የአርባ ምንጭ ከተማ የአዞ እርባታ 1 ሺሕ 500 አዞዎችን አርዶ ቆዳቸውን ለመሸጥ ዓለም ዐቀፍ ጨረታ በተደጋጋሚ ቢያወጣም ገዢ በባለመገኘቱ እና በመጨረሻም ቆዳውን ለመግዛት የቀረቡት ጣሊያናዊ ግለሰብ ያለተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሸጥ በመጠየቃቸው ሽያጩን ለመፈፀም መታሰቡ ታወቀ። የእርባታው ኀላፊ የሆኑት ወንድሙ አባተ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ቆዳው ለብልሽት እንዳይዳረግ በአዲስ አበባ በሚገኘው ቆዳ ልማት ኢኒስቲትዩት ተልከው እንዲቀመጡ ተደርጎ ነበር።
“ሆኖም ኢንስቲትዩቱ እንዚህን ቆዳዎች እንድናስወጣ እና ለገቢያው እንድናቀርብ ደብዳቤ የተላከልን በመሆኑ ለግብይት የቀረቡ ቆዳዎችን ያለ ጨረታ እንዲሁም ያለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመሸጥ ተገደናል” ብለዋል። ከ100 እስከ 500 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጡት እነዚህ ቆዳዎች የሚዘጋጁት ዕድሚያቸው ከሦስት እስከ ስምንት ዓመት ከሚሆኑ አዞዎች ሲሆኑ እነዚህም ከ25 ሳንቲ ሜትር እስከ 50 ሳንቲ ሜትር የሚሆን የደረት ስፋት ያለቸው ሲሆኑ ነው።
ተቋሙ በውስጡ እስከ 20 ሺሕ የሚሆኑ አዞዎችን የመያዝ አቅም ቢኖረውም በአንድ ግዜ ከ4 ሺሕ የማይበልጡ አዞዎችን ብቻ ያስተዳድራል። ነገር ግን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እየወረደ ባለው የአዞ ቆዳ ገበያ እንዲሁም አዞዎቹን ለመመገብ ከሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ የተነሳ የእርባታው እንቅስቃሴ ዝቅተኛ ሆኗል። በተጨማሪም በኛ በእርባታው ከፍተኛ የሆነ የገቢያ ትስስር መቀዛቀዝ መኖሩንም ወንድሙ ይናገራሉ። ዓለም ዐቀፍ ግብይቱ ከዚህ ቀደም እንደነበረው አትራፊ ቢሆን ከቆዳው ባለፈ የአዞ ሥጋንው ለውጪ ግብይት የማቅረብ አቅምም እንደነበራቸው ወንድሙ ተናግረዋል። አንድ ኪሎ የአዞ ሥጋ 5 ኪሎ ግራም የሚሆነው እስከ 15 ዶላር ድረስ የሚሸጥ ሲሆን በኬኒያ እና በቻይና ሰፊ ገበያ ነበሩ።
በአሁኑ ወቅት አዞ እርባተው 2 ሺሕ 600 አዞዎች ሲኖሩት ከእነዚህም 1 ሺሕ የሚሆኑት ቆዳቸውም ለውጪ ገቢያ እንዲውል ብቁ ናቸው። የተቀሩት አዞዎች በቅርቡ ለግብይት እንደሚደርሱ ተናግረዋል። ለእነዚህም ጫጩት አዞዎች የሚዘጋጀው ምግብ አሣ እና ሥጋ ሲሆን ይህንንም ለማቅረብ በዓመት 5 መቶ ሺሕ ብር ወጪ እንደሚሆን ኀላፊው ጨምረው ተናግረዋል። እርባው በዓመት አጠቃላይ ገቢው በአማካኝ እስከ 8 መቶ ሺሕ ብር ሲሆን ከፍተኛ የሚባለው ወጪም የምግብ እንደሆነ ኀላፊው አስታውቀዋል።
አንድ አዞ በወቅቱ ካልታረደ እና ከ 8 ዓመት ግዜ ካለፈ ቆዳቸው የሚጠነክር ሲሆን የደረታቸውም ስፋት ከዚህ የሚያልፍ ከሆነ ጥቅም ላይ አይውልም።
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ አራት ዓይነት የአዞ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን በኦዞ እርባተው ውስጥ የሚገኘው እና ተመራጭ የሆነው ናይል ኮሮኮዳይ ነው። ይህ አዞ ከሌሎቹ በተለየ ተፈላጊ የሆነ ዝርያ ሲሆን በዓለም ዐቀፍ የቆዳ ጥራት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የአዞ ዓይነት ነው።
በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኘው እንዲሁም በአገሪቱ ብቸኛ የሆነው የአዞ እርባታ ከ2005 ጀምሮ ዓለም ደረጃ የገበያ ትስስሩ እየቀዘቀዘ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት በተቋሙ በዓመት ከ3 ሺሕ እስከ 4 ሺሕ የሚሆኑ ጫጩቶች የሚገቡ ሲሆን በመጪው 2012 አራት 4 ሺሕ አዞዎችን ለማስገባት ዝግጀቱን አጠናቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011



