የምርት ገበያ የሰኔ ግብይቱ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ

0
1473

ኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሰኔ ወር 45 ሺሕ ቶን የተለያዩ ምርቶችን በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገደማ ማገበያየቱን አስታወቀ። በምርት ገበያው ከተገበያዩት ውስጥ አዳዲስ ሰብሎች እንደሚገኙበትም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ምርት ገበያው የሚገቡት አዳዲስ ምርቶች የግብይት መጠኑ ከፍ እንዲል ምክንያት እንደሆኑትም ተገልጿል። በዚህ ዓመት ማለትም 2011 ታኅሣሥ ወር ላይ አኩሪ አተርና ሽምብራ ወደ ምርት ገበያው መካተታቸው የተነገረ ሲሆን በሰኔ ወርም 40 ቶን ሽምብራ በምርት ገበያው ተገበያይቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያ ላይ 40 ቶን ሽምብራም 7 መቶ 72 ሺሕ ብር ግብይቱ ተፈፅሟል። በሌላ በኩል ደግሞ ከሽምብራ ጋር ምርት ገበያውን የተቀላቀለው አኩሪ አተር በሰኔ ወር ላይ ከቡና በመቀጠል ከፍተኛ የምርት አቅርቦት የታየበት የምርት ዓይነት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ አረጋግጣለች።

አኩሪ አተር በሰኔ ወር 11 ሺሕ 409 ቶን መጠን ያለው ምርት ለግብይት የቀረበ ሲሆን 1 መቶ 77 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የግብይቱ ዋጋ ጠቅላላ ዋጋ ሆኖ ተመዝግቧል። በተጠቀሰው ወር አኩሪ አተር በምርት መጠን ከቡና ቀጥሎ በኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም በግብይት ዋጋ ከቡና እና ሰሊጥ ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱን አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። አኩሪ አተር ወደ ምርት ገበያው ከገባበት ከታኅሣሥ 2011 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 3/2011 ድረስ 92 ሺሕ 103 ቶን ምርት ለገበያ የቀረበ ሲሆን 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚሆን ግብይትም ተፈፅሟል።

በሰኔ ወር 2011 በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቀረበው የቡና መጠን 21 ሺሕ 372 ቶን ሲሆን አጠቃላይ የግብይት መጠኑም 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ነፃነት ተስፋዬ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። በወሩ በኹለተኛ ደረጃ ግብይት ዋጋ በማስመዝገብ የተጠቀሰው ሰሊጥ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ምርት መጠኑ በ11 በመቶ ቢቀንስም ያስመዘገበው የግብይት ዋጋ ደግሞ በተቃራኒው በ18 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ለማወቅ ተችሏል። በዚህም ረገድ በሰኔ ወር በምርት ገበያ በኩል 5 ሺሕ 760 ቶን ሰሊጥ የተገበያየ ሲሆን ለዚህም 3 መቶ 55 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ዋጋን አስመዝግቧል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሰኔ ወር 2011 ነጭ ቦሎቄ 1 ሺሕ 728 ቶን አቅርቦ 35 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አገበያይቷል። ምርቱ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ በ24 በመቶ የቀነሰ ሲሆን የግብይት ዋጋው ግን በ1 ነጥብ 3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በአጠቃላይ አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዚህ ዓመት ወደ ምርት ገበያው ከገቡት በስተቀር ሌሎች ምርቶች የምርት መጠናቸው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ማሽቆልቆል ማሳየቱን ገልፀው፤ የግብይተ ዋጋው ደግሞ ጭማሪ እንዳሳየ ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here