵያ የቡና ዋጋ በታሪክ ከፍተኛውን ዋጋ ማሽቆልቆል ባሳየበትና ምርቱን ለዓለም ዐቀፍ ገበያ ማቅረብ ተግዳሮቶች በበዙበት ጊዜ በትጋት ሲሰሩ የነበሩ ቡና ላኪዎችን ማገድ ችግሩን ማባባስ እንደሆነና ታገዱበት የተባለው ምክንያት በእርግጥም ተከስቶ ቢሆን በሥራ ላይ እያሉ ሊታረም የሚገባ ነው ብለዋል።

አምስት እና ከዛ በላይ ወራትን በእገዳ ላይ የሚገኙት ቡና ላኪዎች ለበርካታ ዘርፈ ብዙ ችግች መጋለጣቸውን እና አሁንም የሚመለከተው አካል ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል። በምርት ገበያ እንዳይገበያዩ ተብለው ዕገዳ ከተጣለባቸው ቡና ላኪዎች ውስጥ የሚገኙት መኩሪያ ዓለማየሁ በዕገዳው ምክንያት ለረጅም ጊዜ በቋሚነት ቡና ሲረከቧቸው የነበሩ ዓለም ዐቀፍ ደንበኞቻቸው መራቃቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here