ኢዜማ የክልሎች ልዩ ኃይል እንዲፈርሱ ጥሪ አቀረበ

0
727

በክልሎች የተሰማራው ልዩ ኃይል ህጋዊ መሠረት የሌለው በመሆኑ መፍረስ አለበት ብሎ እንደሚያምን ኢዜማ አስታውቋል፡፡ ሰላምና ፀጥታን ያሰፍናል የተባለው ልዩ ኃይል በየአካባቢው የግጭትና የስጋት ምንጭ መሆኑንም ፓርቲው ግልጿል፡፡

የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ የሕዝብን ፀጥታ፣ የዜጎችን ደኅንነት እንዲጠብቁ ኃላፊነት ቢሰጣቸውም የዚህን ተቃራኒ የሆነ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ በየክልሉ ያለው ልዩ ሃይል፣ በክልሎች መካከል ያለውን ልዩነት በወንድማማችነት መንፈስ ከመፍታት ይልቅ፣ እንደ ተለያዩ ሀገሮች እንዲተያዩ ማድረጋቸውን በማውሳት፣ በዚሁ ከቀጠሉ ለማእከላዊ መንግሥትም ስጋት መሆናቸው እንደማይቀር አሳውቀዋል፡፡

ናትናኤል እንደሚሉት፣ በተግባር የተስተዋለውም ሰላምና ፀጥታን ያሰፍናል የተባለው ልዩ ኃይል በየአካባቢው የግጭትና የስጋት ምንጭ መሆኑን ነው፡፡
ናትናኤል፣ በ2006 ሐምሌ ወር በጋምቤላ የክልሉ ልዩ ኃይል ከመከላከያ ሰራዊት ጋር መዋጋቱን አስታውሰው፣ ሁኔታውን ተከትሎ የክልሉን ልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት ደረጃ ተደርሶ የነበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም በ2008 በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት የክልሉ ልዩ ኃይል የግጭቱ አንድ አካል እንደነበር በፓርላማ ጭምር በአጣሪ ኮሚሽን መገለፁንና በሌላ በኩል በ2010 በሱማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ለአንድ ሚልዩን ዜጎች መፈናቀል ምክንያት በሆነው ግጭት ላይ ሁለቱ ክልሎች መሳተፋቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ይላሉ፡፡

አሁንም ከላይ ከተጠቀሱት ጥቂት ማሳያዎች በዘለለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክልሎች ፋክክር በሚመስል መልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር በማሰልጠን ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ናትናኤል፣ ኢዜማ ይሄን አደገኛና ህገ-ወጥ አደረጃጀት መፍትሄ ለመስጠት ወቅቱ አሁን ነው ብሎ ያምናል ብለዋል፡፡

የፌደራሊዝም መምህሩ ሲሳይ መንግስቴ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት፣ የፌደራሉንና የክልሎችን ሥልጣን በሚዘረዝሩት አንቀጾች 51(6) እና 52(2)(ሰ) ላይ እንደተገለጸው ሁለቱም መንግሥታት የየራሳቸውን የፖሊስ ተቋሟት እንደሚያቋቁሙ ይገልጻል፡፡ ሁሉም የክልል ሕግጋት መንግሥታትም ይኼንኑ ሥልጣናቸውን በድጋሜ አረጋግጠዋል፡፡ በመሆኑም በክልሎች ውስጥ ስላሉ የሕግና ሥርዓት ማስከበር፣ የሕዝብ ደኅንነትና ሰላምን ማስጠበቅ የየራሳቸው ተግባር ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ሥራ ለማስጠበቅ የተለያዩ ስያሜ ያላቸውን የፖሊስ ኃይል ቢያቋቁሙ ከልካይ የለባቸውም፡፡

ይሁን እንጂ የየራሳቸውን የፖሊስ ተቋሟት እንደሚያቋቁሙ ቢገልጽም፣ እንዴትና በምን መልኩ የሚለው ዝርዝር ሃሳብ ባለመቀመጡ አፈጻጸሙ ላይ ችግሮች እንዲስተዋሉ ማድረጉን የሚያወሱት ሲሳይ፣ መንግስት በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

በኢዜማ ዕምነት የተረጋጋች፣ ፍፁም ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፊታችን ከቆሙት ትልቅ ተግዳሮቶች አንደኛው ይሄ በየክልሉ የተደራጀ የታጠቀ ልዩ ኃይል ነው ብሎ ያምናል፡፡ ኢዜማ ይህን ሕገ-መንግስታዊ ያልሆነ በክልሎች ስር የተዋቀረ የፀጥታ ኃይል ህጋዊ ወደሆኑት የፓሊስ እና የመከላከያ ኃይል በመቀላቀል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መንገድ መጥረግ አለበት ይላል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here