ሰኞ፣ ሐምሌ 15 በሲዳማ ዞን የተቋቋመውን “ኮማንድ ፖስት” መገናኛ ብዙኀንን ጨምሮ ብዙዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ ጋር አንድ አድርገው መመልከታቸው ስህተት ነው የሚሉት ማርሸት መሐመድ፥ በሲዳማ ዞን የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት እርምጃዎችን መውሰዱ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው ነው ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። ይሁንና ክልሉ በፌደራል ጸጥታ አካል ዕዝ ሥር በሚተዳደር ኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር ሲል ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የሰጠው ውሳኔ ሕጋዊ መሰረት የለውም ብለዋል።
የሲዳማ ዞን በክልል የመደራጀት መብት ከሐምሌ 11/2011 ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ አለበት በሚል ወደ ጎዳና በወጣው የብሔሩ ወጣት – ኤጄቶ – እና ጸጥታ አካላት መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት በዞኑ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድም፣ የሃይማኖት ተቋማት እንዲቃጠሉ፣ ለወጣቶች መታሰር እንዲሁም በዞኑ የሚገኙ የሌላ ብሔር ተወላጆች ለስደት እንዲዳረጉ ሆኗል።
በሲዳማ ዞን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር እንዲሁም መላ ክልሉን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ሐምሌ 15/2011 ባወጣው መግለጫ ከሐምሌ 15 ቀን ጀምሮ አጠቃላይ የክልሉ ጸጥታ ጥበቃ በፌደራል የጸጥታ ኀይል ቁጥጥር ሥር ሆኖ በዕዝ ሥርዓት (command post) እንዲመራ ወስኗል። መግለጫው “የክልሉ መደበኛ የጸጥታ መዋቅር ውጤታማ ስላልሆነ” በመደበኛ መንገድ የሕግ የበላይነት ማስከበር አለመቻሉን ጠቅሶ ችግሩን ለመፍታት ኮማንድ ፖስት በክልሉ መንግሥት ጥያቄ እንደተቋቋመ ያትታል።
በነገራችን ላይ በአንዳንድ መገናኛ ብዙኀን እና ማኅበራዊ ገጾች በደቡብ ክልል “አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” እንደታወጀ ተደርጎ የተዘገበው በስህተት ነው። የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት መግለጫ ስለ ክልሉ ጸጥታ ቁጥጥር ሥርዓት ከማተት ባለፈ በግለሰቦችም ሆነ በቡድን መብቶች ላይ ገደብ የማያደርግ፣ የተከለከሉ ተግባራትንም ያላካተተ እና በሕገ መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጅበትን ሥርዓትም ጠብቆ የተደነገገ ስላልሆነ መግለጫውን እንደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውሰድ ተገቢ አይደለም።
‘ኮማንድ ፖስት’
የኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ሥርዓት በአገራችን በሰፊው ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በ2009 ታውጆ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኋላ ነው። በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስተሩ የሚመረጡ አባላትን ያካተተ እና በጠቅላይ ሚኒስተሩ በራሱ የሚመራ ኮማንድ ፖስት የተቋቋመው ሲሆን ተግባሩም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም እንዲከታተል እና እንዲመራ ነበር። በ2010 ዳግም ታውጆ በነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት ሲራጅ ፈጌሳ የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ነበር። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላም የኮማንድ ፖስት በተለያዩ ጊዜያት ተቋቁሟል። ወለጋ አካባቢ፣ በቅማንት፣ በመተከል፣ እና ሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመቆጣጠር የተቋቋሙትን ኮማንድ ፖስቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
በአጠቃላይ ኮማንድ ፖስቶቹ የሚቋቋሙት የተለያዩ የፌደራል እና ክልል ጸጥታ አካላትን በጋራ የሚያሰባስብ ዕዝ በመመስረት ሲሆን ዓላማውም የፌደራል እና የክልል ጸጥታ አካላትን አቀናጅቶ በመምራት የተከሰተውን የጸጥታ ችግር መቆጣጠር ነው። ሲቋቋሙም የፌደራል እና ክልል ጸጥታ አካላትን በጋራ በማቀናጀት ሲሆን፣ የሚቋቋሙትም በአዋጅ ወይም በጊዜያዊነት በጸጥት አካላት ቅንጅት ነው። በደቡብ ክልል በሳምንቱ መጀመሪያ ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በቀር፣ በብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት የተቋቋመ ኮማንድ ፖስት አናገኝም።
እስኪ በብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ የተቋቋመውን እና የደቡብ ክልል በፌደራል ጸጥታ አካላት ዕዝ ሥር እንዲተዳደሩ በሚል የተላለፈውን ውሳኔ ሕጋዊነት እና ሕገ መንግሥታዊነት እንመርምር።
የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ተግባር
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በ1994 በአዋጅ ቁጥር 257/1994 የተቋቋመ በፌደራል መንግሥት አስፈጻሚው አካል ሥር የሚገኝ ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ ቢያንስ ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን እነዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ምክትላቸው፣ የውጭ ጉዳይ እና መከላከያ ሚኒስትሮች፣ የደኅንነት ዋና አዛዥ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ናቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨማሪ ሰዎችን ሊሰይምም ይችላል። ምክር ቤቱ ያስፈለገው “የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት ባልተጠበቀ ሁኔታ ከሚከሰቱ እንዲሁም ተገማች ከሆኑ አደጋዎችና ፈተናዎች በመጠበቅ ረገድ ተጨማሪ ዋስትና ሊያስገኝ የሚችል አሠራር ለመዘርጋት” እንደሆነ በማቋቋሚያ አዋጁ ተጠቅሷል።
ምክር ቤቱ እንዲያከናውን በሕግ በዝርዝር የተሰጡ ተግባራት (ሥልጣን አይደለም)፤ በአጠቃላይ በብሔራዊ ደኅንነት እና በመከላከያ ፖሊሲዎች ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማማከር፣ ለደኅንነት የሥጋት ምንጭ የሆኑ ሁኔታዎች በመገምገም የእርምጃ ሐሳቦችን ማቅረብ፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት በሚነካ ጉዳይ ላይ መምከር እና የአፈጻጸም መመሪያዎችን ማመንጨት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲደነገግ በሚንስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ የሚወሰኑ ተግባሮችን ማከናውን ናቸው። እነዚህን በአዋጁ በግልጽ የተቀመጡትን የምክር ቤቱን ተግባሮች ዝርዝር ለተመለከተ ምክር ቤቱ አማካሪ፣ ሐሳብ አቅራቢ እና የሚሰጡትን ተግባራት ከማከናወን አልፎ በአንድ ኮማንድ ፖስት የማቋቋም እና ኮማንድ ፖስቱም የክልል መሠረታዊ ሥልጣን የሆነውን ጸጥታ ማስከበር ሥልጣን እንዲረከብ ለማድረግ የሚያስችለው ሕጋዊ ሥልጣን የለውም።
በፌደራል ጸጥታ አካላት የሚመራ “ኮማንድ ፖስት”?
በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት መሠረት የክልል መንግሥታት ከተሰጣቸው ሥልጣን መካከል የክልል ፖሊስ ኀይል በማደራጀት የክልል ሰላምና ጸጥታ ማስጠበቅ አንዱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራል መንግሥት የአገር መከላከያ፣ የደኅንነት እና የፌደራል ፖሊስ ኀይል የማደራጀት ሥልጣን ተሰጥቶታል። እነዚህ የፌደራል የደኅንነት እና ጸጥታ አካላት ያላቸው ሥልጣን እና ተግባር በየማቋቋሚያ አዋጆቻቸው ተዘርዝረው ይገኛሉ። ከሕገ መንግሥቱ አጠቃላይ የሥልጣን ክፍፍል መርህ መረዳት ያለብን አንድ ነገር ቢኖር የክልል ሰላም እና ጸጥታ የማስከበር ሥልጣን በበላይነት የሚመ’ራው በክልሉ በራሱ መሆኑን ነው።
በሌላ በኩል፣ ክልሎች የፌደራል መንግሥት አካል እንደመሆናቸው የክልል ሰላም እና ደኅንነት ለክልሎች ብቻ የተተወ ጉዳይ አይደለም። በሕገ መንግሥቱ በግልጽ እንደተደነገገው “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ የሀገሪቱ መከላከያ ኀይል እንዲሰማራ” ሊደረግ ይችላል። እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን መጠበቅ፣ መከላከል እና የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማስከበር የፌደራል መንግሥት ኀላፊነት እንደመሆኑ ይህንን ግዴታ ለመወጣትም ሲባል የፌደራል መንግሥት የክልሎችን ጥያቄ ሳይጠብቅ በክልሎች ጣልቃ የመግባት ሥልጣን አለው። በመጨረሻም፣ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔም የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ሊታዘዝ ይችላል።
ከላይ በተመለከቱት ሁኔታዎች የፌደራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባ ከሆነ፣ የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ (ቁ.359/1995) መሠረት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ ችግሩን ለመቆጣጠር የፌደራል ፖሊስ ወይም የመከላከያ ሠራዊት ወይም ኹለቱም እንዲሰማሩ ሊያደርግ ይችላል። በነገራችን ላይ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 51(14) መሠረት በክልል ጣልቃ እንዲገባ የተፈቀደለት የአገሪቱ መከላከያ ኀይል ብቻ ነው፤ ፌደራል ፖሊስ ይህን ማድረግ ስለመቻሉ በሕገ መንግሥቱ አልተመለከተም።
በአጠቃላይ በፌደራል መንግሥት የሚሰማራው ኀይል ችግር ባለበት ክልል ሰላም እና ደኅንነት እንዲከበር ተመጣጣኝ እርምጃዎችን እንዲወስድ በሕግ የተፈቀደለት ነው። የፌደራል ኀይል በተቻለ መጠን ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር የጸጥታ ችግሩን በመቆጣጠር ተልዕኮውን ከመፈጸም ባለፈ የአንድን ክልል ፖሊስ እና ጸጥታ አካል በሥሩ በማድረግ የክልሉን ሰላም እና ደኅንነት በበላይነት ለመምራት የሚያስችል እና በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ለክልሎች የተሰጠን ሥልጣን በጊዜያዊነትም ቢሆን ተረክቦ ለማስተዳደር የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ አግባብ የለም። በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጠው የፌደራል ሥርዓት እና ሥልጣን ክፍፍል መርህም ጋር ይጋጫል።
ማጠቃለያ
በሲዳማ ዞን የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት እርምጃዎችን መውሰዱ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው ነው፤ የተወሰደውን እርምጃ ተመጣጣኝነት በገለልተኛ አካል መመርመር እንደተጠበቀ ሆኖ። ነገር ግን መላ ክልሉ በፌደራል ጸጥታ አካል ዕዝ ሥር በሚተዳደር ኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር ሲል ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የሰጠው ውሳኔ ሕጋዊ አይደለም። ምክር ቤቱ ይህንን ለማድረግ በሕግ የተሰጠው ሥልጣን የለም።
በርግጥ ከዓላማው አንጻር ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ ተገቢ ነው ብሎ መከራከር ይቻላል፣ ነገር ግን እንደ ከዚህ በፊቶቹ ሁሉ ወይ በአዋጅ ወይም በጸጥታ አካላት ቅንጅት የክልል ጸጥታ አካላትን ባሳተፈ እና የክልሎችን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን በማይነካ መልኩ ማድርግ ይቻል ነበር።
ይህ ብቻም አይደለም፤ በአንድ ዞን በተከሰተ የጸጥታ ችግር መነሻ በመላ ክልሉ ተግባራዊ የሚሆን የኮማንድ ፖስት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነት ግልጽ አይደለም። ይህን ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊ መሠረትም የለም። እንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎች የሚኖራቸው ፖለቲካዊ አንድምታም አደገኛ ነው። ምክር ቤቱ በመግለጫው “የክልሉ መደበኛ የጸጥታ መዋቅር ሥራ ውጤታማ አይደለም … መዋቅሩም በአጀንዳዎች የተተበተበ ነው” ሲል የገለጸበት መንገድ በቅርብ ጊዜያት እየቀረቡ ያሉትን የደቡብ ክልል መንግሥት አልቦነት ክርክር የሚያጠናክር፣ የክልሉን መንግሥት ሕጋዊ ህልውናም የሚያጠይቅ እንደሆነ መገመት ይቻላል።
ማርሸት መሐመድ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው marishetm@yahoo.com ይገኛሉ።
አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011