የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ የማቋረጥ ውሳኔ እና የሚያሳድረው ተጽዕኖ

0
702

በአዲስ ማለዳ ሰኔ 22/2011 (ቅፅ 1 ቁጥር 34) “በዐቃቤ ሕግ የሚቋረጡ ክሶችን የሕግ ባለሙያዎች ተቃወሙ” የሚል ትንታኔን መነሻ በማድረግ ካሣዬ አማረ ዐቃቤ ሕግ የደረሰበትን ውሳኔ ሐሳብ በመቃወም የራሳቸውን መከራከሪያ አቅርበዋል።

በአዲስ ማለዳ ሰኔ 22/2011 (ቅፅ 1 ቁጥር 34) “በዐቃቤ ሕግ የሚቋረጡ ክሶችን የሕግ ባለሙያዎች ተቃወሙ” የሚል ትንታኔን መነሻ በማድረግ ካሣዬ አማረ ዐቃቤ ሕግ የደረሰበትን ውሳኔ ሐሳብ በመቃወም የራሳቸውን መከራከሪያ አቅርበዋል።

ለመንደርደሪያነት እንዲረዳ በአዲስ ማለዳ ላይ የወጣው ጽሁፍ “የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት በመንግሥት ላይ 11.9 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ከአንድ ዓመት በፊት ተመሥርቶባቸው የነበሩት የቀድሞ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጄክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፀዳለ ማሞን ጨምሮ የአራት ኀላፊዎች ክስ ተቋርጦ ከእስር የተፈቱት ኅዳር 11/2011 ነበር” ይላል። ይህ ወሳኔ እና ሌሎች ከዚህ በፊት የተወሰኑ ጉዳዮች ተግባራዊ የተደረጉ ስለሆነ የጽሁፉ ዓላማ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳየት ለወደፊቱ ምን ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ መጠቆም ነው።

የሕግ ባለሙያዎቹ እንደሚሞግቱት ውሳኔው የተነሳበት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀፅ (6) ንዑስ አንቀፅ (3ሠ) በተሰጠው ክስ የማቋረጥ ሥልጣን ላይ ሦስት ክፍተቶች አሉት። አንደኛው “ለሕዝብ ጥቅም ሲባል” የሚለው ሐረግ በአዋጁ ውስጥ በግልፅ ያልተቀመጠ ስለሆነና ውሳኔ በሚሰጠው አካል በተለያየ ጊዜ እና ሁኔታ ትርጓሜው ሊለዋወጥ ስለሚችል አከራካሪ እንደሚያደርገው፣ በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ የወንጀል ሥነ ሥርዐት ሕጉ ለአቃቤ ሕግ ክስ የማቋረጥ ሥልጣን እንዳልሰጠው እና የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ 943/2008 አንቀፅ (6) ንዑስ አንቀፅ (3ሠ) ግን ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲያቋርጥ ሥልጣን ይሰጠዋል። በሦስተኛ ደረጃ ዐቃቤ ሕግ ክስ ይቋርጥ ሲል ፍርድ ቤት የሚቋረጥበትን ምክንያት የመጠየቅ መብት እንደሌለው ያስረዳል።

የዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ሀብት የመዘበሩ ግለሰቦችን ክስ ማቋረጥ አያሌ አሉታዊ ውጤቶች ማስከተል መቻሉ አከራካሪ አይደለም። የአገር ሀብት በመመዝበሩ ምክንያት ክስ ተመሥርቶባቸው እና ዋስትና ተከልክለው በክርክር ላይ የነበሩትን ግለሰቦች (በተለያየ ኀላፊነት ላይ የነበሩ) ክሳቸው መቋጫ ላይ ሳይደርስ መቋረጡ ሕዝቡ በራሱ እና ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚያደርገውን ትግል ወደ ምንቸገረኝነት የሚያሸጋግረው መሆኑ እና አያገባኝም ወደሚለው የከፋ አስተሳሰብ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑ በጥብቅ ሊጤን ይገባዋል። ውሳኔው ከሕግ ይልቅ ጠባብ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት እንደሆነ የሚነገርለት ጣልቃብነት አሁንም በፍትሕ ሰርዓቱ ውስጥ እንዳለ እና የፍትሕ አካላት በነፃነት ሊንቀሳቀሱ እንደማይችሉ እንደማሳያ ሊያገልግል ይችላል። በተለይ ከሌብነት ጋር የተዛመዱ ጉዳዮች በክስ ማቋረጥ መብት ሥም ነፃ ማድረግ ሕዝቡ በፍትሕ አካላት ላይ የነበረውን አመኔታ የበለጠ እንዲቀንስና እንዲሸረሸር ማድረጉ አይቀሬ ነው።

በተለይ የወደፊቱ ተረካቢ ወጣቱ ትውልድ ከዚህ ውሳኔ ምን ሊማር ይችላል የሚለው በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳስበን ይገባል። ቀደም ባሉት ጊዜያት በተመደብንበት መሥሪያ ቤት ልምድ ለማግኘት ረዘም ላለ ጊዜ ለማገልገል ፍላጎቱም፣ ጥረቱም ነበር። ብዙዎቹን ባይወክልም አሁን አሁን ትኩረቱ በአንድ መሥሪያ ቤት ልምድ ለማግኘት ሳይሆን ከደመወዝ ውጭ የሚገኝ ጥቅም ማሳደድ ነው። ለመስክ ሥራ የሥራ መሣሪያ (እንደ ላፕ ቶፕ፣ ሌሎችም) ተሰጥቷቸው በዚያው ይዘው የሚጠፉ፣ ለግል ጥቅም ፍለጋ ብዙ መሥሪያ ቤቶችን የሚለዋውጡ (instances of civic neglect) እኩይ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ራስ ወዳድ ግለሰቦች ያሉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በአናቱ ላይ ደግሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሙስና ምክንያት ክስ የመሠረተባቸውን ግለሰቦች ክስ ሲያቋርጥ ምዝበራ ለመፈፀም የተዘጋጁት እንዲደፋፈሩ ከማድረጉ ባሻገር ያላሰቡበትን ወጣቶች ወደዚህ እኩይ ምግባር እንዲሳቡ አያደርግም ማለት የዋህነት ነው።

በተጨማሪ የሕዝብ ሀብት መጠበቅ ወይም ማስተዳደር ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ምዝበራ መፈፀም ምንም ሊያስፈራ እንደማይችል አልፎም ነፃ መሆን እንደሚቻል ስለሚያስቡ በተጠናከረ መንገድ ሌብነት እንዲስፋፋ የሚያደርግ አደገኛ የውሳኔ መስመር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባዋል።

ነገርን ነገር ያነሰዋል፣ ከአንድ ወር ተኩል በፊት የፌደራሉ ዋና ኦዲት መሥሪያ ቤት በዋና ኦዲተር በኩል የፋይናንስ ስርዓትን ሳይከተሉ የተመደበላቸውን ገንዘብ ከሕግ ውጭ ወጪ ያደረጉትን እና ያልተወራረደ በሚሊዮን የሚቆጠር ሒሳብ አለባቸው ያሏቸውን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ዩንቨርሲቲዎች የተመለከተ ሪፖርት ለሕዘብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረባቸው ይታወሳል። እንደ ሃገር አሳፋሪ ሥራ የተከናወነ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ የዩንቨርስቲዎች የበለጠ የሚያስገርም እንዲሆን ያደርገዋል። ከሌሎቹ ለይቶ ለማየት የተፈለገው የትምህርት ተቋማቱ ወጣቱን የኅብረተሰብ ክፍል የያዙ በመሆናቸውና በወጣቶቹ ፊት የሚከናወን ማንኛውም ተግባር ትኩረት እና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው እሙን ነው። መልካም ሥነ ምግባር እንዲሰርፅ መምህራን ሲተጉ በግልባጩ የዩንቨርሲቲዎቹ አመራር ሕገወጥ አሠራር ግን የሚያሳፍርና ለትውልዱ መጥፎ ሐሳብ እንዲያቆጠቁጥ የሚያደርግ ይሆናል፣ እየሆንም ነው። ተቋማዊ በሆነ መንገድ ሲታይ መምህራን እና የትምህርት አስተዳደሩ ከፀረ ምዝበራ ጋር የተዛመዱ ሐሳቦችን እና ሥራዎችን በምን የሞራል መሠረት ነው ለተማሪዎቻቸው የሚያሳውቁት? ነገስ ወጣቶቹ ተመርቀው ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ በሕዝብ ሀብት ማስተዳደር ላይ ምን ዓይነት አቋም ሊይዙ ይችላሉ?

ሌብነት (በዳቦ ሥሙ ሙስና) የአገር ጠንቅ እና የዕድገት ፀርን ከመቀነስ ጀምሮ ማጥፋት ዒላማ ባደረገ መልኩ ለማከናወን ሁሉን ዐቀፍ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚያስፈልገበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምክንያቱም በሁሉም መስክ ዝርፊያ ተካሒዷል፣ እየተካሄደም ነው። ያልተማረውም፣ የተማረው ሁሉ የዝርፊያው ተዋናይ ሆኗል። ሳይሠሩ ማግበስበስ የተለመደ እና ይህም በሽታ በወጣቶች (ፆታ ሳይለይ) ላይ ተጋብቶ ሳይደክሙ ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚገኝበትን መንገድ በመፈለግ እና በማግኘት ምዝበራው በከፍተኛ ደረጃ እና በገሃድ እየተፈጸመ ነው። ከባለሀብቱም መካከል ቢሆንም ከዚህ አስከፊ እና አገር ገዳይ ምዝበራ የራቁ አይደሉም። ታክስ በመሰወር፣ ተፈላጊ ሸቀጥ ‘ለዓየር ባየር’ በማመቻቸት፣ ከደረጃ በታች እና ለጤና ጎጂ የሆኑ እቃዎችን (መድኀኒቶችን፣ የግንባታ ‘ማቴሪያል’፣ ፈሳሽ ነክ የሆኑ፣ በምግብ መልክ ያሉ …) ወደ አገር አስገብቶ በመሸጥ ጀምሮ የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ከአገር የማሽሽ ደባ እየተፈፀመ ያለበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ወደ ውጭ በመላክ ምርጥ ላኪ ተብሎ የተዘመረለት እና የተሸለመ ድርጅት በሳምንቱ (በፎርቹን ጋዜጣ የወጣ) ብር 790.2 ሚሊዮን ብር ታክስ ማጭበርበሩ ተጋልጧል። በዚህ መልክ በአገራችን የሌብነት ድራማው እንደቀጠለ ነው።

ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት ገንዘብ በአመዛኙ ከግብር ከፋዩ፣ ከውጭ ንግድ፣ በውጭ ምንዛሬ የሚገኝ ሐዋላ፣ ከለጋሽ አገራት የሚገኝ ችሮታ እና ከውጭ በብድር የሚሰበሰብ ስለሆነ ሕይወታቸውን ጎዳና ላይ ከሚገፉት ጀምሮ በድኅነት ውስጥ የሚኖረው ዜጋ በሙሉ የሀብቱም፣ የዕዳውም ባለቤት ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ኀላፊነትን ተገን በማድረግ የተገኘው ሀብት ለግል ጥቅም ሲውል በተመዘበረው ልክ ወደ ባሰ ድኅነት የሚወርደው ዜጋ እየጨመረ እንደሚሔድ ብዙ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም። የሕዝቡ ሕይወት ሲዖል ሆኗል፣ ኑሮ ውድነቱ የሚያንገፈግፍ ደረጃ ላይ ደርሷል፣ ሕዝቡ የመከራ ሕይወት እየገፋ ይገኛል። ብዙ ጊዜ የሚያስተዛዝበው ለመዝባሪዎቹ የስብኣዊ መብት ጉዳይ ዐቢይ አጀንዳ ሆኖ ይነሳል፣ ነገር ግን የተመዘበረው የድሃው ኅብረተሰብ መብት ግን ከመድረክ ፍጆታ ውጭ ትኩረት አያገኝም።
ምን ይደረግ?

በጽሁፉ መነሻ ሐሳብ መሠረት የመጀመሪያው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማቋቋሚያ አዋጅ ውስጥ ያለውን አከራካሪ አንቀጽ ፈትሾ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ፣ የሕዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤትም አከራካሪ የሆነውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ውስጥ ያለ አንቀጽ በመመርመር አስፈላጊ የሆነውን ውሳኔ በመስጠት የፀረ ምዝበራ ትግሉን ማገዝ፣ የፌደራል ፀረ ሙስና ተቋምን በቅርበት ክትትል ማድረግ የሚጠበቅበት ተግባር ነው። ወደፊት ሊታሰብበት የሚገባው ምዝበራ የሚፈፅሙ ግለሰቦች የሚዳኙበት ራሱን የቻለ ሕግ የማርቀቅ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ይህንን የአገር ጠንቅ ለመታገል በፀረ ምዝበራ እንቅስቃሴ ውስጥ የአንዱ አካል ተግባር የሌላውን አካል ሥራ የሚያጠናክር መሆን ይገባዋል እንጂ የሚቃረን አሠራር መኖር የለበትም። ከመደጋገፍ ይልቅ ወደ ቅራኔ የሚመራ ከሆነ በዜሮ ድምር ውስጥ እንድንዳክር ያደርገናል፣ የፀረ ምዝበራ ትግሉን ያዳክመዋል። ሌብነትን እንደሥራ የያዙ ግለሰቦች እና ድርጅቶችን ለመታገል የሚቻለው መንግሥት፣ ሲቪል ማኅበረሰብ እና የግሉ ሴክተር ሕዝቡን ማዕከል በማድረግ በጋራ እና በተናጠል በሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግልና መስዋትነት ነው። ለዚህም መንግሥት፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ እና የግሉ ሴክተር ከሕዝቡ ጋር የመከላከል ጥረቶች እና የማዳን ርምጃዎች የመውሰድ ተከታታይ ጥረት ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪ የአገር ሀብት ለዝርፊያ እንዳይጋለጥ መንግሥት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ከተግባራዊ እንቅስቃሴ ጋር ይጠበቅበታል።

በማስረጃ የተደገፈ እና ውጤታማ ሌብነትን የመከላከል ሥራ ለመሥራት መንግሥት ህገ ወጥ ሥራን ለሚያጋልጡ ዜጎች (whistle blowers) የሕግ ከለላ፣ አስተማማኝ ጥበቃ፣ የሥራ ላይ ዋስትና እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲከበር የሚያደርግ ሕግና አሠራር መዘርጋት አለበት፣ ካለም በተግባር እንዲውል መደረግ አለበት። ማንኛውም ሕጋዊም ሆነ ሕገወጥ የሆነ ተግባር ከኅብረተሰቡ ዕይታ ውጭ ስላልሆነ ምዝበራ እና ሌሎች ሕዝብንና አገርን የሚጎዱ ተግባራት ሲፈፀም ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ሲያስታውቁ ተገቢው ጥበቃ ሊደርገላቸው ይገባል። ይህም ሌብነትን የመከላከል ርምጃውን የሚያጠናክርና ሌሎችም በምንቸገረኝነት የማይተውት ጉዳይ ይሆናል።

ከዚሁ ጎን የዲሞክራሲ ተቋም ከሚባሉት አንዱ የሆነውን የፌደራል ፀረ ሙስና ተቋም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በሥልጣን እና በአቅም በማጠናከር እና ከሥራ አስፈፃሚው ጣልቃ ገብነት እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆን ማስቻል ያስፈልጋል። ተቋሙ አሁን ባለው ቁመና አቅም የሌለው እና የሚያሳድረው ተጽዕኖ እዚህ ግባ የማይባል ስለሆነ ውጤት ከፈለግን ጠንካራ ተቋም ሊደረግ ግድ ነው።

ሌብነትን ለመከላከል ማስተማር እና ማሳወቅ መሠረታዊ ግባቶች ናቸው። የሚተላለፈው ትምህርት ፍሬ እንዲይዝ ከተፈለገ ግን ጠንካራ እና የማያወላዳ ርምጃ በመዝባሪዎች ላይ ጎን ለጎን መከናወን አለበት። በተግባር ሌብነት እየጨመረ ባለበት ሁኔታ ትምህርት ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም። ሌላው ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ኹለተኛ ደረጃ የሚሰጠው ትምህርት አርዓያ በሆኑ ብቁ ዜጎች መታገዝ አለበት። ለዚህም በሥራቸው፣ በሥነ ምግባራቸው እና በሥራ ታሪካቸው ምሣሌ የሚሆኑ ብቁ ዜጎችን በማፈላለግ ልምዳቸውን ለተማሪዎች እንዲያካፍሉ ማድረግ ፀረ ምዝበራ ትምህርቱ እንዲጠናከርና ፍሬ እንዲያሳይ ማድረግ ያስችላል። ይህን ትምህርት በማስተላለፍ እና ውጤት እንዲኖረው በማስቻል በኩል የጥበብ ሰዎች እና ሚዲያዎች ኀላፊነት ባለው መልኩ የፀረ ሌብነት ትግሉ እንዲጠናከር በማዝናናት እና በማስተማር ኅብረተሰቡን ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል።

ከትምህርት ቤት፣ ከጥበብ እና ከሚዲያ በተጨማሪ ቤተሰብ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት። ቤተሰብ ለሕፃናት የውጭውን ዓለም ማሳያ መስኮት ሆኖ የሚያገልግል ቀዳሚ ተቋም ነው። የሕፃናትን አዕምሮ በመቅረፅ በኩል ከትምህረተ ቤት፣ ከጥበብ፣ ከሚዲያ፣ ከተቋማት በተጨማሪ ቤተሰብ ሌላው ባለድርሻ ነው። ስለዚህ ልጆችን በመልካም ሥነ ምግባር በመቅረፅ በኩል ቤተሰብ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት መወጣት አለበት።

ካሣዬ አማረ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህር እና ስድስት መጽሐፍትንም ያሳተሙ ሲሆን በኢሜል amarek334@gmail.com አድራሻቸው

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here