ለ75 ዓመታት በብሔራዊ ሙዝየምነት በማገልገል ላይ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም ራሱን ችሎ እንዲዋቀር ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ታወቀ። በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሥር እንደ አንድ ክፍል ሲተዳደር የቆየው ሙዚየሙ ሥሙ እና መዋቅሩ ተቀይሮ “የተንቀሳቃሽ ቅርሶች ልማት ዳይሬክቶሬት” ተብሎ በ2006 ተዋቅሮ እንደነበር ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ራሱን የቻለ ሙዝየም እንደ አገር ሳይኖራት ቆይቷል።
የሙዝየም አደረጃጀትና መዋቅር ራሱን ችሎ አለመኖሩ ኢትዮጵያን በሙዝየም የሚገባውን ያህል ተወዳዳሪ እንዳትይሆን እንዳደረጋት የሙዝየምና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ልማት ዳይሬክተር ኤፍሬም አማረ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። የአገር ውስጥ እና የውጪ ጎብኚዎች በሚጠብቁት ልክ ሙዝየሙ አገልግሎት እንዳይሰጥ ያደረገው መዋቅሩ በተጨማሪም በነበረበት የበጀት ጥገኝነት በመዋቅሩ ሊካተቱ የሚገባቸው ባለሙያዎች እንዳይካተቱም አድርጓል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ይረዳል የተባለው የሕግ ማዕቀፍ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ተረቅቆ ለኢፌዴሪ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቀርቦ እየታየ ሲሆን፤ በቅርቡም ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚኖር መድረክ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዋጁ ውይይት ተደርጎበትና ባለድርሻ አካላት መክረውበት በመመሪያ ወደ ተግባር ሲወርድ፤ ከአደረጃጀት ጀምሮ ያሉበትን ችግሮች እንደሚፈታ ይጠበቃል ያሉት ኤፍሬም አክለውም እርምጃው የሙዝየሙን ተወዳዳሪነት ከፍ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
“ትንሽ ቅርስ ያላቸው አገራት ያላቸውን አሰማምረው ነው የሚያቀርቡት፤ እኛ ግን የቅርስ ሀብት አለን። አደረጃጀቱን ማላቅ ሲቻል ተወዳዳሪነቱ ከፍ ይላል። አሁን ባለበት ደረጃም ብዙ ጎብኚ አለ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም ከ75 ዓመታት በፊት በአፄ ኀይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተቋቋመ ሲሆን፤ በወቅቱ ቅርስ በማሰባሰብና ለዕይታ በማቅረብ “ቤተመዛግብት ወመዘክር” (የአሁኑ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ድርጅት) ተብሎ አገልግሎት ይሰጥ ነበር። በኋላ ቅርስ ስብስቡ እየጨመረና ጥናቶች እያደጉ ሲሔዱ በሒደት ሙዝየሙ ብቻውን ሲወጣ በዘገምተኛ ሒደት የአሁኑ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ተቋቁሟል።
እስከአሁን ድረስ የሙዝየምነት እውቅና ሳይኖረው ቢቆይም፤ የቱሪዝት መዳረሻ ሆኖ ያገለግል የነበረው ብሔራዊ ሙዚየሙ ከ1985 ጀምሮ እስከ 2009 ድረስ በነበሩ ዓመታት በ1 ሚሊዮን 933 ሺሕ 662 የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኚዎችን እንዳስተናገደ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011



