የአዲስ አበባ “ቡና ሱቆች” ዓይነተ ብዙ – ከፍተኛ ዋጋ

0
1384

አስቴር ደምሴ የቀይ ዳማ ቆዳ፣ ስታወራ ፈገግታ የማይለያት ፍልቅልቅ የ27 ዓመት ወጣት ስትሆን ለገሀር አካባቢ በሚገኝ የግል ባንክ ውስጥ በሒሳብ ባለሞያነት ተቀጥራ እየሠራች ትገኛለች። “ቡና ሳልጠጣ መዋል አልችልም” የምትለው አስቴር በቀን ቢያንስ ኹለት ጊዜ ቡና የምትጠጣ ሲሆን ምሳ ከበላች በኋላ ከጓደኞቿ ጋር ኮሜርስ ጀርባ የሚገኘው የጀበና ቡና መሸጫ ቤት መሔድ ብታዘወትርም አንዳንዴ ደግሞ ስቴዲየም አካባቢ የሚገኘው ጫካ ቡና ትሔዳለች። አስቴር ˝ቡና ባሕላችን ከመሆኑ በተጨማሪ የማነቃቃት አቅም ስላለው በብዙ ሰዎች ዘንድ ተመራጭ ነው። ሲቆላ መዓዛው የሚስብና ጣዕሙም መልካም መሆኑ ደግሞ ተወዳጅ ለመሆኑ ተጨማሪ ምክንያት ነው” በማለት ትናገራለች። በሥራ ቀናት አዘውትራ ከምትሔድበትና የጀበና ቡና ከሚሸጥባቸው ቦታዎች በተጨማሪ በእረፍት ቀናቶች ከጓደኞችዋ ጋር ምቾት ያላቸውና በደረጃ ከፍ ወዳሉ እንደ ቶሞካ፣ ካልዲስና ግሪን ጎልድ ያሉ የቡና መሸጫ ቦታዎች ትሔዳለች።

ኢትዮጵያዊያን ከሚታውቁበት ነገሮች አንዱ ቡና በመሆኑ እንደአስቴር ያሉ በርካታ ሰዎች ከቡና ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቡና አምራች አገር ከመሆንዋ በተጨማሪ ለየት ባለ የቡና አፈላል ስርዓቷ ትታወቃለች። ታጥቦ፣ በብረት ምጣድ ወይንም ማንከሽከሻ ተቆልቶ፣ በሙቀጫ ተወቅጦ የሚጀምረው የቡና አፈላል ስርዓታችን አቦል፣ ቶናና በረካ ተብሎ እስከ ሦስተኛ ድረስ በመጠጣት ይጠናቀቃል።

ይሁንና ለዓመታት ቡና ቤት ሲባል ወደ ሰው አዕምሮ የሚመጣው ከባንኮኒ ጀርባ በመጠጥ የተከበበ ግርግዳ፣ እስኪያልባቸው ደንሰው ላባቸው ግንባራቸው ላይ ችፍ ችፍ ያለ ወጣቶች የተጋመሰ የመጠጥ ጠርሙስ ከበው ሲስቁ፣ ሕይወት ፊቷን አዙራባቸው በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ላይ የተሠማሩ እህቶች የሚገኙበት ስፍራና በጫጫታ የተሞላ ቦታ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህን ቡና ቤት ሲባል መጠጥ ቤት ትዝ እንዲለን የሚያደርገውን ለብዙ ጊዜ የቆየ ሁኔታ የሚቀይር ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን ውስጥ ብቅ እያለ ይገኛል። ምንም እንኳን በግልጽ ቡና ቤት ተብሎ በአማርኛ ባይጻፍባቸውም በዋናነት የቡና መሸጫ ቤት እንደሆኑ እንዲያስታውቅና ሥማቸው ከቡና ጋር ተያይዞ እንዲነሳ የሚፈልጉ ነጋዴዎች ከንግድ ቤታቸው ሥም ቀጥሎ ‘ኮፊ’ የሚል ነገርን በማስከተል ሥም እያወጡ እንደሚገኙ ለማሳየት ካልዲስ ኮፊ፣ አፍሮ ፍሌቨር ኮፊ፣ ዚንግ ኮፊና መሰል የቡና መሸጫ ሱቆችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ዚንግ የፕራይም ሮዝ እህት ኩባንያ ሲሆን ፕራይም ሮዝ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ቡናን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል። አሁን ደግሞ ከኹለት ወር በፊት ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በከፈቱት በዋናነት የቡና መሸጫ ሱቅ ውስጥ በዓይነታቸው ለየት ያሉ ትኩስና ቀዝቃዛ ቡና በመሸጥ ላይ ናቸው።

ዚንግ የቡና መሸጫ ካፌ በአገራችን እንብዛም ያልተለመዱ እንደ የቡና ድራፍት ያሉ የቡና ዓይነት ለደንበኞች በማቅረብ ይታወቃል። በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ቡናን ወደ አልኮል መጠጥነት መቀየር እንደሚቻል የምትናገረው የዚንግ የግብይትና ማስተዋወቅ ባለሞያ የሆነችው ረቂቅ አስራት፥ በዚንግ የሚገኘው የቡና ድራፍት ከአልኮል ነጻ ሆኖ በከፍተኛ የአየር ግፊት ቀለምና ጣዕም የሌለው የናይትሮጂን ጋዝን በመጨመር የድራፍት ጣዕም እንዲኖረው ተደርጎ የተጠመቀ ነው ብላለች። በዚንግ የቡና መሸጫ ውስጥ በቀዝቃዛ ውሃ የተጠመቀ የቡና ድራፍትን (ናይትሮ ኮፊ) በሰባ አምስት ብር ማግኘት ይቻላል።

ሌላው ደግሞ ድሪፕ ቦክስ በመባል የሚታወቀው የቡና ዓይነት ሲሆን ይህ የቡና ዓይነት በስሱ ተቆልቶ በካርቶን የታሸገ ነው። በአንዱ ካርቶን ውስጥ ስምንት የቡና ከረጢቶች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ከረጢቶች በቡና ስኒ ላይ በማስቀመጥና በአናቱ ሙቅ ውሃ በመጨመር የተጣራ ቡና ማግኘት ይቻላል። አንዱ ካርቶን ድሪፕ ቦክስ በ150 ብር ይሸጣል።

ረቂቅ “ምንም እንኳን አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ቡና ካልተፋጀ ምኑን ቡና ሆነ የሚሉ ቢሆንም ዓላማችን ቡናን በተለያየና ምቹ በሆኑ መንገዶች በማዘጋጀት ማስተዋወቅና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ የቡና አፈላል ዓይነቶችን ወደ አገራችን ማምጣት ነው” በማለት ዚንግ የቡና መሸጫ ሱቅን ለየት ባለ መንገድ የከፈቱበትን ምክንያት ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች። “ለምሳሌ በአገራችን በፕላስቲክ ጠርሙሶች ታሽገው የሚሸጡት የለስላሳ መጠጦችና ውሃ እንጂ ቡና አይደለም። እኛ ግን ቀዝቃዛ ቡናን በፕላስቲክ ጠርሙስ በግማሽ ሊትር በማዘጋጀት በ150 ብር ለገበያ አቅርበናል” በማለት አክላለች። ይሁንና የብዙ ደንበኞቻቸው ምርጫ የለመደው ትኩስ ቡና በመሆኑ የቀዝቃዛ ቡና ተጠቃሚዎች ቁጥር ጥቂት መሆኑን ረቂቅ ተናግራለች።

በዚንግ ቡና ሲዘጋጅ የሙቀት መጠኑ ተመጥኖ እንዲሁም ቡናው ሲቆላ ሳይጠቁር በመሆኑ የተፈላው ቡና አይመርም እንዲሁም ከልክ በላይ አያቃጥልም። በመሆኑ አንዳንድ ደንበኞች ወፈር ያለ ቡና መረር ይላል ከሚል መነሻ በወረደ ቡና ይሠራ እንዲሁም ትኩስ አድርጉት በማለት ቅሬታቸውን እንደሚያቀርቡ ረቂቅ አልሸሸገችም።
ሌላው ደረጃቸው ከፍ ካሉ የቡና መሸጫ ቤቶች ውስጥ የሚጠቀሰው ሰሚት አካባቢ የሚገኘው አፍሮ ፍሌቨር ኮፊ አንዱ ነው። በአፍሮ ፍሌቨር ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆነው አፈወርቅ ንጉሤ እንደገለጸው ከሆነ አፍሮ ፍሌቨር ቡናን ለውጪ ገበያ በማቅረብ እንደሚታወቅና በጋንቤላ 2 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የቡና እርሻ እንዳላቸው ገልጿል። በካፌያቸው ውስጥም ጥራት ያለው ቡናን እንደሚያቀርቡ አክሏል።

አፍሮ ፍሌቨር የውስጠኛው ክፍል ግድግዳ በተለያዩ ስዕሎች ያጌጠ ሲሆን ሰፋ ያለው የታችኛው ክፍል (‘ግራውንድ’) ውስጥ የተዘረጋ ስኒና ረከቦት፣ የሕጻናት መጫወቻዎች፣ ማንኛውም ደንበኛ ቡና እየጠጣ ሊያነባቸው የሚችል ከአርባ በላይ መጻሕፍት ይዟል። ወላጆች ከላይ ቡና እየጠጡ ሲያወጉ ሕጻናት ልጆቻቸው የታችኛው ክፍል ውስጥ እንዲጫወቱና ለደንበኞቻቸው ምቾት ሲሉ የሕጻናት መጫወቻ ስፍራውን እንዳዘጋጁ የሚናገረው አፈወርቅ ቀለል ያለ ቤተ መጽሐፍት እንዲሆን ታስቦ የተሠራው የመጽሐፍት መደርደሪያ ስፍራው ደግሞ የደንበኞችን የማንበብ ልምድ ለማበረታታትና ለማጎልበት ይረዳል በሚል እምነት እንደተዘጋጀ ገልጿል። ቦታው ጸጥ ያለ በመሆኑ ለንባብ ይመቻል ያለው አፈወርቅ ደንበኞቻቸው የራሳቸውንም መጽሐፍ ይዘው መጥተው ማንበብ እንደሚችሉ ተናግሯል።

በአፍሮ ፍሌቨር ከስፕራይትና ከቶኒክ ጋር የተቀላቀለ ቡና በ25 ብር የሚሸጥ ሲሆን ቡና ብቻውን ደግሞ በ20 ብር ማግኘት ይቻላል። አፍሮ ፍሌቨር ቀዝቃዛ ቡናን መሸጥ ጀምረው የነበረ ቢሆንም የቀዝቃዛ ቡና ፈላጊ ደንበኞቻቸው ቁጥር ትንሽ በመሆኑ ለጊዜው ቀዝቃዛ ቡናን መሸጥ አቁመዋል። ˝ቀዝቃዛ ቡናን ለመጥመቅ አንድ ቀን ይፈጃል። ለምሳሌ ዛሬ ከተጠመቀ ነገ ነው ለመጠጣት የሚደርሰው። ደንበኛ ከሌለ ግን ይደፋል። ቀዝቃዛ ቡና ወዲያው ተጠምቆ ወዲያው ስለማይደርስ የቀዝቃዛ ቡና ፈላጊዎቻችን ቁጥር እየጨመረ እስኪመጣ ድረስ ለጊዜው ቀዛቃዛ ቡና መጥመቅ አቁመናል ˝ ሲል አፈወርቅ ቀዝቃዛ ቡና መጥመቅ ያቆሙበትን ምክንያት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

ከአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ ቀጥላ ወደ ውጪ በምትልከው የቡና መጠን በኹለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ደግሞ ከብራዚል፣ ቬትናም፣ ኮሎምቢያና ኢንዶኔዢያ ቀጥሎ ቡናን በማምረት ትታወቃለች። ባሳለፍነው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመረተው 469 ሺሕ ቶን ቡና ውስጥ ከ225 ሺሕ ቶን በላይ የሚሆነውን ደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካንና ጀርመን ጨምሮ ወደ 60 የውጪ አገራት በመላክ ከ881 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች። ከ244 ሺሕ ቶን በላይ የሚሆነው ቡና ደግሞ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ውሏል። ከ15 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ቡናን በማምረት ተግባር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here