በአሶሳ ዙሪያ ወረዳዎች የእንስሳት ወረርሽኝ ተከሰተ

0
829

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ወረዳ በተከሰተ የእንስሳት በሽታ ምክንያት ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ በአራት ቀናት የተለያዩ የቀንድ ከብቶችን መግደሉን የክልሉ የፓርክ እና የዱር እንስሳት ባለሥልጣን አስታወቀ። አምባ 11 ቀበሌ የተከሰተው የአስታገር የእንስሳት በሽታ የቀንድ ከብቶችን አፍ በማቁሰል መመገብ እንዳይቸሉ በመከልከል 32 የእርሻ በሬዎች እንዲሁም የወተት ላሞች እና ጥጃዎች መሞታቸው ታውቋል።

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሳሙኤል አድማሱ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የአስታገር በሽታ ከዚህ ቀደም በክረምት ወራት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚጋጥም ቢሆንም እንስሳቶችን እስከመግደል ደረጃ የሚያደርስ አልነበረም።በአሁኑ ወቅት በከብቶቹ ላይ የሚያሳው ምልክትም ሆነ ተጽዕኖ ከፍተኛ ቢሆንም እስከአሁን ወደ ሰው ያልተላለፈ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

አርሶ አደሮችም የመኸር እርሻ ዝግጅት ላይ በመሆናቸው የእርሻ በሬዎችን ለግብርና ሥራዎች የሚጠቀሙበት ወቅት በመሆኑ በመንግሥት በኩል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከብቶቹ የሚመገቡት ሣር ነገሮችን በመሆኑ ለዚህ አስከፊ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ በመሆኑ ፈጣን እርምጃ ሊወሰድ ይገባልም ብለዋል።

የበሽታውን ስርጭት ለመቆታጠር እና የታመሙትንም ከሞት ለመከላከል በባሕላዊ መልኩ ኅብረተሰቡ ክትትል እያደረገ ሲሆን በበሽታው የተጠቁ እንስሳትንም በቤት ውስጥ በማቆየትና ሙቅ እና መሰል ምግቦችን መመገብ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው። የሽታው መነሻ እስኪረጋገጥ ድረስ ምልክቱ የታየባቸውን ከጤነኞቹ ከመለየትም ባለፈ በበሽታው የሞቱትን በመቅበር የበሽታውን ሥርጭት ሊያቆሙ እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

በአሶሳ ከተማ የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪ ባለሙያዎች በቀበሌው ተገኝተው ባደረጉት አሰሳ የአሰታገር በሽታ ሰባት ዓይነት እንደሆነ የበሽታውን ዝርያ በመለየት ክትባት ለመስጠት ተጨማሪ ናሙና የማሰባሰብና ሥራ እየተካሔደ መሆኑን አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት ውጤቱ ሲታወቅ ለፌደራል መንግሥት እንደሚላክ እና ቀድመው በማሳወቃቸውም ዝግጀት እየተደረገ እንደሆነ ሳሙኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፈው የአስታገር በሽታ ከቀንድ ከብቶች በተጨማሪ በጎች እና ፍየሎችን የሚያጠቃ ሲሆን በሽታው በተከሰተበት በ11 ኪሎ ሜትር ዙሪያ የመስፋፋት አቅም ያለው በመሆኑ በአጎራባች አምባ 10 እና በሌሎች ቀበሌዎች መታየቱንም ገልጸዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2010 በተደረገ ቆጠራ መሰረት 9 መቶ ሺሕ የሚጠጉ የቀንድ ከብቶች መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክተሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here