ሦስት ፓርቲዎች የምርጫ ረቂቅ ሕግ ውይይትን ረግጠው ወጡ

0
631

በኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ሕግ ውይይትን ከተሳተፉት መካከል የሦስቱ ፓርቲ ተወካዮች ረግጠው መውጣታቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረ ገጽ ላይ የወጣው መረጃ አስታውቋል።

ሐሙስ፣ ሐምሌ 18 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ሕግ ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ ማኅበራት ተወካዮች ጋር ውይይት ባካሔደበት ወቅት በረቂቁ ሕጉ እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች አልተካተቱም፤ ሐሳቦቻችንና አስተያየቶቻችን ያልተካተቱበትን ሰነድ ለመቀበል እንቸገራለን በማለት መድረኩን ረግጠው የወጡት ፓርቲዎች የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን)፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) መሆናቸውን ከምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ፓርቲዎቹ፣ እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች ሳይካተቱ ረቂቁ ሕጉ እንዳይጸድቅ ሲሉ ቋሚ ኮሚቴውን አሳስበዋል።

ፓርቲዎቹ ውይይቱን ረግጠው እንዲወጡ ያደረጋቸው አንድ አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ቢያንስ ዐሥር ሺሕ እንዲሁም አንድ የክልል ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ ቢያንስ አራት ሺሕ አባላት እንደሚያስፈልጉ ረቂቅ ሕጉ በማካተቱ መሆኑ ታውቋል።

ሌላው በውይይቱ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ በእጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ የምርጫ ሒደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሥራ ገበታቸው በጊዜያዊነት እንደሚለቁና ደመወዝና ጥቅማ ጥቅማቸውም እንደማይከበር በሚዘረዝረው አንቀጽ 33 ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here