የበጀት ዓመቱ የስንዴ ፍጆታ በእጥፍ ዕድገት አሳየ

0
1220
  • ግዢውን ለመፈጸም ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደራጓል

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ ለኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ለግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር እና ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዢ መፈጸሙን እና ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አስታወቀ።
በበጀት ዓመቱ ከፍተኛውን የስንዴ ፍጆታ ለተፈናቀሉ ዜጎች በብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል የተሰራጨ ሲሆን 6 መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚሆነው ስንዴ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ መገዛቱም ታውቋል።

ለኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን 1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ገደማ ወጪ የተደረገ ሲሆን ለግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር 1 መቶ 55 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ ማድረጉን አመላክቷል።

በዓመቱ ውስጥ አገልግሎቱ ለትራንስፖርት ባለሥልጣን የትራንስፖርት ትራፊክ ማኔጅመንት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሕንፃ ግንባታ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ገደማ እና ለቃሊቲ መናኸሪያ ግንባታ ግዢ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ ያ ደረገ ሲሆን ለእነዚህም 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ግዢ መፈፀሙን የአገልግሎቱ ሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ አሰፋ ሰለሞን አስታውቀዋል።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በ2011 በጀት ዓመት የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት የሚውሉ በማዕቀፍ ስምምነት ጨረታ በብር 2 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር፣ የስትራቴጂክ ግዥ በብር 11 ነጥብ 1 ቢሊዮን እና ለግንባታ ግዢ በብር 8.2 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለተሽከርካሪ ግዥ በብር 9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ ያደረገ ሲሆን ለእነዚህም ግዢዎች በድምሩ 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ግዥ ፈጽሟል።

የግዥ አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በብር መጠኑ የ15 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን ለብልጫው በምክንያትነት ከሚጠቀሰው ውስጥ በበጀት ዓመቱ በርካታ የስንዴ ግዥ የተፈጸመ በመሆኑና የስንዴው መጠን ከባለፈው በጀት ዓመት ከተገዛው የ815 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብልጫ ያለው መሆኑ አገልግሎቱ አስታውቋል።

በበጀት ዓመቱ ተሽከርካሪዎች፣ ቁርጭራጭ ብረታ ብረቶች፣ ያገለገሉ ቶነር ካርትሬጆች፣ ያገለገሉ የተሽከርካሪ ጎማዎች፣ ከመነዳሪዎችና እና ያገለገሉ የተሽከርካሪ የመኪና ባትሪዎችን በግልጽ ጨረታ በማስወገድ በድምሩ ብር 94 ሚሊዮን ገደማ ገቢ አስገኝቷል። የተወገደው ንብረት የገቢ መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ35.3 በመቶ ማነስ አሳይቷል። ከዚህ ቀደም በአገልግሎቱ በኩል ይወገዱ የነበሩ የልማት ድርጀቶች ቁርጭራጭ ብረታ ብረቶች፣ በራሳቸው ንብረቶቹን እንዲያስወግዱ ከገንዘብ ሚኒስቴር ሰርኩላር በመተላለፉ መጠኑ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here