የሲዳማ ፓርቲዎች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጡት ቀነ ገደብ ነገ ይጠናቀቃል

0
710
  • ፓርቲዎቹ ለሚፈጠረው ችግር ምርጫ ቦርድና የክልሉ መንግሥት ኀላፊነቱን ይወስዳሉ ብለዋል

ሦስት የሲዳማ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን አስመልክቶ ሕዝበ ውሳኔው የሚካሔድበትን ቀን ቆርጦ እስከ ነገ እሁድ ሐምሌ 7 ድረስ እንዲያሳውቅ ቀነ ገደብ ሰጥተዋል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ እንዲያስፈጽም የጠየቁት ፓርቲዎቹ የተጠየቀው ሳይፈጸም ቢቀር ለሚፈጠረው ማንኛውም ችግር የክልሉ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ ኀላፊነቱን ይወስዳሉ ብለዋል።

ፓርቲዎቹ በሰጡት መግለጫ ላይ የሲዳማ ሕዝብ በተደጋጋሚ ሲያቀርበው የነበረውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ፣ ራሳቸውን ባገዘፉ አምባገነን ኀይሎች ሲታፈን ቆይቷል ብለዋል። የሕዝቡ ጥያቄ መብት እንጂ ልመና አይደለም ያለው መግለጫው፣ ምላሹ መሰጥት ያለበት በፖለቲካ ስሌት እና በምሁራን ጥናት ሳይሆን፣ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ነው ሲሉም አሳስበዋል።

ቦርዱ ባሳለፍነው ማክሰኞ ከምሁራን ጋር አድርጎት በነበረው ውይይት እንዲሳተፉ ያቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ ያደረጉት ፓርቲዎቹ ጥያቄው በሕገ መንግሥቱ መሰረት እንጂ በምሁራን ውይይት ሊፈታ አይችልም ሲሉም ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ላለፉት በርካታ ዓመታት ሕዝቡ በክልል የመደራጀት መብቱን ሲጠይቅ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ (ሲአን) የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ደሳለኝ ኔንሳ፣ የሲዳማ ሕዝብ ባለፉት 12 ወራት ሕጋዊ መንገዱን ጠብቆ ሕገ መንግሥታዊ መስመሩን ተከትሎ ቢሔድም፣ ከመንግሥት አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ ተደጋጋሚ ጫና ለማድረግ ተገዷል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 24/2011 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ባቀረቡት የዓመቱ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ፣ ለቀረበላቸው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በክልል ለመደራጀት ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች የምርጫ ቦርድና ሌሎች አስፈፃሚ ተቋማት እስኪደራጁ በትዕግስት ይጠብቁ ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የካቲት 8/2011 የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሚሊዮን ማቴዎስ፣ በሐዋሳ ከተማ በተካሔደው የኦሮሞና የሲዳማ ልኂቃን የምክክር መድረክ ላይ የሲዳማ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የሚያስችለውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር “የሲዳማ ሕዝብ በዚህች አገር ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ባደረገው አስተዋጽዖ ልክ ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት አለው። የኹለቱን ሕዝቦች ልኂቃንን ያገናኘው የዛሬው መድረክ፣ የሲዳማ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት መካሔዱ ልዩ ያደርገዋል” ሲሉም ገልጸው ነበር።

ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ ከምሁራን ጋር ሐዋሳን አስመልክቶ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አክቲቪስት ስዩም ተሾመ፣ ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የኦሮሞና የክልሉ ልኂቃኖች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፣ እነዚህን አካላት መንግሥት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here