ከኀይል ይልቅ ሕጋዊ አማራጭ ይቅደም

0
1000

ሰሞኑን በአገር ዐቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የተለያዩ አካላት ስብሰባ ሲያካሒዱበትና መግለጫ ሲያወጡበት የከረሙት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት ሥር የሚገኘው የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ጎልቶ ወጥቷል።

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 (3) መሰረት ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር መብት አለው። ይህ መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡና ሕዝቡ በሰፈረበት መልከዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌደራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል ብሎ ይደነግጋል። ከዚህም በተጨማሪ በክልል የመደራጀት ጥያቄ የሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ በአንቀጽ 47 (3) ላይ ተጠቅሷል።

በክልልነት የመደራጀት መብትን ለመጠቀም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጥያቄዎች እየቀረቡ ይገኛሉ። ለአብነትም በደቡብ ክልላዊ መንግሥት የክልላዊ ጥያቄያቸውን አፅድቀው ለክልሉ መንግሥት ያቀረቡ 11 ዞኖች እንደሚገኙ ይታወቃል። ምንም እንኳን የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ከሌሎቹ በንጽጽር ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ሲሆን ለደቡብ ክልል መንግሥትና በክልሉ መንግሥት አማካኝነት ደግሞ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ሕጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ የቀረበ ጥያቄ ነው። በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈፃሚነት የሚካሔደውን ሕዝበ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆኑና ዕጣ ፈንታውን የመወሰን ተግባር ብቻ እንደቀረው ያመላክታል። እንደዚህ ዓይነት ሕጋዊ አካሔድ ሌሎች በተመሳሳይ የክልልነት ጥያቄ ለሚያቀርቡ አካላት አስተማሪ በመሆኑ ሊከተሉት ይገባል።

የደቡብ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ የምርጫ ቦርድ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው ለማስፈጸም እየሔዱበት ያለው አግባብ በአዎንታዊ መልኩ መታየት አለበት ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ለአብነትም የክልሉ ገዢ የሆነው የደበቡ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የክልልነት ጥያቄን በጥናት ላይ ተመስርቶ ማላሽ ማግኘት እንዳለበት በመወሰን በዝርዝር ሕዝቡን ያሳተፈ ጥናት ማድረጉን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ላይ መግለጹ ይታወሳል። በጥናቱ የቀረቡ አማራጮችን በመመርመር የሕዝቡን የጋራ ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጠውን አማራጭ በመውሰድ የክልልነት አደረጃጀት ጥያቄዎችን በሚመልሱበት አግባብ አቋም መውሰዱን ጨምሮ በመግለጫው ላይ አትቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9/2011 ባወጣው መግለጫ ደግሞ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄን ሕዝበ ውሳኔ ለማካሔድ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል። ይሔም ሌላው በአዎንታዊነት የሚወሰድ ተግባር በመሆኑ እውቅና መስጠት ያስፈልጋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ራሱን እንደአዲስ የማደራጀት ሥራን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቦርዱን ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳን ሹመት በማጸደቅ መጀመሩ ይታወሳል። በተከታታይም የቦርዱን ሥልጣንና ተግባር የሚወስነውን ሕግ ማርቀቅና በተወካዮች ምክር ቤት የማጸደቅ፣ የምርጫ ሕጎችን የማሻሻልና ተቋማዊ ለውጦችን የማከናወን እንቅስቀሴ ሲያደርግ መቆየቱ በቅርበት የቦርዱን እንቅስቀሴ ለሚከታተሉ ሁሉ ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው። አራት የቦርዱን አባላት ሹመት ሰኔ 6/2011 መከናወኑም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

በተለይ ከላይ የተጠቀሱት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ አደረጃጀት በአገር ውስጥ የሲዳማውን ሕዝበ ውሳኔ ጨምሮ ሌሎች ሕዝበ ውሳኔዎች እንዲሁም አገር ዐቀፍና ክልላዊ ምርጫዎች ፍትሐዊ፣ ነፃና ተዓማኒ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ብቃት እንዲኖረው አዎንታዊ ሚናቸው ከፍተኛ ነው። የሲዳማውን የክልልነት ጥያቄ በተመለከተ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሔድ ምርጫ ቦርዱ ዝግጅት እያደረገ ለመሆኑ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ላይ ማስታወቁ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህም ቦርዱ ኀላፊነቱን ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት የሚያሳይ በመሆኑ በአዎንታዊ መልኩ ይወሰዳል።

ይሁንና የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሰላምና ደኅንነት ተለይቶ አይታይም። በዚህ ሳምንት ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደቡብ ክልል በተለይ አዋሳና ዙሪያዋ ውጥረት የሰፈነበት ድባብ እንዳለ እንዲሁም የፀጥታ አካላትም በከተማዋ ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝት እንዲሁም ከሌሎች መገናኛ ብዙኀን ዘገባ ለመረዳት ችላለች።

ይህንን ውጥረት ተከትሎ በተለይ በአዋሳ ከተማ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምፆች እንደሚሰሙና ቁጥሩን ማረጋገጥ ባይቻልም የሰዎችን ሕይወት የነጠቁ ግጭቶችም መፈጠራቸው እየተሰማ ይገኛል፤ መገናኛ ብዙኀንም ይህንኑ በመዘገብ ላይ ናቸው።

አዲስ ማለዳ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ፀጥታ የማስከበር ጉዳይ የክልሉና የፌደራል መንግሥታቱ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ ከማስከተሉ በፊት በትኩረት እንዲያጤኑትና ሁኔታዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ይገባቸዋል ትላለች። ሁሉም አካላት ከኀይል ይልቅ ሕጋዊነት እንዲያስቀድሙም አበክራ አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች።

በተለይ የአገር ሰላምና ደኅንነት በከፍተኛ ደረጃ ፈተና ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት የሲዳማና ሌሎች በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት ሥር የሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ተጨማሪ የፀጥታና ደኅንነት ሥጋት ምንጭ ሊሆኑ አይገባል። ሁሉም ወገኖች ሰከን ባለ መልኩ ሁኔታዎችን መመልከት እንዲሁም ሕግን የማክበርና የማስከበር ኀላፊነት እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ እያሳሰበች፤ ሕገ መንግሥታዊ የሆነው የክልልነት ጥያቄ ጨምሮ ሁሉም ነገሮች ምላሽ የሚያገኙት አገር ስትኖር፣ የአገር ሕልውና ሲጠበቅ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባዋል ስትል ያላትን መልዕክት ታስተላልፋለች። ሁሉም ዓይነት ጥያቄዎች ሕግን መሰረት ባደረገ መልኩ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል በማለትም መልዕክቷን ትደመድማለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here