የስደተኞች ተፅእኖ በአዲስ አበባ

0
531

ሮቤል አይኖም የ24 ዓመት ለግላጋ ወጣት ነው። ከሰሜናዊ ቀይ ባሕር ዳርቻ ከሆነችው ኤርትራ ግዛት አካለ-ጉዛኤ ከኹለት ዓመት በፊት ነበር ቀን በአቃጣዩ ሐሩር ሌት አስቸጋሪውን ቁር ተቋቁሞ ድንበር አሳብሮ ወደ ኢትዮጵያ የገባው። መጀመሪያ ትግራይ ክልል እንዳባጉና በተባለ ጊዜያዊ መጠለያ የስደተኛ ከለላ ከተደረገለት በኋላ ወደ ሽመልባ ስደተኛ ጣቢያ እንዲተላለፍ እንደተደረገ የሚናገረው።

ሮቤል ወደ ኢትዮጵያ ለመኮብለል ያነሳሳው ከዓመታት በፊት ታላቅ ወንድሙ እና እህቱ እሱ በመጣበት መንገድ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ተከትሎ ሲሆን ወንድም እና እህቱ የስደተኛ ምዝገባውን በሚገባ አሟልተው ከጨረሱ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከውጭ አገር የሚላክላቸውን ገንዘብ እንደምንም በማብቃቃት እየኖሩ እንደሚገኙ በመረዳቱ እሱም ልቡ ወደ ስደት ተነሳሳ (የሚሰማው ነገር ከነበረበት ኑሮ እጅግ ቅንጡ ነበር)። ሮቤልም ሆነ ቤተሰቦቹ ኢትዮጵያ ከኤርትራ አንጻር ልዩነቱን መግለጽ የማይችሉት ጉዳይ ቢሆንባቸውም ልባቸው ግን ወደ ሦስተኛ አገር መሻገርና የበለጠ እና የተሻለ ሕይወት መኖር ነው።

“በሽመልባ ስደተኛ ጣቢያ ከወር በላይ አልተቀመጥኩም” በማለት በትግረኛ ቅላጼ የሚናገው ሮቤል ቀድመው በአዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩትን እህትና ወንድሙን ለመቀላቀል መቻሉን ይናገራል።

የሮቤልን ታሪክ እዚህ ጋር እንግታው እና አዲስ ማለዳ ሮቤልን እና መሰል ስደተኞችን አቅፋ በያዘችው አዲስ አበባ ተዘዋውራ ያገኘችውን እንቃኝ። የስደተኞችን መበራከት ተከትሎ ዘርፈ ብዙ የኑሮ ውድነቶች እየተከሰቱ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታዝባለች። በተለይ ደግሞ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሚገኙበት የቦሌ አራብሳ መኖሪያ አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጉልህ የሚታይ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ለመረዳት ተችሏል። በዚህ አካባቢ ከዚህ ቀደም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ይታይ የነበረው ባለ አንድ መኝታ ቤት 1 ሺሕ 800 ብር ዋጋ በአሁኑ ጊዜ ወደ 2 ሺሕ 600 መቶ ብር ማሻቀቡን ለማወቅ ተችሏል። ይህ ደግሞ በቀደመው ጊዜ የባለ ኹለት መኝታ ቤቶች የኪራይ ዋጋ እንደነበር አዲስ ማለዳ ለጉብኝት በሔደችበት ወቅት በአካባቢው በቤት አከራይ እና ተከራይ በማገናኘት የሚሠራው ወንድወሰን አበባው የሚናገረው። እንደ ወንድወሰን አስተያየት ከአንድ ዓመት ወዲህ በርካታ ኤርትራዊያን ስደተኞች መግባታቸውን ተከትሎ የቤት ኪራይ ዋጋ በድንገት ማሻቀቡን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ሥሙ ቄራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በርካታ ኤርትራዊያን የሚገኙበትና ከ1990ው የኹለቱ አገራት ጦርነት በፊት በርካታ የኤርትራ ተወላጆች ይኖሩበት የነበረ አካባቢ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህ አካባቢ አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ የአካባቢውን ነዋሪዎች ባናገረችበት ወቅት ምላሾችን ተቀብላለች። የቄራ አካባቢው ነዋሪ ኤሊያስ መንሱር “ቄራ የድሮ ሥሙ እንጂ በአሁኑ ሰዓት ፀብ የለም። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጠጥ ቤቶች እና ዋና መንገዶች ላይ ፀብ መከሰት ጀምሯል፤ በአብዛኞቹ ደግሞ [የፀቡ ተሳታፊዎች] ከኤርትራ የመጡ ስደተኞች ናቸው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

በዚሁ አካባቢ የኤልያስን ሐሳብ የሚደግፉ በርካታ ለቁጥር የሚያዳግቱ ሰዎች ማግኘት አዳጋች አይደለም። በተመሳሳይም በንፍስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የቄራ አካባቢ የማኅበረሰብ ዐቀፍ የፖሊስ አገልግሎትም ለአዲስ ማለዳ ሲገልጽ በአካባቢው የድብድብ ወንጀሎች እየተበራከቱ እንደመጡ እና በአመዛኙም ከኤርትራ የመጡ ስደተኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ከማኅበረሰብ ዐቀፉ የፖሊስ አገልግሎት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአብዛኛው ድብድቡ ከነዋሪው ጋር ሳይሆን በስደተኞች መካከል በሚከሰት አለመግባባቶች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ የሱማሊያ ዜግነት ያላቸው ስደተኞች ይገኙበታል በተባለው በቦሌ ሚካኤል አካባቢም አዲስ ማለዳ ቅኝቷን አድርጋለች። በዚህ አካባቢ ከስደተኞች ጋር ተያይዞ ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ የለም የሚል አስተያየት ሰጪ በርካታ ቢሆንም የአብዱሰላም ሽኩሪ አስተያየት ግን ቀልብ የሚገዛ ነበር።

“ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ማስተናገዷ ባይከፋም ስደተኞች ግን እንደ አስተናጋጅ አገር ሳይሆን ግዴታ አድርገው የሚቆጥሩ አሉ። እዚህ አካባቢ ለምሳሌ እኛ እዚህ ባንመጣ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምታገኘው ገቢ አይኖርም። ስለዚህ እኛ የኢትዮጵያ ገቢ ማስገኛዎች ነን የሚሉ አሉ” ሲል በሌላ መንገድ የስደተኞችን አስተሳሰብ አስቃኝቶናል።

በኢትዮጵያ የሚገኙት የጎረቤት አገራት ስደተኞች ወደ ሦስተኛ አገር ለመሻገር የነበራቸው ፍላጎት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተቀዛቀዘ የመጣ ይመስላል። ይህ የሆነበት ምክንያት በቅርቡ በኢትዮጵያ ውስጥ በስደተኝት የሚገኙ የውጭ አገራት ዜጎች የመሥራት፣ የንብረት ባለቤትነት መብት እንዲሁም ዜጋ እስከ መሆን የሚደርስ ሕግ ተግባራዊ ካደረገች በኋላ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የባለታሪካችን ሮቤል እህት አዝመራም ባለመብት ስላደረጋት ሕግ በግልፅ መናገሯ የሐሳቡን እውነተኛነት ድጋፍ ይሰጣል። “[ከእንግዲህ] ወደ ሦስተኛ አገር መሻገርን የምናፍቀው ጉዳይ አይደለም፤ እዚህ መሥራት ጀምሪያለሁ።” ትላለች

በእርግጥ የአዝመራና ወንድሞች ገና ከትውልድ ቀያቸው ሲነሱ መዳረሻቸውን ጣሊያን አድርገው ስለነበር የቀድሞው ጉጉታቸው ይቀንስ እንጂ አሁንም ልባቸው ረግቶ ኢትዮጵያ ላይ ጎጆ ሊቀልስ አልቻለም።

አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተርን ከበደ ጫኔን አነጋግራለች። ዳይሬክተሩ ሲናገሩ፤ በሕጋዊ መንገድ በስደተኛ ጣቢያዎች ተመዝግበው በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች መኖራቸውን በመግለጽ አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ ሦስተኛ አገር ለመሻገር እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ፍላጎት እንደሌላቸው ያስረዳሉ። ጣሊያን ከኢትዮጵያ ወደ የኹለት ዓመቱ ከ500 እስከ 600 ኤርትራዊ ስደተኞችን እንደምትቀበል አስረድተዋል።

ስደተኞቹን ተከትለው ተከሰቱ ስለተባሉት ኢኮኖሚያዊ እና ሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ሲያብራሩም። “የኑሮ ውድነቱ እኔ በተለያዩ የኀላፊነት ቦታዎች በነበርኩባቸው ጊዜያት ይከሰቱ የነበሩ ችግሮች እንጂ የስደተኞችን መምጣት ተከትሎ የመጣ አዲስ ጉዳይ አይደለም” ሲሉ ይናገራሉ። ቀጥለውም በሰላምና መረጋጋቱ በኩል እምብዛም እውቀቱ እንደሌላቸው እና በስደት መጥተው ጥገኝነት ሳይጠይቁ ወደ መሐል አገር ገብተው ዘመድ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥራቸው ብዙ ስለሆነ የሰላም መደፍረሱም በዛው ልክ ሊጨምር እንደሚችል አንስተዋል።

በቅርቡ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በሚመለከት ስለ አፀደቀችው ሕግም ሲናገሩ “ማንም ስደተኛ አገሩ ሰላም ከሆነ ሰው አገር ላይ የፈለገ ቢመቸው መኖር አይፈልግም። ሕጉም [ቢሆን] እስከ አሁን ድረስ ተግባራዊ አልሆነም። ስለዚህ የስደተኞች ተረጋግቶ መቀመጥ ጉዳይ ከአዲሱ ሕግ ጋር የሚያያዝ አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በማያያዝም ከበደ በአሁኑ ወቅት በሱማሌ ክልል ደሎ የስደተኛ ጣቢያ ከዓለም ዐቀፍ ለጋሾች ጋር በመተባበር ስደተኞች እና ዜጋው ሕዝብ በጋራ አካባቢውን እያለሙ የሚጠቀሙበትን መርሃ ግብር ተቀርፆ 70 በመቶ ከነዋሪው 30 በመቶ ደግሞ ከስደተኛው በማድረግ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here