የቀረጥ ነፃ አዋጁ ሲፀድቅ በዓመት 20 ቢሊዮን ብር ያድናል ተባለ

0
398

እየተረቀቀ ያለው አዲስ የቀረጥ ነፃ አዋጅ ሲጸድቅ መንግሥት በየዓመቱ ይሰጥ ከነበረው የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ 20 ቢሊዮን ብር ለማዳን ማሰቡን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። በረቂቁ በ35 የመንግሥት አካላት ሲሰጥ የነበረውን የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ወደ አራት ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር ሲታዩ የነበሩ ክፍተቶችን በጥናት ለይቶ ለመለወጥ ማሰቡን ለማወቅ ተችሏል።

በጥናቱም ላይ ዘላቂ እና ጤናማ የንግድ ዕቅድ ይዘው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የውጪ ባለሀብቶች እንዲሁም የአገር ውስጥ አልሚዎች ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻዎች ይልቅ የገበያ ፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ይበልጥ እንደሚመሰረቱ ያትታል። ጥናቱ አክሎም በተለያዩ የመንግሥት አካላት ሲሰጥ የነበረው የቀረጥ ነፃ መብት በተለያየ መልኩ ለእኩይ ዓላማ ሲመዘበር እንደነበረ እና ይህም ቀላል የማይባል ጉዳት ማስከተሉን አረጋግጧል።

የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሃጂ ኢብሳ እንደሚሉት አዋጁ እንደ እስከዛሬው በማበረታቸው አፈፃፀም ላይ ብቻ ሳይሆን የክትትል ስርዓቶችንም ያካተተ እና ጥልቅ ዕይታዎች ያሉት ነው። የቀረጥ ነፃ መብቶቹ ከተሰጡ በኋላ ለተባለላቸው ዓላማ መዋላቸውን ወይም አለመዋቸውን ለመከታተል የሚያግዝ ስርዓትም ይዘረጋል ብለዋል። አክለውም እስከዛሬ በተናጠል ሲሰጥ የነበረው ይህ መብት አዋጁ ያዋቅረዋል በተባለው ሦስቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ኮሚሽኑ በሚሳተፉበት ስብስብ በጋራ የሚወሰን እንደመሆን ይጠበቃል ብለዋል።

“በተገባደደው የበጀት ዓመት የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጋራ የቀረጥ ነፃ መብት ጥያቄዎች ሲያስተናግዱ የነበረ ሲሆን አዋጁም ይህንን የሚደግፍ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን ገና የመጨረሻ ደረጃ ላይ ያልደረሰ ስለሆነ ብዙ የሚለወጡ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ ሃጂ አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ለአካል ጉዳተኛ ዜጎች ተዘጋጅቶ የነበረውን የተሸከርካሪ ወንበር ከቀረጥ ነጻ መብት ባለሀብቶች በእጅ አዙር በመጠቀም የደረሰውን ኪሳራ የሚያስታውሱት ሃጂ፥ ከምንም በላይ መብቶቹ ለሚሰጡበት ዓላማ መዋላቸው ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ይፋ ባደረገው ጥናት፥ የቀረጥ ነፃ ማበረታቻዎች ሥር የሰደደ ችግር እንዳለባቸው እና ለካፒታል ሥራዎች ተብለው የሚገቡ እቃዎችን ወደ ገበያ በማውጣት በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ እየደረሰ ካለው ችግር በተጨማሪ ፍትሐዊ የሆነውን የገበያ ፉክክር የሚረብሽ ነው ማለቱም ይታወሳል። የአፈጻጸም ክትትል ማነስ እንዲሁም ዝቅተኛ የሆነ የመዝገብ አያያዝ ስርዓት ጥናቱ ከለያቸው ችግሮች መካከል ሲሆኑ ኮሚሽኑ የሕግ ክፍተቶችን በመጠቀም መንግሥት ማግኘት ካለበት ገቢ ከፍተኛ መጠን ያለውን ገቢ እንደሚያጣም አትቶ ነበር።

በተለይ የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ችግሮችና አሻጥሮች በግንባር ቀደምትነት በማዕድንና በግንባታ ዘርፎች መሆናቸው ቀደም ሲል ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here