አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የዕቅዱን 103 በመቶ ትርፍ አስመዘገበ

0
1197

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2011 የያዘውን የትርፍ ዕቅድ 103 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታወቀ። ባንኩ በ2010 የበጀት ዓመት 480 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘት የቻለ ሲሆን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 670 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ለአዲስ ማለዳ አስታውቆ ዕቅዱ 630 ብር እንደነበርም አክሏል።
የባንኩ የትርፍ ጭማሪ ከሌሎች ባንኮች አንፃር ሲተያይ በቀዳሚነት ሊያስቀምጠው እንደሚችል የዘርፉ ባለሞያዎች ተናግረዋል። በዚህም ረገድ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በማትረፍ ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ በኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ዳሽን ባንክን በትርፍ ዕድገት ፍጥነት እንደሚበልጠው ለማወቅ ተችሏል።

በዚህም መሰረት ዳሽን ባንክ ከቀዳሚው የበጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በዚህ ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ 23 በመቶ ሲሆን አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ 39 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ከባለፈው አመት ትርፉ አንፃር ጭማሪ አሳይቷል። ይህ ደግሞ በትርፍ እድገት 70 በመቶ ካስመዘገበው ከአዋሽ ባንክ እና 57 በመቶ የትርፍ ዕድገት ካስመዘገበው አቢሲኒያ ባንክ በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያደርገዋል።

203 ቅርንጫፎችን በመላው ኢትዮጵያ አካባቢዎች የከፈተው አንበሳ ባንክ በ2027 በኢትዮጵያ መሪ ባንክ ከሚባሉት ዋነኛው እና ቀዳሚው ለመሆን ራዕይ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። በ2 ቢሊዮን ብር ካፒታል እና በ1 ነጥብ18 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የሚንቀሳቀሰው ባንኩ በባለፈው ዓመት የተገኘው ትርፍ ለአክሲዮን ባለድርሻዎች ሲከፋፈል በአንድ አክሲዮን 302 ብር እንደነበር ተገልጿል።

የባንኩን ዕድገትና ሊደርስበት ስላለው ደረጃ በተመለከተ የባንኩ ምክትል ፕሬዘዳንት ዳንኤል ተከስተ ለአዲስ ማለዳ ሲገልፁ፤ እንደ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራበት ያለው ጉዳይ ተደራሽነትን ወደ አርሶ አደሩ እና በገጠራማው አካባቢ ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ዳንኤል ገለፃም ይህ ከሆነ የውጭ አገራት የገንዘብ ተቋማት ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ሥጋት ሊፈጥርበት እንደማይችሉና በኮርፖሬት ደረጃ ግን መወዳደር ተግዳሮቶች እንደሚኖሩበት አስታውቀዋል ።

አንበሳ ባንክ በ2010 ያስመዘገበው 480 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ከታክስ ፣ ኦዲት እንዲሁም ተዛማጅ ጉዳዮች ተቀናሽ በኋላ 393 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቆ ነበር። በተመሳሳይም ባንኩ ለደምበኞቹ ያበደረው የገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን ይህም ታቅዶ ከነበረው የ36 በመቶ ዕድገት እንደነበር የሚታወስ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here