የእግር ኳስ ተጫዋቾች ክፍያ ጣራ በመዘጋጀት ላይ ነው

0
663

በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የእግር ኳስ ቡድኖች ውስጥ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ወርሃዊ ደሞዝን እንዲሁም ዝውውርን በሚመለከት የክፍያ ጣራ ለማበጀት እየተሠራ እንደሆነ ታወቀ። የክፍያ ጣሪያው በእግር ኳስ ቡድኖች ዘንድ ያለውን የተጋነነ እና ወጥነት የሌለውን የክፍያ ምጣኔ ለመቆጣጠር ታስቦ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ፌደሬሽኑ እንዳስታወቀው ለተጫዋቾች የሚከፈለው የደሞዝ መጠን “አንድ ዓይነት” ባለመሆኑ እንዲሁም ምንም ዓይነት ገደብ ባለመኖሩ የእግር ኳስ ቡድኖች ተጫዋቾቻቸውን ለመክፈል አቅም እያነሳቸው እንደሆነ ገልጿል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ለማካሔድ የሚቸገሩባቸው አጋጣሚዎች ቀላል የማይባሉ ጊዜያት እንደሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ባሕሩ ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለተጫዋቾች የክፍያ ጣራን በሚመለከትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየመከረ ሲሆን፤ በቅርቡም ውይይቱ ተጠናቆ ውሳኔ ላይ እንደሚደረስ ባሕሩ ጨምረው አስታውቀዋል። ከዛ በፊት ግን በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የእግር ኳስ ቡድኖች ያሳተፈ ውይይት እንደሚካሔድም አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

አዲስ ማለዳ ከፌደሬሽኑ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑት የእግር ኳስ ቡድኖች ውስጥ ለአንድ ተጫዋች ዝቅ ሲል 25 ሺሕ ከፍ ሲል ደግሞ 280 ሺሕ ብር ወርሃዊ ደሞዝ የሚከፍሉ ቡድኖች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል። ለዚህም ደግሞ መላ የማይበጅለት ከሆነ ወደ ፊት ገንዘብ ያላቸው ጥቂት የእግር ኳስ ቡድኖች ብቻ ሊቀሩ እንደሚችሉ እና የእግር ኳሱ ኢንዱስትሪም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ብሎም እስከ መክሰም እንደሚያደርስ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ተናግረዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣው የተጫዋቾች ክፍያ በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ከፍተኛ ወጪ ለተጫዋቾቻቸው ከሚከፍሉ ሦስት አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ እንድትካተት እንዳደረጋት ተገልጿል። በአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ በመቀጠል በአገር ውስጥ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ኢትዮጵያ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ከተጫዋቾች ወርኀዊ ደሞዝ ባሻገርም የተጫዋቾችን ከአንዱ ቡድን ወደ ሌላው ቡድን የሚደረገውን ዝውውርም ፌደሬሽኑ ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየመከረበት እንደሚገኝ እና እሱም ገደብ ሊጣልበት እንደሚችልም ታውቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ውሳኔዎችን እያሳለፈ ሲሆን በቅርቡም መጠሪያቸው ብሔር ተኮር የሆኑ የእግር ኳስ ቡድኖች ስያሜያቸውን እንዲያስተካክሉ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አስታውቆ በቀጣዩ ዓመት በፕሪምየር ሊግ ጭዋታዎች ላይ ፀብ እና ብጥብጥ ከተፈጠረ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጨዋታዎች በዝግ ስታዲየም እንዲካሔዱ እንደሚያደርግም አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here