የሕዝብ ንብረቶችን ወደ ግል የማዞር ኹለቱ ገጽታዎች

0
971

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አንጋፋ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን እና መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ወደ ግል ለማዞር ያሳለፈው ውሳኔ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ባለሙያዎችን ለኹለት በመክፈል ሲያከራክር አንድ ዓመት አልፏል። የአዲስ ማለዳዋ ሐይማኖት አሸናፊ ውሳኔውን በተመለከተ የተቋማቱን ቀድሞ ኀላፊዎች እንዲሁም ይመለከታቸዋል ያለቻቸውን ምሁራንና ባለሙያዎች አነጋግራ ርዕሱን የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጋዋለች።

ግንቦት 28/2010 በአዲስ አበባ የተደረገው የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ 36ተኛ የሥራ አስፈፃሚ ጉባኤ ከልማታዊው መርሁ የማይጠበቁ ውሳኔዎችን ይዞ በሰበር ዜና ነበር ብቅ ያለው። በወቅቱ አዲስ በነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፊት ላይ የሚታየው ፈገግታም በእጃቸው ላይ ይዘው ወደ ስብሰባ አዳራሹ የገቡት ወረቀት ላይ ምን እንዳለ የመስማት ጉጉትን ይጨምራል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በምክትላቸው ደመቀ መኮንን የተመራው መደበኛ ስብሰባ ኢቲዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኀይል ማመንጫዎች፣ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ድርጅት ትልቁን የአክሲዮን ድርሻ መንግሥት ይዞ ቀሪውን የአገር ውስጥ እና የውጪ ባለሀብቶች እንዲይዙ “አቅጣጫ ማስቀመጡን” መገናኛ ብዙኀን በየተራ ተቀባበሉት።

በሥራ ላይም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የባቡር ፕሮጀክቶች፣ የሆቴል አገልግሎት እንዲሁም የተለያዩ የማምረቻ ፕሮጀክቶች በአክሲዮን ሽያጭ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ይዞታ እንዲተላላፉ ሲል አካትቶ ውሳኔው አስነበበ። ሥራ አስፈፃሚው በዚህ ሒደትም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ዕድል ለመስጠት መታሰቡ ለውሳኔው እንደምክንያት ከተዘረዘሩት ሐሳቦች መካከል ይገኛል።
ውሳኔው የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግዶ እንደተለመደው በአዲስ አጀንዳ ከመተካት ይልቅ ላለፈው አንድ ዓመት በየጎራው ክርክሮችን ማስተናገዱን ቀጥሏል። በተለይም በእንግሊዝ አገር ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ባልደረባ ለሆኑት፣ ለእንደ እዮብ ባልቻ (ዶ/ር) ላሉ ምሁራን ፓርቲው ለ27 ዓመታት ይዞ ከመጣው የኢኮኖሚ ማኒፌስቶ በድንገት የመታጠፍ አካሔድ መሆኑንና በብዙ መልኩ አደጋ ይዞ እንደሚመጣ በተለያየ ግዜ ሲገልፁ ነበር፡፡

በሚያዚያ ወር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በተደረገው በአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ እንዲሁም በተደጋጋሚ በትዊተር ገጻቸው ተቃውሟቸውን የሚያሰሙት እዮብ በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት እነዚህን ውሳኔዎች የሚያሳልፍበት ምንም ዓይነት ቅቡልነት የለውም በማለት ያብራራሉ። ተወዳድሮ ባሸነፈበት ምርጫ ወቅት በግሉ ዘርፍ የሚመራ የምጣኔ ሀብት መርህን እንደሚከተል የገለፀው ነገርም የለም ሲሉ ውሳኔው ሕዝብ የፈቀደው አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
የእዮብን ሐሳብ የሚጋሩት የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ክቡር ገና ሕዝቡም ለዚህ አጀንዳ መልስ እንዲሰጥ በምርጫው አልተጠየቀም መልስም አልሰጠም ሲሉ ያስረዳሉ። “የዘይት ፋብሪካ ወይም የዳቦ ፋብሪካ ተሸጧል። አሁን ግን የምናወራው መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ስለመሸጥ ነው። ይህ ከዚህ ቀደም ሲደረግ ከነበረው ወደ ግል የማዛወር ሒደት የተለየ ነው” ሲሉ የሚናገሩት ክቡር “እነዚህ ሀብቶች ለአገር ውስጥ ወይም ለዓለማቀፍ ገዢዎች እንዲቀርቡ ሕዝቡ ተጠይቆ የመከረበት ጊዜ አላጋጠመኝም፤ የሕዝብ ድምፅ የሚመስል ነገር እንኳን አልተደረገም” በማለት ሐሳባቸውን አጠናክረዋል።

ይልቁንም የምርጫ ዘመኑ መገባደጃ ላይ ኢሕአዴግ ይህንን ውሳኔ ይዞ መምጣቱ ያልተለመደ ነው የሚሉት ክቡር እነዚህ ሀብቶች ሲገነቡ ከአንድ መንግሥት በላይ የፈጁ ሆነው በአንድ መንግሥት በቀላሉ ሲሸጡ ከዚህ መንግሥት በኋላ ሊመጣ የሚችለውን ፖሊስ ሊያደናቅፉ ይችላሉ ሲሉ ሥጋታቸውን ጠቅሰዋል።
ክቡር ለገበያ የቀረቡትን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለኹለት በመክፈል መሰረታዊ እና መሰረታዊ ያልሆኑ የሕዝብ አገልግሎቶች የሚሰጡ በማለት፤ እንደስኳር ያሉ ፍብሪካዎችን በምሳሌነት በማንሳት “መሰረታዊ ያልሆኑት የመንግስት ድርጅቶች ወደ ግል ማዛወሩ ችግሩ አይታየኝም” ብለዋል። ይሁንና ስትራቴጂያዊ ሀብቶች የሚባሉት መሰረታዊ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የተወሰነው ውሳኔ ግን የምጣኔ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ህልውና ጉዳይ ናቸው ሲሉ በአንክሮ መታየት እንዳለበት ያሳስባሉ።

ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ በልማት ድርጅቶች ላይ የሚነሳው የተወዳዳሪነት እና የውጤታማነት ጥያቄም ተቋሞቹ በተሰጣቸው አቅም ልክ የሚመዘን ነው ሲሉ ክቡር ይናገራሉ። “ከቦርድ ጀምሮ የድርጅቶቹ ኀላፊዎች እንዴት እንደሚመረጡ የሚታወቅ ነው፣ ዛሬ ደካሞች ስለሆኑ ካልሸጥናቸው የምንላቸው እነዚህ ድርጅቶች ደካሞች ሆነው እንዲመጡ ስለተደረጉ ነው” በማለት ያብራራሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት ግርማ ዋቄ እንደሚሉት የኢትዮጵያ አየር መንገ ትርፋማ ከመሆኑ ባሻገር የአገሪቱን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማንቃቱን እና የእቃ ማመላለሻ ክንፉም ለወጪ ንግዱ ያለውን አበርክቶ ለአየር መንገዱ ስትራቴጂአዊነት እንደ ማስረጃ ያነሳሉ፡፡ ግርማ አክለውም የአገሪቱ የወጪ ንግድ የማያመጣውን የውጪ ምንዛሬ የሚያመጣው አየር መንገዱን መሸጥ ማለት በብር የሚሰበስበውን ትርፍ ሳይቀር በዶላር ይዘው ለሚወጡ ባለሀብቶች አሳልፈን እንሽጥ ማለት ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ክቡር በግርማ ሐሳብ ባለመስማማት ይዘው የሚወጡት የውጪ ምንዛሬ አሳሳቢ አይደለም ይላሉ። “እንደቴሌኮም እና አየር መንገድ ያሉ ዓለማቀፍ ንግድን የሚያካትቱ ሥራዎች ከውጪ የሚገኘው ገቢ ይዘው የሚወጡትን ወጪ የሚሸፍን ይመስለኛል” ሲሉ ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ክቡር ተቋማቱ ካላቸው የኢኮኖሚ ዋጋ በበለጠ በገንዘብ የማይተመነው የብሔራዊ ማንነት ላይ የሚያመጣው ጫና ቀላል አይደልም ሲሉ ይከራከራሉ። “በአፍሪካ ውስጥ ስጓዝ የማየው አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን በከሰረ አየር መንገድ ካላቸው ሼር ይልቅ ስኬታማ በሆነው የኢትየጵያ አየር መንገድ ላይ ያላቸው የእኔ ነው የሚለው ስሜት እና ኩራት ይበልጣል፡፡ አሁን ካለንበት ከፋፋይ የፖለቲካ ዓለም ውስጥ አንድ ብሔራዊ ማንነትን ለመፍጠር እነዚህ አገራዊ ኩራቶች ትልቅ ሚና አላቸው።”

እነዚህ እንደ አገር የሚያስማሙን እና በጋራ አሉን የምንላቸው ተቋማት ከተሸጡ አገሬ ውስጥ ምን አለኝ ወደሚለው መሔድ ይመጣል ሲሉ ክቡር ያነሳሉ። አክለውም በአውሮፓ ስላሉ እና ከመንግሥት እጅ ስለወጡ መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሲያስረዱ ‹‹የድርጅቶቹ ባለቤቶች የጡረታ ባለሥልጣኑ፣ የከተማ አስተዳደሮች ወይም ባንኮች ናቸው፤ ያ ማለት ደግሞ ድርጅቶቹ የሕዝብ ናቸው ማለት ነው።››

የአፍካን ፖለቲካል ኢኮኖሚ መምህሩ እዮብ በበኩላቸው በሚኖሩበት አገረ እንግሊዝ መሪው የሠራተኞች ፓርቲ ትልቁ ማኒፌስቶ በግለሰብ እጅ ያለውን መሰረታዊ አገልግሎት ወደ መንግሥት መመለስ ወይም በየክፍለ አገራቱ አዳዲስ የሕዝብ አገልግሎቶችን መዘርጋት መሆኑን አንስተው እኛስ ለምን ወደኋላ እንሄዳለን ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ “በእንግሊዝ ሃገር የባቡር አገልግሎቱ ምንም ዓይነት የአገልግሎት መሻሻል ሳያሳይ ዋጋው ግን በየዓመቱ እስከ 15 በመቶ ጨምራል፣ ስድስቱ የኤሌትሪክ አቅራቢዎችም እንደፈለጉ ዋጋ ይጨምራሉ መንግስታቸውም ይህንን ለመቀየር እየሰራ ነው” ሲሉ ያነጻጽራሉ።

መንግሥት እነዚህን መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደ ግል የማዘዋወሩ ውሳኔ የከተሜውን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለገበሬው፣ ለገጠር ሴቶች እና እናቶች ምን ይጠቅማል የሚለው ያልተሰላ ድንገተኛ ለውጥ መሆኑን እዮብ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል። በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ግለሰቦች እንዲወስኑ ማድረግ ማለት በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት በመብት ላይ የተመሰረተ የዜግነት ግንኙነት መሆኑ ቀርቶ የገዢ እና ሻጭ ግንኙነት መሆኑ ጤናማ ያልሆነ ነው ሲሉ ያክላሉ። መንግሥት በገበያ መርህ ላይ ተመስርቶ መሰረታዊ ፍላጎቶችን በሚያመጡት ትርፍ ላይ ከተመሰረተ በተለይ የገጠሩ ኅብረተሰብ ተጎጂ ይሆናል ብለዋል።

“ውሃ፣ መብራት እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ዜጎች አንዱ ዕድገትን የሚጋሩበት መንገድ ነው፣ ለዚህም ማሳያ መንግሥት እስከ ዛሬ ከቴሌኮም የሚሰበስበውን ገንዘብ ለባቡር ልማት ብድር ሲከፍል እንደኖረ ሁሉም ያውቀዋል” ሲሉ በአዲስ ወግ ላይ ባቀረቡት በጽሑፋቸው ሰነድ ላይ ያተቱት እዮብ “ከዚህ በኋላ ግን ትርፉን ለባለድርሻዎቹ ያከፋፍላል ማለት ነው። ይህ ማለት መሰረታዊ የመብራት፣ የውሃ የቴሌኮም እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ከመንግሥት ዜጎች የሚጠየቋቸው መብቶች ሳይሆኑ ገንዘብ ያለው ብቻ የሚገዛቸው አገልግሎቶች ይሆናሉ ማለት ነው” በማለት እዮብ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።

ቴሌኮም
የቀድሞው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር) በእዮብ ሐሳብ ባለመስማማት መንግሥት የቴሌኮሙን ገበያ ለግል ውድድር ክፍት ማድረጉ በጥንቃቄ ከተተገበረ ውጤቱ ትልቅ ይሆናል ይላሉ፡፡

“ህብረተሰቡ ማግኘት የሚፈልገውን ያህል አገልግሎት አልሰጠነውም ነበር፣ እነዚህ ተቋማት ሲመጡ እና ውድድር ውስጥ ስንገባ በአንድ አመት ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጡ የሚገመት ነው። ነገር ግን ቴሌኮም ማለት መደበኛ አገልግሎት ማለት ብቻ ሳይሆን የአገር ደኅንነት ጉዳይ ማለትም ጭምር ነው” ሲሉ አንዷለም መወሰድ ስላለበት ጥንቃቄ አፅንኦት ይሰጣሉ፡፡

የሕንድን ተመክሮ ያነሱት አንዷለም ‹‹በህንድ ሃገር የቴሌኮም ለግል ባለሃብቶች ክፍት በሆነበት ወቅት አዳዲሶቹ አገልግሎት ሰጪዎች በነጻ ነበር አገልግሎት የሰጡት›፡፡ የመንግሥትን አገልግሎት አቅራቢ ባልተገባ ፉክክር ሰው እንዲያማርረው እና እንዲጠላው በማድረግ ድርሻውን ሙሉ ለሙሉ [ለግል ባለሀብቱ] ሸጦ እንዲወጣ የማድረግ ፖሊሲ ነበር የተከተሉት” በማለት ሐሳባቸውን በማስረጃ አስደግፈዋል።

ይህ እና መሰል ነገሮች በኢትዮጵያ ገበያ እንዳይደገም አዲስ የሚቋቋመው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው በትንሽ ድርሻ ወደ ገበያው በመግባት የመጠቅለል ፀባይ ከዓለማቀፍ ልምዶች አንጻር በተደጋጋሚ ያጋጠመ ሆኑንን ያስታውሳሉ። በዚህም ረገድ የማቋቋሚያ አዋጁን እንደተመለከቱት እና በጥንቃቄ መሠራቱ ላይ ጥርጥር እንደሌላቸው ገልፀው ዋናው ነገር ይህንን ሕግ መተግበር የሚችል፣ ቴሌኮሙን የሚያውቅ እና ቀጣይነት ያለው ተቋም መፍጠር መቻል ነው ይላሉ።

በቴሌኮሙ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በዓለም ላይ የታየው ልምድ መንግሥታት ድርጅቶቻቸውን ወደ ግል ሲያዞሩ ከፍተኛውን ድርሻ መንግሥት ይዞ መሸጡ የተለመደ መሆኑን ክቡር ገናም ያረጋግጡታል። በሒደትም መንግሥት ዝቅተኛ ድርሻ እንዲይዝ ከማድረግ ባለፈም ሙሉ በሙሉ የተወገደበት መንገድም አለ ይላሉ።
“እነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች ድርጅቱን ትርፋማ ለማድረግ በሚል የአስተዳደር ሥራውን ለመሥራት ይጠይቃሉ፤ ከዛም የካፒታል ዕድገት ያስፈልገዋል ብለው ድርጅቱ እዳ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ኪሳራ ውስጥ በመጣል በመጨረሻም የመጠቅለል ጥያቄ እንዲቀርብላቸው ያደርጋሉ” ያሉት ክቡር፤ “በአጭሩ ዝቅተኛ ድርሻ ይዘው ይግቡ የሚለው የተለመደ የእግር ማስገቢያ ነው።”

እነዚህ የንግድ ተቋማት ቴሌኮሙን ሲይዙ በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሰው ያለባቸውን የከተማ ቦታዎች በመምረጥ የገጠሩን ነዋሪ የመተው ልምድ በሌሎች ሃገራት መታየቱን የሚጠቅሱት አንዷለም በተመሳሳይ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ በዚህ ረገድ ወጥ አሠራር መዘርጋት እንዳለበት ይናገራሉ። ሌላው የኔትወርክ ማማዎች አተካከል እና የመጋራት ሒደቱ የተቆጣጣሪው ትኩረት መሆን ይገባዋል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

“በተወሰነ ሜትር ራዲየስ የሚተከለው የኔትወርክ ማማ በሕግ ካልተቀመጠ የሕዝብ መሬት ያለአግባብ መቀራመታቸው አይቀሬ ነው። በአዲስ አበባ ካሉት ከ700 በላይ ማማዎች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው በጄነሬተር ኀይል የሚጠቀም ሲሆን ይሄንን በአራት ብናባዛው ከተማዋ በጄነሬተር ጭስ ከመታፈኗ ባሻገር የሚባክነውን መሬት ማሰብ ይቻላል” ሲሉ እንደ አንዷለም አሳስበዋል።

የቴሌኮም ዘርፉን ለ125 ዓመታት ያለተወዳዳሪ ይዞ የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም ብቸኛው የሰለጠነ የሰው ኀይል ምንጭ ቢሆንም ብቃት ያለው የሰው ኀይል ልማት አለው ብለው እንደሚያምኑ አንዷለም ይናገራሉ።

“በልምድና በሥልጠና የጠገቡ ሠራተኞች አሉት ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን አሁን ያለው ሠራተኛ ለአራት ኦፕሬተሮች እንደማይበቃ ግልፅ ነው። በተለይም የውድድር መንፈስ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ። [ይሁንና] አዳዲስ ባለሙያዎችን በማሠልጠን በጥቂት ዓመታት የአገር ውስጥ የሰው ኀይሉ ሊያድግ ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

ከፍተኛ ገቢ የሚያገኘው ቴሌኮሙ ሠራተኞቹን መክፈል ላይ ከሲቪል ሰርቪስ አሠራር ወጥቶ ማሻሻል ይችላል የሚሉት አንዷለም በሳቸው የሥልጣን ዘመን ብቁ የሚባሉት የቴሌኮም መሃንዲሶች ወደ ውጪ አገራት ጥለው ይሔዱ እንደነበር ገልጸው ውድድሩ እዚህ ድረስ ሲመጣ ደግሞ ጫናው ከፍ ያለ መሆኑ አይቀርም ብለዋል።

የቴሌኮሙ የገበያ ብቸኝነት፣ መልካም ሥሙ እና የንግድ ስሙን ጨምሮ የቴሌኮሙ የማይዳሰሱ ሀብቶች በአግባቡ ተለክተው ዋጋ ካልወጣላቸው ድርጅቶቹ ሲገቡ ዋጋው ሲለካ መቀነሱ አይቀርም ሲሉ ከሽያጭ በፊት ቅድሚያ መሠራት የሚገባውንም ነገር ጠቁመዋል። ይህንን ቴሌኮሙ ገለልተኛ አካል ቀጥሮ ዋጋውን በአግባቡ በማስለካት ትልቅ ሚና መጫወት አለበት ሲሉ ምክረ ሐሳብ ለግሰዋል።

አንዷለም በዚህ ወደ ግል የማዞር ሒደት ውስጥም የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ሲደግፍ የነበረው ቴሌኮም የግለሰቦች ኪስ ማደለቢያ እንዳይሆን ሥጋታቸውን አልሸሸጉም። ከሽያጩ ጋር በተያያዘም በአዲስ አበባ ቢሮ ከፍተው የቅስቀሳ ሥራ የሚሰሩ ቡድኖች የተለያዩ ባለሥልጣናትን የማግባባት እንዲሁም መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር ሙከራ ማድረጋቸው አይቀርም በማለት መንግሥት እነዚህ ቡድኖች ነገር ከማበላሸታቸው በፊት እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ሲሉ አንዷለም ያስጠነቅቃሉ።

‹‹እንደዚህ አይነት የቢሊዮን ዶላር ግብይቶች ላይ ርብርቡ ቀላል አይደለም። በእኛ ግዜ እንኳን ትንንሽ ጨረታዎችን ስናወጣ ጫና ለማሳደር ብዙ ሙከራ ይደርግ ነበር›› ያሉት አንዷለም ‹‹በየትኛውም የአለም ክፍል የቅስቀሳ ቡድኖች አሉ፣ በአፍሪካ ግን ጠምዝዞ የማስፈጸም አቅማቸው ከፍ ያለ ነው›› ብለው ‹‹ቴሌኮሙ የህዝብ ሃብት ሆኖ ሳለ በዚህ ተግባር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ግን እጅግ ያሳዝኑኛል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በውጪ ምንዛሬ እጥረት የቴኮሙን አቅም በእጥፍ ያሳድገዋል የተባለውን ኹለተኛውን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማስፈፀም እንዳልተቻለ የተናገሩት አንዷለም አሁን ያለው አመራር የውጪ ምንዛሬ ችግሮችን ለመፍታት የወሰደውን እርምጃ አድንቀው ማስፋፊያው እንደሚካሔድም ተስፋቸውን ተናግረዋል።

የቴሌኮም መሰረተ ልማቱ እስከሚስፋፋም አገልግሎት ሰጪዎቹ ደንበኛ በመከፋፋል ያለውን መሰረተ ልማት አቅም አሟጠው መጠቀም እንደሚችሉ አብራርተዋል። የሚመጡት ድርጅቶችም የቴሌኮም የጀርባ አጥንት የሆኑ ሥራዎች ውስጥ ግን መግባት እንደሌለባቸው ያሳስባሉ።

የቴሌኮሙ የጀርባ አጥንት የሚባሉት በመሬት ውስጥ የተቀበሩ ገመዶች፣ ማማዎች፣ በባሕር ውስጥ ያሉ ማስተላለፊየዎችን ያጠቃልላል። መሰረተ ልማቶቹን መንግሥት ይዞ መቀጠሉ ምንም አማራጭ የለውም የሚሉት አንዷለም የሞባይል ኔትወርኮችን ግን ሌሎቹ ቢገቡበትም እንብዛም ችግር የለውም ይላሉ፡፡

‹‹የሰሜን አሜሪካን መንግሰት ጨምሮ አብዛኛው የአለም ሃገራት የቴሌኮማቸው የጀርባ አጥንት ላይ ሙሉ ቁጥር አላቸው። መንግስት መዝጋትም መክፈትም የሚችልበት ቁጥጥር ባለው መልኩ መዋቅሩ መደራጀቱ አግባብ ነው፣ ያ ካልሆነ ግን የሃገር ህልውናን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።››

በአጠቃላይ ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ያለበት አቋም የትኛውንም ተፎካካሪ የመወዳደር አቅም ገንብቷል የሚሉት የቀድሞው ሥራ አስፈፃሚ፤ መንግሥት ቁጥጥር ማድረግ በሚችልበት ሁኔታ መደራጀት አለበት፤ አለበለዚያ ግን የአገር ህልውናን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በዚህ ረገድ የተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ሚና ትልቅ መሆኑን አስምረዋበታል።

አየር መንገድ
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ አስገራሚ ለውጥ መርተውታል የሚባሉት የቀድሞ ሥራ አስፈፃሚው ግርማ ዋቄ ወደ ግል ባለቤትነት በማዞር መሰረታዊ መርህ እንደሚስማሙ ገልፀው ጊዜው ግን አሁን እንዳልሆነ ይናገራሉ።

አንድ ባለቤት በንብረቱ የፈለገውን ያደርጋል፤ ሲፈለግ ይሸጠዋል ሲፈልግ ያካፍለዋል የሚሉት ግርማ የኢትዮጵን ሕዝብ በባለቤትነት የሚወክለው መንግሥት እስከሆነ ይጠቅማል ያለውን ይወስናል ይህንን አከብራለሁ ይላሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመንግሥት ካዝና ገንዘብ ስጡኝ ብሎ ወይም በመንግሥት ዋስትና ብድር ከወሰደ ረጅም ጊዜ ማለፉን በማጣቀስ በአየር መንገዱ ምክንያት መንግሥት ገቢ እንጂ ወጪ የለበትም ሲሉ ያስረዳሉ።

‹‹በሌላው ዓለምም አየር መንገድ ይሸጣል›› የሚሉት ግርማ “የእንግሊዙ ብሪቲሽ አየር መንገድ በከፊል ተሸጧል ሉፍታንዛም እንዲሁ።ንብረቶቹን ወደ ግል ማዞሩ ስህተት ነው አልልም ነገር ግን የሚያስቸኩል ነገር አይደለም። በረጅም ጊዜ ጥናት በሳይንሳዊ መንገድ መካሔድ አለበት” ብለዋል።

ግርማ መንግሥት የገንዘብ እጥረት ካለበት ከአየር መንገዱ የትርፍ ክፍያ መጠየቅ እንዲሁም በውጪ ምንዛሬ በኩል ሊያግዝ ይችላል ሲሉ አማራጭ አቅርበዋል።
ወደ ግል ባለቤትነት የተዘዋወሩ የአፍሪካ አየር መንገዶችን በቅርበት የተከታተሉትና በአቬሽን ኢንዱስትሪ ላይ ለረጅም ዓመታት በመዘገብ የሚታወቁት ቃለየሱስ በቀለ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ግል ማዘዋወር ነጥብ የለውም ሲሉ ይሞግታሉ። ከኬኒያ አየር መንገድ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በቃለ ምልልስ ወቅት አየር መንገዱ በውጪ አገር ባለቤቶቹ እንዲሁም ሕዝብ በያዘው ድርሻ ምክንያት ባለው የፍላጎት መብዛት አስፈላጊውን ውሳኔ ማሳለፍ ያለመቻሉ አንዱ ማነቆ እንደሆነባቸው እንደገለፁላቸው ያወሳሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን መንግሥት ከባለቤትነት ባለፈ እንደሌሎች አየር መንገዶች በዕለት ተዕለት ሥራው ላይ እንብዛም ጣልቃ የማይገባበት በመሆኑ እና እንደ ኬኒያ አየር መንገድ “ብዙ አለቃ” ስለሌለው አግባብ ውሳኔዎችን በፍጥነት መስጠቱ ለስኬቱ መሰረት ነው ሲሉ ቃለየሱስ ይናገራሉ።

ከሌሎች ዓለማቀፍ ተቋመት ጋር በመተባበር ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ እና ሆቴሉን ጨምሮ የካርጎ አገልግሎቱን በምሳሌነትም የሚያነሱት ቃለየሱስ የአየር መንገዱ ድርሻን ለገበያ ማውጣት ግን አግባብ አይደለም ይላሉ። የአፍሪካ አየር ገበያ 80 በመቶ ከአፍሪካ ውጪ ባሉ አየር መንገዶች መያዙን በማስመልከት የአፍሪካ አየር መንገዶች እንዳይጠፉ አየር መንገዱ አዲስ ሚና መጫወት መጀመሩን ገልጸው የፓን አፍሪካዊነት ሥሜቱን ለማጠናከር ሲባል የተጀመረ ሚና ነውም ብለዋል።

ሌሎች አየር መንገዶችን ማጠናከር የቻለ አየር መንገድን መሸጥ ለምን አስፈለገ የሚለው እና የሌሎች አፍሪካ አገሮችን አየር መንገዶችን እንዲገዛ ከተፈቀደ ለምን የእኛን እንከለክላቸዋለን በሚለው ክርክር ኹለተኛውን ሐሳብ የሚደግፉት ቃለየሱስ፤ የሞዛምቢክ አየር መንገድን መቶ በመቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መያዙን ለምሳሌነት ያነሳሉ። ወንድማማችነት ማጠናከሩ እንዳለ ሆኖ ግን የአየር መንገዱን ድርሻ አንስቶ በመሸጥ ሳይሆን ባሉት ተጓደኝ ሥራዎች ላይ ግን ትብብር በመፍጠር ማሳካት ይቻላል ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ወደፊት አየር መንገዱ በከፊል ይሸጥ የሚለው ላይ መስማማት ቢኖር እንኳን በቅድሚያ ለኢትዮጵያውያን ቀጥሎም ለአፍሪካውያን በመሰጠቱ ይስማማሉ። የ
አቬሽን ተንታኙ ቃለየሱስ እንደሚሉት የእቃ ማመላለሻ ክንፉ በተለይም አበባ ወደ ውጪ መላክ ሲጀመር አየር መንገዱ በኪሳራ የወጪ ንግዱን ሲደግፍ እንደበር ተናግረው አሁንም ብዙ የአገር ውስጥ በረራዎች በኪሳራ የሚሠሩ እና አትራፊ ከሆኑት መስመሮች አየር መንገዱ እንደሚያካክስ ይናገራሉ። የውጪ ባለሀብት ድርሻ ቢኖረው ግን ከንግድ እና ከአዋጪነት ውጪ ለአገር ምጣኔ ሀብት ወይም ለዜጎች ተጠቃሚነት የሚስብበት ምክንያት የለም ሲሉ ቃለየሱስ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

ከአየር መንገዱ ዋና ሥራ ጋር የማይገናኙትን ወደ ግል በማዛወር የሥራውን ጫና ማቅለል አለበት ተብሎ በሚነሳው ነጥብ ላይም የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ግርማ ለአየር መንገዱ የመስተንግዶ ሥራ መሥራት የሚችል ድርጅት ስላልነበረ በራሱ መንገድ የገነባውና ለራሱ ደንበኞች ብቻ የሚያገለግልለት ስርዓት ፈጥሯል ሲሉ ይናገራሉ። የሆቴል እንዲሁም የጥገናን ጨምሮ የተለያዩ የአየር መንገዱን ክንፎችም ለራሱ ሥራ የሚጠቀምባቸው እንጂ ከሌሎች የተጋራቸው እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

የኬኒያን እና የደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች ላይ የተወሰዱ ወደ ግል ሃብት የማዞር እርምጃዎችን የሚያነሱት ግርማ “አፍሪካ ውስጥ መንግሥት የሌለበት አየር መንገድ ጉልበት የለውም፤ [የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፊል ሽያጭ] ቢቆይ መልካም ነው” በማለት ግርማ የአገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ችግር እስኪፈታና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የመግዛት አቅም እስኪያድግ ድረስ ብለው ሐሳባቸውን ደምድመዋል።

እንደማጠቃለያ
መንግሥት የተለያዩ ዓይነት የውስጥ እና የውጪ ጫና ውስጥ ገብቶ የልማት ድርጅቶችን በአንድ ጊዜ ለገበያ አውጥቷል፣ ለዚህም በችኮላ ውስጥ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም አደጋ ላይ ጥሏል የሚሉ አስተያየቶች ተደጋግመው ሲሰጡ ተደምጠዋል።

ይህንን በተመለከተ ስራዎች የሚሰሩበት ሂደት ፍጥነት አለው ብሎ ለማመን በቂ የሚባለው ጊዜ ምን ያህል ነው የሚለው በገደብ መቀመጥ አለበት ሲሉ የሚናገሩት በገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) ከውሳኔው በኋላ ያለው ሒደት ጊዜ ተወስዶ እየተሠራበት ይገኛልም ብለዋል። በምሳሌነት የቴሌኮምን ዘርፍ ከጉዳዩ ከአንገብጋቢነት አንጻር ከሚጠበቀው በላይ ጊዜ የፈጀ ነው ሲሉ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

“የአገሪቱ የብሮድባንድ ኢንተርኔት ሥርጭት ከዜሮ በታች አምስት በመቶ ነው። ይህ ማለት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ፣ ከዚህም 70 በመቶ ወጣት ሃይል ይዘን ፍጠኑ [እና] ወጣቶችን በአንድ ላብቶፕ እና በፈጣን ኢንተርኔት ወደ ዓለማቀፍ ገበያ ይቀላቀሉ ነበር መባል የነበረበት” ሲሉ ያብራራሉ። ከዚህ አንጻርም የኮሚኬሽን አዋጁ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመላኩ በፊት የገንዘብ ሚኒስቴር የቴሌኮም ሪፎርም ቡድን አቋቁሞ ይህንን ማጥናቱን እና ይህም በቂ የሚባል ጥንቃቄ ተደርጎ መሠራቱን ያመላክታል የሚል እምነት እንዳላቸው ብሩክ ጨምረው ተናግዋል።

ለእዮብ ግን ይህ ጉዳይ የቴክኒክ ሥራ እና አግባብ ባለው ሕግ የመወጣት ብቃት ሳይሆን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግሮችን መፍታት ችግር ነው። “ጥያቄው በዝናብ ላይ ለተመሰረተው ግብርና ወይም ለ80 በመቶ ገበሬ መፍትሔ የሌለው እና ለዚች ትልቅ አገር ለምትፈልገው የልማት አቅጣጫ ማን የበለጠ ይቃኘው የሚለው ጥያቄ ነው አንገብጋቢ” ሲል በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በተዘጋጀው ውይይት ላይ ያቀረቡት ጽሑፍ ያትታል። ‹‹የከተማው ሰው ጥያቄ ጥሩ ኢንተርኔት የገጠሩ ሰው ደግሞ ልጁንን የሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ነው የሚፈልገው፡፡››

መንግሥት ዋነኛ ሚናውን እየተጫወተ ምጣኔ ሀብቱም በጤናማው ጊዜ እና ሁኔታ ከስህተቶቹ እየተማረ ይሒድ የሚሉት እዮብ መንግሥት ከጨዋታው ሁሉ ወጥቶ ዳር ሆኖ ይይ በሚለው እንዳማይስማሙ ገልጸዋል።

መንግሥት በተደጋጋሚ የሚገልጸው ግለሰቦች ሥራውን ሲይዙ ውድድር ይጨምራል በሚለው ሐሳብ ዙሪያ ታዋቂው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጆሴፍ ስቲግኒዝ እንደይማስማሙ እና ሁሌ እንደማይሠራ “ፕራይስ ኦፍ ኢንኢኳሊቲ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አመላክተዋል። “በመንግሥት ተቋማት ውስጥም ሆነ በግል ድርጅቶች ውስጥ የግለሰብ ሚና ተመሳሳይ ነው። በተጨማሪም አትራፊ ድርጀቶች ለሙስና የተጋለጡ ናቸው የሚለው ሐሳብም ዋነኛው ደላይ እና ጉርሻ አቅራቢም የግሉ ዘርፍ ነው” ሲሉ ይከራከራሉ። ቅልጥፍናን ለመጨመር ተብሎ ወደግል የሚዞሩ ሃብቶችም የማዘዋወር ሂደቱም ይቅር በታዳጊ ሃገራት በአገረ አሜሪካም ለሙስና የተጋለጠ እንደሆነ ይናገራሉ።

የገንዘብ ሚኒሰቴሩ ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ መንግሥት በሦስት ደረጃ ባዋቀረው ኮሚቴ ለእንዲህ ዓይነት ድርጊቶች በር የሚዘጋ መሆኑን ተናግረዋል፤ በተለይም ቀድመው በሚወጡ መረጃዎች እና ሰነዶች ኢ-ፍትሐዊ ውድድርን እንዳይመግቡ በጥንቃቄ እየተሠራ መሆኑን በማመልከት።

ቴክኒካል ኮሚቴ፣ ስቲሪንግ ኮሚቴ እና ማክሮ ቲም የሚባሉ ሶስት ደረጃዎች ታልፈው ውሳኔዎች የሚወሰኑ ቢሆንም፤ ያልተገቡ አዝማሚያዎች መኖራቸው ስለማይቀር እሱንም መንግሥት ጥብቅ ክትትል ያደረጋል ብለው እንደሚምኑ ተናግረዋል።

‹‹የኔ አመለካከት እንደ ስኳር ፋብሪካ ያሉ የተሰሩ ስተቶችን ኪሳራ መንግስት ይሸከም ሳሆን ስህተቶቹን ማረም ይቻላል፣ ያለፈውም ሂደት ብዙ መልካም ውጤቶች ነበሩት›› የሚለው የእዮብ ፅሁፍ ‹‹ልማታዊነት ወድቋል ወደ ማናውቀው ሌላ ጥግ እንሂድ ማለት ዲሞክራሲን ሞክረናል ስላልተሳካልን አምባገነንነት እንሞክረው እንደማለት ነው›› ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

የሰሜን አሜሪካንን 2008 የኢኮኖሚ ቀውስ የሚያስታውሰው ፅሁፋቸው ‹‹የቀውሱ ምክኒት ገበያ መር ኢኮኖሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን መንግስት የቁጥጥር አቅሙን በማጣቱም ጭምር ነው›› ብሎ ‹‹ኢትዮጵያም ሳይረፍድ ከዚህ ትማራለች ብዬ አስባለሁ›› ሲል ያገባድዳል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here