ሰኔ 15/2011 በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተካሔደውን “መፈንቅለ መንግሥት” ተከትሎ በባሕር ዳርና በአዲስ አበባ የከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሌሎች በውል ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎችን ክቡር ሕይወት መንጠቁ ይታወሳል።
ይህንን ድርጊት ተከትሎም መንግሥት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በይፋ አስታውቋል። ከታሳሪዎቹ መካከል የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት፣ የመብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ነጋዴዎችና ፖሊሶች ይገኙበታል። እስሩ የመገናኛ ብዙኀንን ትኩረት ከመሳቡም ሌላ ዓለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የውግዘት መግለጫ እንዲያወጡ አስደርጓል። ለአብነትም መቀመጫውን ሲውዘርላንድ ያደረገው ዓለም ዐቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች መግለጫ አውጥተዋል።
ማንኛውም በወንጀል ድርጊት ፈጻሚነት የተጠረጠረ ግለሰብም ሕግ በሚፈቅደው መሰረት መያዝና ፍርድ ቤት ቀርቦ መዳኘት እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች። ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ሪፖርት ባቀረቡበትና ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ከእንግዲህ ወዲህ “በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ይሁን ማን፥ አስቀድሞ ማጣራት ሳይደረግና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይወጣ፣ አንድም ሰው እንዲታሰር አንፈቅድም” ሲሉ የመንግሥታቸውን የሰብኣዊ መብት አያያዝ ቁርጠኝነት መግለፃቸው ይታወሳል። ይህም በኅብረተሰቡም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ዙሪያ ከሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች ግርማ ሞገስና አድናቆት አትረፎላቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሰብኣዊ መብት አያያዝ ላይ በዓለምቀፍ ደረጃ የነበራትን የተበላሸ ገጽታ ያደሰ ሲሆን፣የመንግሥትንም ቅቡልነት በማጎልበት ረገድ የራሱን በጎ አስተዋፅዖ አድርጎ አልፏል።
ከ“መፈንቅለ መንግሥት” ድርጊት ጋር በተያያዘ የተጀመረው ጅምላ እስራት ግን ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በገቡትና በሕግ በተደነገገ መብት መሰረት ለመካሔዱ ብዙ አጠራጣሪ ጉዳዮች መኖራቸውን መታዘብ ይቻላል። አንዳንድ ተጠርጣሪዎች በሚያዙበት ጊዜ የፍርድ ቤት ትዕዛዝም ሆነ ለመያዛቸው የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት በግልጽ ሳይነገራቸው ፖሊስ ጣቢያ ትፈለጋላችሁ ተብለው ሔደው በዛው መታሰራቸው እንዲሁም ፍርድ ቤት መቅረብ በሚገባቸው ጊዜ አለመቅረባቸውም ታውቋል።
ይሔ ግልጽ የመሰረታዊ መብቶች ጥሰት መሆኑን አዲስ ማለዳ ማስታወስ ትፈልጋለች። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሦስት ካስቀመጣቸው መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሥር በቀዳሚነት የተቀመጡት ሰብኣዊ መብቶች ናቸው። በሕገ መንግሥቱ ከተዘረዘሩት ሰብኣዊ መብቶች መካከል ደግሞ የተያዙ ሰዎች መብቶች በአንቀጽ 19 ላይ ሰፍሯል። ወንጀል ፈጽመዋል በመባል የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲነገራቸው መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። በተጨማሪም የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው። ወዲያውኑም ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ስለመሆኑ ተለይቶ እንዲገለጽላቸው መብት አላቸው ሲልም ደንግጓል።
ሌለው ከተጠርጣሪ እስረኞች ጋር በተያያዘ የሚነሳው ቅሬታ የእስር ቤት አያያዛቸውን በተመለከተ ነው። አዲስ ማለዳ የእስረኛ ቤተሰቦችን በማነጋገር እንዲሁም አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ለፍርድ ቤት ስለእስር ቤት አያያዛቸው ከገለጹት ለመረዳት እንደቻለችው፥ የአንዳንድ ተጠርጣሪዎች አያያዝ በሕጉ በተደነገገው መሰረት ሰብኣዊ ክብራቸውን በጠበቀ ሁኔታ የመያዝ መብት አላቸው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መብት የጣሰ መሆኑን ተረድታለች።
ተጠርጣሪዎች በቀዝቃዛ፣ በቂ አየር በማይዘዋወርበት ጠባብ እንዲሁም ንጽሕናው በተጓደለ ክፍል ውስጥ መታሰራቸውን ቅሬታ ከመቅረቡም ባሻገር በቀን ኹለት ጊዜ ለአጭር ጊዜ ብቻ የፀሐይ ብርሃን እንደሚያገኙና መጸዳዳት እንደሚፈቀድላቸው ቅሬታ ቀርቧል። መንግሥት በይፋ ተዘግቶ ሚውዚየም ለማድረግ በዕቅድ ላይ መሆኑ የተነገረለት በተለምዶ “ማዕከላዊ” እስር ቤት ተመልሶ መጣ እንዴ? ያስብላል። ይህም ከሰብአዊ ድንጋጌ ውጪ በመሆኑ አዲስ ማለዳ አጥብቃ ትቃወማለች።
በተጨማሪም ሕጉ በሚያዘው መሰረት ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብትን በተመለከተ እየተከበረላቸው እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ የተጠርጣሪ እስረኞች ቤተሰቦችና ጠበቃዎች በማናገር ለማወቅ ችላለች። ይህም በምንም መልኩ ከሰብኣዊ ድንጋጌ አንጻር ተቀባይነት ያለው አይደለም።
ስለሆነም ሕግን ለማስከበር የሚሠራ መንግሥት በመጀመሪያ ራሱ ሕጉን ማክበር እንዳለበት ግልጽ ነው። በርግጥ አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ አቋሟን ባንጸባረቀችባቸው ርዕሰ አንቀፆቿ መንግሥት የሕግ ልዕልናን ለማስከበር ያሳየውን ዳተኝነት መተቸቷ ይታወሳል። ለትችቶቹ መነሻ የነበሩት ምክንያቶች ስርዓት አልበኝነት፣ የደቦ ፍርዶች፣ መፈናቀሎች እና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መስፋፋታቸው ነበር። ይሁንና ሕግን ለማስከበር ሕግን መጣስና የሰብኣዊ መብቶችን በመደፍጠጥ መሆን የለበትም። ሕግ ማስከበር ሕግን ከማክበር ይጀምራል የምትለው አዲስ ማለዳ፥ መንግሥት በተለይ በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በጅምላ በተያዙ ተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ አጥብቃ ትጠይቃለች። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ትታወቅበት የነበረው ከሕግ ውጪ ሰዎችን ማሰርና ሰብኣዊነት የጎደለው የእስር ቤት አያያዝ ዳግም ተግባራዊ መደረግ የለበትም። አዲስ ማለዳ አሁንም በድጋሜ የእስረኞች ሰብኣዊ መብት ይጠበቅ ስትል በአጽንዖት ታሳስባለች።
ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011


