ቅን መንግሥት ያስፈልገናል! “ግርግር ለሌባ ይመቻል?!” እንዳይሆንብን

0
586

ኢትዮጵያ በሕግ የሚመራና ተጠያቂነት ያለው ቅን መንግሥት እንዲኖራት ያስፈልጋል የሚሉት መላኩ አዳል መሥራት ይገባል ያሉትንም ምክረ ሐሳብ ፈንጥቀዋል።

 

ሰው እጅግ ራስ ወዳድ ነው፤ እናም ከራሱ በላይ የሚያስቀድመው ማንም የለም። አንዳንዴ ከራሱ በላይ ሌላን ያስቀደመ የሚመስለን ጊዜ አለ። ለእኔ እነዚህ ሒደቶች በደንብ ከመረመርናቸው እንዲያውም የራስ ወዳድነቱ ድንቅ ማሳያዎች ናቸው። ለምሳሌ፣ አባትና እናት ትዳራቸው ባይጥማቸውም ለልጆች ሲባል በትዳሩ ይቀጥላሉ። የልጆች ጉዳይ ከእነሱ የበለጠው በዚህ ውስብስብ ዓለም ያለወላጅ ለመኖር አቅማቸው በቂ ስላልሆነና የልጆች አለመቀጠል የወላጆቹ አለመቀጠል ስለሆነ ነው። የልጆች በወላጆች መወደድና ለእነሱ ሲባል ችግሮችን መጋፈጥ ራስን ከመውደድ ይመነጫል። ከውስጡ ራስ ወዳድነት አለበት። እራስን በዚህ ዓለም የማስቀጠል ፍላጎት።

ሌላው፣ በየሃይማኖቱ የበቁ ሰዎች አሉ። ለእምነታቸው ሟች፣ ለሰው በጎ አድራጊ። እነሱም ቢሆን የድርጊታቸው ዋናው ምክንያት ራስ ወዳድነት ነው፤ ገነትን መውረስና ዘላለማዊ ሕይወት መኖር።

የራስ ወዳድነት ውጤት ከላይ እንደተባለው አዎንታዊ ሲሆን ደግ ነው። “አሉታዊ ሲሆንስ?” አሉታዊ ሲሆን የደካሞች በጠንካሮች መበላትን ያስከትላል። ለዚህም ነው መንግሥት የሚባል ተቋም ያስፈለገው፤ ደካሞችን ለመጠበቅ። መሰረታዊ የመንግሥት ተግባራትም 1) ሕግና ስርዓትን ማክበርና ማስከበር፤ ብሎም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ 2) የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ፣ 3) ዜጎች አገራቸውን “አገራችን” ብለው ይጠሩ ዘንድ የዜግነት ስሜትን እንዲፈጥሩና እንዲያዳብሩ ማድረግ፣ 4) መሰረተ ልማትን ማስፋፋትና አገራዊ ሀብትን በፍትሐዊነትና በእኩልነት ተመስርቶ ለዜጎች እንዲደርስ የማድረግ ተግባርን መከወን ናቸው።

ይህን ለማድረግ ግን መንግሥት ሙሉ ጉልበቱን መጠቀም ይኖርበታል። መንግሥት ጉልበት የሚኖረው ደግሞ ከብዙኀኑ ቅብልነቱን ሲያረጋግጥ ነው። ቅቡልነት የሚረጋገጠው ደግሞ ብዙኀኑ የሚስማማበት ሕግጋትን በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ነው። አሁን ምኑንም እየፈጸመ አይደለም። ስለዚህም ሕዝቡ መንግሥት አለ ብሎ ከማምን ደረጃ እየወጣ ነው።

የሥልጣኔ መገለጫዎች ቅድስና (ሃይማኖት)፣ ደግነት (ሥነ ምግባርና ሞራል)፣ እውነት (አመክንዮ፣ እውቀትና ክህሎት)፣ ውበት (ሥነ-ጥበብ)፣ ጠቃሚነት (ምጣኔ ሀብትና ተጠቃሚነት)፣ እና የእነሱም ዕድገት ናቸው። የሥልጣኔ ጸሮችና ለአገር ሰላም መጥፋት መንስኤዎች ደግሞ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ ሌባ ፖለቲከኞች፣ የማይጠግቡ ባለሀብቶች፣ ብልሹ የፍትሕና የደኅንነት አካላት፣ ደካማ የትምህርት ሥርዓት፣ እውቀቱና ተጠያቂነቱ የሌለው መገናኛ ብዙኀን፣ የሥነ ምግባርና የሞራል እሴት መጥፋት፣ የውጭ መንግሥታትና ባለሀብቶች ጣልቃገብነት፣ የውሸት ሐሳብ አቅራቢ ልኂቃን፣ የእኛ ድንቁርና እና ድኅነታችን ናቸው። ድኅረ ዘመናዊነት (Post-modernism/constructionism) የሚባል ሐሳብ፣ ሁሉም አንጻራዊ ነው በማለት የጋራ እውነት፣ የጋራ ሥነ ምግባርና የጋራ ሞራል እንኳን እንዳይኖረን እያደረገ ነው፤ የዘውጌ ፖለቲካም ይህ ችግር አለበት። ለዛም ነው፣ ሁላችንም በየቅርጫታችን ሊከቱን የሚጣደፉት። አሳቢነት ተፈጥሮንና ሰውን ከማወቅ ይጀምራል።

ለዚህ ደግሞ የስነ ሰብዕ (humanities) ትምህርቶች፦ ታሪክ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ፍልስፍና፣ የማኅበረሰብ ጥናት፣ ሥነ ልቦናና ተዛማጅ ትምህርቶች በበቂ መሰጠት አለባቸው። ይህን ስናደርግ የትምህርት ስርዓታችን አገር በቀል እውቀቶችን እንዲያጠቃልልና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሆን የታሰበበት ሆኖ እንዲዘጋጅ ማድረግ አለብን። ይህም ከመንጋነት የወጣ አሳቢ ትውልድ ለመፍጠር ይጠቅማል። ለጥሩ ባሕል መወለድም ጥሩው መንገድ ነው። ይህም ዘላቂ ለሆነ፣ ከዘውጌነት ለወጣ አንድ የምጣኔ ሀብት፣ ማኅበራዊና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያበቃል።

ኢትዮጵያ የተቃኘችው እንደማነኛውም የምናየው ታላቅ አገር ከላይ ወደ ታች ተዋረዳዊ (vertical hierarchical) የአስተዳደር ስርዓት እንጂ ለቤተሰብ እና ካለፈ ለሰፈር በሚሆን እኩልነት (egalitrean) መንገድ አይደለም። እናም በኹለተኛው መንገድ ያተረፍነው የጎጥ ሽፍታዎችን፣ መፈናቀልንና ሞትን ነው። ሰላማችንና አንድነታችን ዘላቂ የምናደርገው በሠራዊታችንና በደኅንነታችን ጥንካሬ፣ ባለን ሀብትና በጋራ ሰንደቃችን አይደለም፤ በጋራ ትርክትና ርዕዮት እንጂ። የጋራ ትርክትና ርዕዮት ከምንም በላይ ኀያል ነው። ማንም ሊያስቆመውና ምንም ጠላት ሊያሸንፈው አይቻለውም። ለዚህም የጋራ ትርክትና ርዕዮት የማሰብ፣ የማመንጨትና የመተግበር አቅምና ቅንነቱ ያላቸው የፖለቲካ መሪዎች ያስፈልጉናል። የጋራ ትርክትና ርዕዮት የሌለው አገር ደኅንነትና ህልውና የተጠበቀ አይደለም።

የዘውግ ወይም የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ግን የጋራ ትርክትንና ርዕዮትን የሚያጠፋ የዘረኝነት ዋናው መገለጫ ነው። የኢትዮጵያም ፖለቲካ የሚያጠነጥነው በዚሁ ላይ ነው። እንዲያውም ከዘውጌ ፓርቲዎች መብዛት አንጻር፣ በጣም አክራሪ ዘውጌ መሆን ተወዳዳሪነትን ይጨምራል። ዋናው ችግራችንም ዘረኝነትን የመንግሥት መዋቅራችንና የአስተዳደር ስርዓታችን ማድረጋችን ነው። ይህም የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን የክልል መንግሥታትና የፌዴራል መንግሥትን ግንኙነት ያለአድሎ የማስተካከል፣ ስርዓት በያዘ መልኩ ያልተከናወነው የአገራዊ መግባባት፣ የተጠያቂነት እና የእርቅ ጉዳይ አለመከናወን እና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩን ትቶ ለዘሩ ብቻ የሚሠራ ተረኛና ዘረኛ እንዲሆን አድርጎታል። በቅርቡ የተፈጸመው የባለሥልጣናትና የጦር መኮንኖች ግድያም በመንግሥት ደረጃ ያለው የዘረኝነቱ መገለጫ ነው። ከአገራችን ክስተቶች ምን ተማርክ ብትሉኝ፣ አንድ ርዕዮት አዎንታዊና አሉታዊ ጎኑ በደንብ ተጠንቶ ወደ ሕዝብ ካልወረደ፣ ሰውን ወደ እንሰሳነት የመቀየር አቅም እንዳለው ነው።

ኦሮሞው፣ አማራውና ትግሬው በቀደመው ትናንት ያልነበሩ፣ ከትናንት እስከ ዛሬ ሌሎችንም ውጠው ያደጉ ማኅበራዊ ስሪቶች (social constructs) ናቸው።

በተጨማሪም ኦሮማራና የኩሽ ኅብረት እያልን ለምንፈልገው ሁሉን አቃፊ አንድነትና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምሥረታ እንቅፋት በሆነ ተጨማሪ የዘር ፖለቲካ መሰማራቱ እዚህ ላይ ሊገታ ይገባል። ኦነግንም፣ ሕወሓትንም፣ አብንንም የሚደግፍም ሆነ የሚጠላ ሁሉ መረዳት ያለበት፣ ሁሉም ድርጅቶች የተዋቀሩባት ሐሳብ ዘረኝነት መሆኑን ነው። ስለዚህም የራስን ቤት ማጽዳቱ ይቅደም። ልኂቃንና ፖለቲከኞች ግን የመሪነት ኀላፊነታቸውን መወጣት ትተው፣ ሕዝብን እያወናበዱ ብሔራቸውን የመደበቂያ ዋሻ አድርገውታል። ስለዚህም ለሚታየው አዎንታዊም አሉታዊው ውጤት ተጠያቂዎቹ እነዚሁ አካላት ናቸውና በሕዝብ ውስጥ መመሸጋቸውን ያቁሙ፣ ከቻሉም በአዎንታዊ መንገድ ሕዝብን ይምሩ።

የዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥትም መሠረቱ ይኸው ጠባብ ብሔርተኝነት ነው። ይህም ከሕገ መንግሥቱና ከፌደሬሽኑ አወቃቀር ጋር ተዳምሮ ዋናው የችግራችን ምንጭ ሆኗል። እናም ከዚህ ችግራችን እንደ አገር እንዴት እንውጣ፣ ምን ዓይነት ርዕዮት ያስፈልገናል፣ ምን ምን ተቋማት ያስፈልጉናል፣ ችግሮቻችን ምንድን ናቸው፣ የሕዝብ መንግሥት እንዴት ይመስረት፣ ሕገ መንግሥቱን እንዴት ይሻሻል፣ ፌዴሬሽኑ18 እንዴት ይስተካከል፣ በአጠቃላይ ምን ዓይነት የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገናል በሚለው ላይ መስማማት ይጠይቃል። የዘር ፓርቲዎችን መመስረት የሚያግድ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያም ያስፈልገናል። ተጨቁነን፣ ባሕልና ቋንቋ ተጭኖብን ነበር የሚሉና ብሶታችን ድሮ ተደረግብን የሚሉትን ሌሎች ላይ ሊያደርጉ የሚፍጨረጨሩ፣ የሕዝብ ጨቋኝ እንደሌለ ሊገነዘቡ ይገባል። ያለዚያ የጎለበተ በሚመስለን ላይ ሂስ መሠንዘሩና የጉልበት አፈና መተግበሩ ብቻ አይበቃም፤ እንዲያውም ቀጣይ ችግር ያስከትላል። ክልል ላይ “መፈንቅለ መንግሥት” ነበር ማለት፣ የአዴፓ መሪዎች ግድያ፣ አዲስ አበባ ላይ የጦር መኮነኖች ሞት፣ ጠንካራ ናቸው የተባሉ ሁሉ የአማራ ልጆች መገደልና መታሰር ምን ይነግረን ይሆን?

ተቋማት በሌሉበት አገር የሚመራ መሪ ተቋምም ነው። አቅም ካለው፣ የሕግ መሰናክል ስለማይኖርበት የበለጠ ሲያከናውን፣ ሙት ከሆነ ግን አገርን አደጋ ላይ ይጥላል። ስለዚህም በሕግ የሚመራና ተጠያቂ መንግሥት አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ በየትኛው እየተመራች ይሆን? በመጀመሪያ የሕወሓት ተገፍቶ መውጣት፣ የአዴፓ መውጣት በር ላይ መድረስ፣ ቀጥሎ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ዳራ በብዙ የሚቀይረው ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቻሉ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን ችግር ፈትተው አገርን በትክክል ይምሩ፤ በብዙኀኑ ውስጥ ቅቡልነታቸው እንዲመለስ ከፈለጉ፣ ሕገ መንግሥቱን ያሻሽሉ፣ ፌዴራል አወቃቀሩን ያስተካክሉ፣ ሕጎችን ያስተካክሉ/ያውጡ፣ ተቋማትን ይገንቡ። በጠቅላላው እንደ ፔንዱለም መወዛወዙን አቁመው፣ ከጃዋርና ኦነግ ተላላኪነትና ከተረኛ ገዥነት ወጥቶ፣ ብዙኀኑን የሚወክል የመንግሥትነት ኀላፊነቱን ይወጡ። የብዙኀኑን ጥቅምና ስምምነት የሚጻረሩ ሊመከሩ፣ ካልሆኑ በሕጉ መሰረት ለሠሩት ወንጀል ሊጠየቁ ይገባል።

የዲሞክራሲና የእኩል ተጠቃሚነቱ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ ገበሬውንና ከኦሮሞ፣ አማራና ትግሬ ውጭ የሆነውንም በገጠርና በዳር የሚኖረውን ትኩረቱ ውስጥ አስገብቶ መሥራት አለበት። 80 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ መተዳደሪያ፣ ዋናው የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ግብርና ወደ ጎን የተገፋ ይመስላልና ጥንቃቄ ይደረግ። እየተወሰዱ ያሉ የምጠኔ ሀብትና የመንግሥትን ላማት ድርጅቶች ወደ ግል ድርጅቶች ለመለወጥ የተግባራዊ የተደረጉና የሚደረጉ ፖሊሲዎች እንደገና ሊፈተሹ ይገባል። ጠንካራ መንግሥት የሚለካው ለብዙኀኑና ለቀጣይ አገር ህልውና በመሥራት እንጂ ጉልበትን የሥልጣን ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ለይቶ በማፈንና በማጥፋት አይደለም። ቅንነት የሌለው መንግሥት ለአገርም ለራሱም አይሆንምና። ይህን ማድረግ የሚችለው ግን በኦዴፓ ቤት ያለውን ቆሻሻ ካጸዳና ይህን የግርግረና የሴራ ፖለቲካ ካቆመ ብቻ ነው። ያለዚያ ግን አገር እየተተራመሰ፣ ቤቱን ሳያፀዳ በሥልጣኑ መቀጠሉ ለምንና ለማን እንደሚበጅ ግልፅ አይደለም።

መላኩ አዳል የባዮ ሜዲካል ሳይንስ የዶክትሬት ተማሪ ናቸው ።
በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here