በመዘዋወር ነጻነትና በውሕዳን መብቶች ላይ ጥናት እየተደረገ ነው

0
529

የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት፣ “የመዘዋወር ነፃነትና የውሕዳን መብቶች በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ አዲስ ጥናት እያስጠና ነው። ጥናቱ ለብሔር ተኮር ግጭቶች ምላሽ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮሚሽኑ ተናግሯል።

በሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ታደሰ ተሰማ፣ ጥናቱ በአምስት ክልልሎች በአማራ፣ ቤንሻንጉል፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና የኢትዮጵያ ሶማሌ በ29 ወረዳዎች ላይ ከ1 ሺሕ 80 ግለሰቦች በሚወሰድ ናሙና መሠረት በማድረግ እንደሚጠና ገልፀዋል።

ታደሰ፣ ጥናቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚያጠናው በአካባቢው ነባር ያልሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች /non-indigenous minorities/ መብቶታቸውን እንዴት እየተከበረላቸው እንደሆነ፤ መብት ሲባል የማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የመማር፣ የመቀጠር እና የአካል ደኅነነት መብቶችን እንደሚያካትት አንስተው፤ ከነባሮቹ የብሔረሰብ አንጻር ተከብሮላቸዋል ወይስ አልተከበረላቸውም ለሚለው ጥያቄ ይመልሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል። ኮሚሽኑ ይህንን ጥናት በUNDP የገንዘብ ድጋፍ እና በኮሚሽኑ የውስጥ አቅም እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል።

ዳይሬክቶሬቱ፣ ጥናቱን ለማጥናት እንዲያስችል ከኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት እና ጥናቱ ከሚካሔድባቸው ክልሎች ያሉ የኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች የተውጣጣ እና እያንዳንዱ ሦስት አባላት ያሉት አምስት ቡድኖች ከሰኔ 21/ 2011 ጀምሮ በተጠቀሱት አምስቱም ክልሎት ተሰማርተዋል ብሏል። የቡድን አባላቶቹ በ25 ቀናት ውስጥ መረጃውን ሰብስበው እንደሚመጡ ይጠበቃል። በቀጣይ 2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት መጨረሻ ጥናቱ ተጠናቆ ለኅትመት እንደሚበቃ አዲስ ማለዳ ከኮሚሽኑ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ጥናቱ እንዲጠና መነሻ የሆነው አንዱ ምክንያት ከ2008 ጀምሮ የተፈጠሩ ብሔር ተኮር ግጭቶች ሲሆኑ፣ በአንድም በሌላ መልኩ ሲንፀባረቁና የአገሪቱን ፀጥታ ሲያውኩ የነበሩት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋሉት ተወላጅ ያልሆነውን ዜጋ የማግለል እንቅስቃሴዎች መሆናቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪም፣ በተደጋጋሚ ለኮሚሽኑ ይቀርቡ የነበሩ አቤቱታዎችም ለጥናቱ መነሻ እንደሆኑ ገልፀዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በሰብኣዊ መብት ላይ የሚሠሩ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ ለብሔረሰብ ተኮር ጥቃቶችና ግጭቶች የማያዳግም የፖሊሲና የአፈጻጸም እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳስብ መግለጫ በማውጣት ድርጊቱን ሲያወግዙና ሲመክሩ እንደነበር ያስታወቀው ኮሚሽን መሥሪያ ቤቱ ለእነዚህ ችግሮች ዘላቂና አጋዥ መፍትሔ ለማምጣት የበኩላቸውን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here