አዲስ አበባ በቸልተኝነት ቅርሷን እያጣች ነው!

0
1549

ከወራት በፊት በአዲስ አበባ በተለምዶ ፈረንሳይ የሚባለው አካባቢ ገነተ ኢየሱስ ቤተክርስትያን ከፍ ብሎ በልዩ ሥሙ “የራስ ካሳ ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው ቦታ የፈረሰ አንድ ቤት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በልማት ሥም የቤቶች መፍረስ አዲስ ባልሆነባት ከተማ ላይ የዚህ ቤት መፍረስ መነጋገሪ የሆነው ቤቱ ታሪክ የያዘ በመሆኑ ነው። የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ልማትን ተገን አድርጎ በቸልታ ለፈጸመው ድርጊት፤ “ቤቱ በቅርስነት ስለመመዝገቡ ምንም ዓይነት መረጃ የለኝም” የሚል ምላሽ መስጠቱም የሚታወስ ነው።

ቤቱ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ለአገራቸው ክብር እንዲሁም ነፃነት በአርበኝነት ሲታገሉ የነበሩት ወንድማማቾች መካከል የደጃዝማች አበራ ካሣ ነበር። ለጣልያን ባደሩ የገዛ ወገኖቻቸው ተላልፈው ተሰጥተው የተሰዉት ደጃዝማች አበራ ካሣ፤ ከዓመታት በኋላ እንዲህ ባለ የተቋም ግዴለሽነት አንድም ለሥማቸው መታሰቢያነት ይሆን የነበረው ቤት ተላልፎ ተሰጥቷል።

“የቅርስ ጥበቃ ሥራ አንድ የልማት አካል ነው” ያሉት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ጥገና ባለሙያ አቤል አሰፋ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ ቅርሶች እንደ ቅርስ እንደማይታዩ በመጥቀስ ባለሥልጣኑ (ባለ ስልጣን መሥሪያ ቤት ከመሆኑ በፊት) በአዲስ አበባ ቅርሶች አጠባበቅና ቅርሶቹ ስላሉበት ሁኔታ ማጥናት መመዝገብ የጀመረው በ1982 እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

እጅግ በርካታ ቅርሶች ባሏት አገር ላይ፤ ቅርስን በኪነ ሕንጻ ጥበብ አስደናቂ ከሆኑት ከላሊበላና አክሱም በዘለለ የሚመለከት ብዙ አይደለም። “በአዲስ አበባ ቅርስ አለ ወይ?” ብለው ስለመኖሩ የሚጠራጠሩ በባሕልና ቱሪዝም ተቋማት የሚሠሩ ሰዎች እንዳሉ መታዘባቸውን ጭምር አቤል ያነሳሉ። ይሁንና በእንጦጦ ከሚገኘው ቤተ መንግሥት ጀምሮ፤ በአዲስ አበባ በርካታ ቅርሶች ስለመኖራቸውም አስታውሰዋል።

“የአዲስ አበባ ቅርስ ስንል፤ የከተማዋን ምሥረታ ተከትሎ የከተማዋን መስፋፋትና ዕድገት እንዲሁም ርዕይ ያካተተ ነው። በኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ ምሥረታቸው ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ከተሞች ይለያል። አዲስ አበባም ነጻ ከተማ በመሆኗ ኋላ ቀር ቢሆንም እንኳን አገር በቀል ቅርጽ ነበራት” ብለዋል። ከዛም አልፎ የአፍሪካ ኅብረት ሲመሠረት፤የአዲስ አበባ ታሪክ ከኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ አድጓል።

በአዲስ አበባ የቅርስ ቤቶች ትኩረት ውስጥ የገቡበትና ለሥጋት የተጋለጡበት ምክንያት የተለያየና በርካታ መሆኑን አቤል አያይዘው ጠቁመዋል። ከመልሶ ማልማት፣ ከመሬት ዋጋ ንረትና ለቅርስ ጥበቃ ከተነፈገው ትኩረት አንጻር እነዚህ ቤቶች ሥጋት ውስጥ መግባታቸውን አንስተዋል።

በአዲስ አበባ ከተመዘገቡት 400 በላይ ቅርሶች መካከል በግለሰብ ይዞታ ሥር ያሉት በቁጥር 72 የሚደርሱ ናቸው። በውርስ የተቀበሉ ባለይዞታዎችም ቅርሶቹን ለማስተላለፍ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ባለሙያው ያነሳሉ። እንደውም “አዲስ አበባ ላይ የቅርስ ቤት መያዝ ዕዳ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ። ይህም ባለይዞታዎች በገንዘብ ተጠቃሚ ካለመሆናቸው በላይ በቅርሱ ኩራት የሚሰማቸው ባለመሆናቸው ነው። ከዚህ በተጓዳኝ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊነቱን አውርዶ ራሱን ማግለሉ፣ የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቅርስን በሚመለከት የሚንቀሳቀሰው አደረጃጀት የተጠናከረ አለመሆን፣ የባለሙያ እጥረትና የሕግ መጣረሶች ተባብረው ተግዳሮት መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

ባለሥልጣኑ በ1992 አሁን ባለው መጠሪያ ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ ኀላፊነቶች ተረክቧል የሚሉት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ምዝገባ ቁጥጥር ዳይሬክተር ደሳለኝ አበባው፤ በአዋጅ ቁጥር 209/1992 ከተቀመጡ የተቋሙ ሥልጣንና ተግባራት መካከል ቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር፣ ጥናትና ምርምር፣ ቅርስ ማሰባሰብ ብሎም ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ፣ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶችን አልምቶ ለቱሪስት ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የተንቀሳቃሽ ቅርሶች ልማትና ኤግዚቢሽን የማቅረብ ኀላፊነቶች ይገኙበታል።

በአዲስ አበባ በቅርሶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በተመለከተ፤ ባለሥልጣኑ የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከአቅሜ በላይ ነው ካላለው በቀር ጣልቃ እንደማይገባ ግን ገልጸዋል። አሁን ባለው የመንግሥትም ሆነ የተቋማት አደረጃጀት መሠረት፤ ባለሥልጣኑ በሁሉም ጉዳይ ላይ ይመለከተኛል ካለ ከታች በየደረጃው ያሉ አደረጃጀቶች አስፈላጊነታቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ስለዚህም ባለሥልጣኑ ራሱን ራቅ ማድረግን መርጧል።

ከዛም አልፎ እንደአገር ካለው የቅርስ ብዛትና ስፋት አንጻር ባለሥልጣኑ ለሁሉም ተደራሽ መሆን እንደማይቻለው ነው ያነሱት። በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች በተመለከተ ሙሉ ኀላፊነቱ የአዲስ አበባ የባልሕና ቱሪዝም ቢሮ ነው ማለት ነው። የተቋማቱ “ኃላፊነቱ የእናንተ ነው” ብሎ መጠያየቅ እንዳለ ሆኖ ሊዘነጋ የማይገባው ደግሞ የቅርሶች ምዝገባ ጉዳይ ነው።

ቅርሶች መመዝገባቸው በአንድ በኩል የሕግ ጥበቃና ከለላ እንዲያገኙ ያስችላልና፤ የቅርሶችን ምዝገባ ጉዳይም ደሳለኝ አንስተዋል። ይሁንና በአቅም እጥረትና ከብዛትና ስፋቱ የተነሳ ምዝገባ ላይ ችግር እንዳለ ነው የገለጹት። በዚህ መካከል ያልተዘመገቡ ቅርሶችም አደጋ ላይ መሆናቸውን ልብ ይሏል። ጉዳዩ በአዲስ አበባ ታሪካዊ የሆኑ ብሎም በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች ሲፈርሱ የበለጠ ትኩረት ተሰጠው እንጂ፤ አስቀድሞም በፓርኮች፣ በመንገድ ማስፋፊያና ግንባታዎች የፈረሱ ቁሳዊ ቅርሶችና የታጎሉ ማኅበረሰባዊ እሴቶች በርካታ መሆናቸው ግልጽ ነው።

አዲስ አበባ ላይ የተከሰቱትን የቅርስ ማፍረሶች በተመለከተ አዲስ ማለዳ መረጃ ለማሰባሰብ የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አቅንታለች። ደረጄ ስዩም በአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ቁጥጥርና ምዝገባ ኀላፊ፤ በአዲስ አበባ በ2003 እና 2008 የቅርስ ምዝገባ መደረጉን አስታውሰዋል። የተመዘገቡ ቅርሶችንም ለፕላን ኮሚሽን፣ ለመሬት ማኔጅመንት፣ ለግንባታ ፈቃድ፣ በዐሥሩ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ የባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች እንዲሁም ለከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ቀጥታ ግንኙነት አላቸው ለተባሉ አካላት ሁሉ እንዲያውቁት ተደርጓል ብለዋል።

በመንግሥት ተቋማት እየፈረሱ ያሉ የተመዘገቡ ቅርሶች ከግዴለሽነት የተነሳ ነው ብሎ በድፍረት ለመናገር የሚያስችለውም ይኸው ነው። ቀን ላይ ማፍረስ ጀምረው በማኅበረሰብ መሯሯጥና ከልካይነት ማፍረሻዎቻቸውን እንዲያነሱ ተነግረው ሳለ፤ “በሌሊት ሊያፈርሱት ይችላሉ” የሚሉ ሥጋቶች መፈጠራቸው የሚያሳየው፤ አፍራሾቹ መረጃ ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን እያወቁም እንደሚያጠፉ ነው።

ይህ ሁሉ ስለተመዘገቡ ቅርሶች ነው። ከወራት በፊት ተመሳሳይ ዕጣ የደረሰው “ቡፌትዳ ላጋር”ን ስንመለከት ያልተመዘገቡ ቅርሶች ዕጣ ፈንታም አሳሳቢ መሆኑን ማየት ይቻላል። በዚህ ላይ በባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቋሚ ቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር ባለሙያ ዘውድነሽ መንገሻ “ቡፌትዳ ላጋር”ን ጠቅሰው በቅርስነት አለመመዝገቡ ክፍተት እንደፈጠረ ጠቅሰዋል።

ዘውድነሽ እንዳሉትም ያልተመዘገቡ ቅርሶችን በተመለከተ ከሕግ አንጻር ጫና መፍጠር ይከብዳል። ይህም ሆኖ የመንግሥት ተቋማት ጋር ክፍተት ብሎም አለመናበብ መኖሩን ሳይጠቅሱ አላለፉም። ፈረሱ የተባሉ ቀድሞ የተመዘገቡ ቅርሶችን “ቅርስ እንደሆነ አላወቅኩም ነበር” በሚል ቸልተኝነት የሚያፈርሱት ተቋማት የመንግሥት ሆነው የተገኙበት ጊዜ ጥቂት አይደለምና።

አስናቁ ፀጋዬ በቢሮው የተንቀሳቃሽ ቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር ባለሙያ ናት። ችግሮች በስፋት መኖራቸውን ማሳያ ብላ የጠቀሰችው ለመጨረሻ ጊዜ የተደረገው የቅርስ ምዝገባ ምን ያህል ትኩረት ያልተሰጠው እንደነበር በመጥቀስ ነው። በ2008 የተካሔደው ምዝገባ አንድ ወር እንኳን የሚሞላ በቂ ጊዜ ሳይሰጠውና በጥቂት ባለሙያዎች ያውም ‘በጀት ለመቆጠብ’ ለሆቴሎች ብቃት ላይ ዳሰሳ ከሚያደርጉ ባለሙያዎች ጋር ተዳብሎ የተደረገ መሆኑን አስታውሳለች።

አስናቁ አያይዛ እንኳን በሌላ ተቋማትና በቢሮው ከክፍል ክፍል ከሚሰጠው ትኩረት አንጻር ለቅርስ ክፍል ያለው አመለካከት በእጅጉ አነስተኛ ነው ትላለች። “ማኅበረሰቡ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሚሠራውም ግንዛቤ የሌለው ነው። ቅርስ ምን እንደሆነ የማያውቁና ስሜት የማይሰጣቸው ሰዎች አሉ” ብላለች።

ሁሉም የሚያነሱት ነጥብ መካከል በአዲስ አበባ የታሪክ ስፋትና የቅርስ ብዛት ካለው ገንዘብና ባለሙያ አንጻር የሚደረገው ምዝገባ ማነሱን፤ በመዘናጋት ቸልተኝነት ምክንያት የሚመለከታቸው የመንግሥትና የከተማ አስተዳደሩ ክፍሎች ለቅርሶች የሚያደርጉት ጥበቃ ውስን መሆኑን፣ አዲስ አበባ ላሉ ቅርሶች የሚሰጠው ትኩረት እጅግ አነስተኛ እንደሆነ፣ ስለቅርስ በቂ ግንዛቤና ተቆርቋሪነት የሌላቸው ሰዎች ተቋማቱ ውስጥ መገኘታቸው እንደ ችግር የተጠቀሱ ናቸው።

እነዚህ ችግሮች መፍትሄ ካላገኙና በሚወሰዱ ሕጋዊ እርምጃዎች የቅርሶችን ዋጋ ከፍ ማድረግ ካልተቻለ፤ በአዲስ አበባ ከ400 በላይ ቅርሶች አሉና፤ ለአጥፊዎች ሁኔታዎች ተመቻችተው ይቆያሉ ማለት ነው።ኃላፊነቱ ወደታች ወርዶ ከተጠያቂነት በቅርብ ርቀት የሚገኘው ባለስልጣኑም፤ በየጊዜው ከክልል እንዲሁም ከክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ ለባለሙያዎች የሚሰጠው ሥልጠና ፍሬ ማፍራት የሚችለው ወርዶ በሚገባ መሥራት የሚችል ባለሙያ ሲኖር መሆኑም መዘንጋት አይርበትም።

ባለሥልጣኑ አሁን ላይ የሚገለገልበት አዋጅ ከተገባሩ በተሸለ ለቅርሶች ክብር እንደሚገባ የሚገልጥ ነው። በዚህም አንድ የአገር ሀብት፤ በቅርስነት እንዲመዘገብ በቀደመው ጊዜ እንደነበረው ዕድሜ ብቻ አይደለም ከግምት ውስጥ የሚገባው። በቀደመው አሠራር ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ እንደ ቅርስ ለመመዝገብ መስፈርት ነበር። አሁን ላይ በታሪክ፣ በባሕል፣ በሳይንስ፣ ዕደ ጥበብና ሥነ ጥበብ ተፈላጊነት ያለው መሆኑ እንደ ባለሙያ ከታየና ከተገመገመ ቅርስ ተብሎ ይመዘገባል።

በአዲስ አበባ የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ራሱን የቻለ ቅርስን የተመለከተ መዋቅር ተዘጋጅቶ ምደባ እየተካሔደ መሆኑን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች። ይህም ከሆነ በአዲስ አበባ ታሪክ የተሸከሙ ቅርሶችን በተመለከተ በሙሉ ኀላፊነትና ያለ ሰበብ አስባብ የሚሠራ፣ ተጠያቂ የሚሆንና የሚሟገት ክፍል ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ከሆነ የፈረሱት የአዲስ አበባ ቅርሶች መስዋዕት ሆነው ሌሎቹን እንዳተረፉ ታሪክ ይመዘግበዋል። በአዲስ አበባም ቅርስና ታሪክ ከልማት ጋር ተስማምተውና ተግባብተው ማየት ይቻላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here