የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ
የዓለምን የአየር ንብረት ለውጥ ተከትሎ በርካታ ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች መመለክት የዕለት ተዕለት ተግባር መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነው። አንድ ነጥብ 4 ሚሊዮን ሕዝብ ከሚኖርባት የጃፓን ከተማ ኪዮቶ እስከ አውሮፓዊቷ ዴንማርክ ርዕሰ መዲና ኮፐንሀገን ድረስ የአየር ንብረት ለውጥንና የበካይ ጋዝ ልቀትን በተመለከተ ለመምከር የዓለም ኀያላን አገራት ያልወጡበትና ያልወረዱበት ጊዜ የለም። ምክንያቱ ደግሞ በአምራችነት ዘርፍ የዓለምን የምጣኔ ሀብት ጥግ ነክተነዋል የሚሉት ባለፀጋ አገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት በካይ ጋዝ ለከባቢ አየር ሙቀት መጨመር ትልቁን ድርሻ በመያዝ ተመልሶ ራሳቸውን በአውሎ ንፋስና በጎርፍ እንዲጥለቀለቁ ማድረጉ ነው።
ታዲያ በቅርብ ዓመታት ልዩነት እየተመላለሰ ምድርን የሚጎበኛት የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያታቸው ደግሞ በሰው ልጆች የሚተገበሩ የደን ጭፍጨፋዎች እና የበካይ ጋዝ ልቀቶች መሆናቸው ነገሩን እጅን በእጅ የመቁረጥ ያህል ያቀርበዋል። በፈረንጆች 2005 በአሜሪካ የደቡብ ምሥራቃዊ አቅጣጫ በምትገኘው ሉዚያና ግዛት ባለች ቀድሞ የባሪያ አሳዳሪ ምድር ኒው ኦርሊያንስ የተከሰተው ወጀብ አዘል አውሎ ንፋስን ማንሳት ይገባል። ይህ አውሎ ንፋስ በድንገት ከዝምተኛው ፓስፊክ ውቅያኖስ በመነሳት ነበር በሰዓት 125 ማይል እየገሰገሰ ኒው ኦርሊያንስን እንዳልነበረች በማድረግ ወደ አጎራባች ግዛቶች በማለፍ ሚሲሲፒንና አላባማን አፈር አግብቷል። ሃሪኬን ካትሪና በሚል የዳቦ ሥም የሚጠራው ይህ አውሎ ንፋስ ከአንድ ሺሕ 800 በላይ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፎ አሜሪካንም እንደ አገር 125 ቢሊዮን የሚገመት ውድመት አስከትሎ የእብደት ዛሩን አሳረገ።
የኒው ኦርሊያንሱ ከፍተኛ ውድመት አሜሪካም ከጉዳቷ ሳታገግም፤ ዓለምም ችግሩን የሰማበት ጆሮው ጭውታ ሳይሽር ከስድስት ዓመታት በኋላ በሩቅ ምሥራቋ የፀሐይ መውጫ አገር ጃፓን ይኸው አመለኛ አውሎ ንፋስ ሥሙን ሳይቀይር ሃሪኬን ካትሪና በሚል ሥያሜ ኀያል ክንዱን አሳረፈባት። እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ጉዳቱ የከፋ ነበር፤ በጃፓን ላይ የደረሰው ግን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነውና ነገሩ አውሎ ንፋሱን ተከትሎ የመጣው ጎርፍ የጃፓንን ብሔራዊ የንኩሌር ማብላያዋ ፉኩሽማን አጥለቀለቀ። በዚህ ጊዜ በዚህ ዓለም ላይ ሥጋ ለባሽን በቅፅበት በድን ሊያደርጉ የሚችሉ ጠንካራ ጨረሮች ከማብላያው አፈንግጠው በመውጣት አካባቢውን የሞት ጓዳ አድርገውት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በዚህ ጊዜ ጃፓን ከተፈጠረባት ድንጋጤ እና የምጣኑ ሀብት ድቀት ለማገገም በርካታ እርዳታዎችን ከለጋሽ እንዲሁም ከተለጋሽ አገሮችም ለመቀበል ወደ ኋላ አላለችም። ኢትዮጵያ የ 3 መቶ ሺሕ ዶላር ዕርዳታ ማድረጓም ይታወሳል። የሆነው ሆኖ ጃፓን ያፈነገጡ ጨረሮችን በጠንካራ ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር ካደረገች በኋላ ፉኩሽማን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋት ታሪክ አደረገችው።
የአየር ንብረት ለውጥ ገፅታው ይለያይ እንጂ በታዳጊ አገራትም ላይ በርካታ ችግሮችን እያስከተለ ከዘመን ዘመን የማይሻሻለውን የኑሮ ዑደት ሲያባብሰው ይገኛል። በተለይ ደግሞ በአገራችን ኢትዮጵያ በየዐሥር ዓመታት ልዩነት ብቅ እያለ ከቁም እንስሳት እስከ ሰብኣዊ ፍጡር ፈጅቶ የሚሔደውን የኤሊኖ የአየር ንብረት ለውጥ ማየት ብቻ በቂ ነው። ከምሥራቅ ሕንድ ውቅያኖስ በሚነሳ ደረቅ ንፋስ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ የሚለው ኤሊኖ በኢትዮጵያ ያለው የተመናመነ የደን ሽፋን ለሚያደርሰው ጉዳት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርለት በአየር ንብረት ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ምሁራን አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
የደን ሽፋን በኢትዮጵያ
በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያሳተሙ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በከፍተኛ ተመራማሪነት የሚያገለግሉት ዩሐንስ አበራ (ዶ/ር) ሲያብራሩ የትኛውም ዓይነት ንፋስ ወደ አገራችን በሚነፍስበት ጊዜ የራሱ የሆነ አሉታዊ እና አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖሩት ተናግረው ነገር ግን በንፋሳቱ መዳረሻዎች ላይ የሚኖረው የደን ሽፋን ግን የሚደርሰውን ጉዳት ከመቀነስ ብሎም ከመከላከል አኳያ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ። ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ከዓመት ዓመት የሚከሰተው ድርቅ መንስኤው የደን መመናመን እንደሆነም አልሸሸጉም። ስለሆነም ደረቃማ ንፋሳት ወደ ኢትዮጵያ ሲነፍሱ መቆጣጠር በማይቻልበት ደረጃ ድርቅ የሚከሰተው ሲሉ ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ጥናት እንደሚያመለክተው ከአገሪቱ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት ውስጥ 4 በመቶ የሚሆነው በደን የተሸፈን መሆኑን ቢጠቁሙም በርካቶች ግን ከዚህ የተለየ አስተያየትና ቁጥሩ ከ3 በመቶም ዝቅ ሊል እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ የአካባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንየደን ሽፋኑን በሚመለከት ለአዲስ ማለዳ ማብራሪያ ሲሰጥ፤ 4 በመቶ የሚለው መረጃ በደጋማው የአገሪቱ ክፍል ያለው እና የተፈጥሮ ደን የሚባለው ብቻ ተቆጥሮ መሆኑን በመግለፅ ይጀምራል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ተስፋዬ ጋሻው በቆላማ እና በወይና ደጋማ አካባቢዎች ያሉትን የተፈጥሮ ደን ሽፋኖችን ማዕከል ያደረገ እንዳልሁነ ጠቁመው የቆላ ደን የሚባለው ደግሞ 15 በመቶ ሽፋን እንዳለው ጠቁመዋል። በቆላማ አካባቢዎች ባለው የደን ሽፋን ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የጋምቤላ ክልል እንደሆነም ኀላፊው ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ። ጌታቸው አያይዘው የአገሪቱ የደን ሽፋን በለፉት ዓመታት በርካታ የስህተት መረጃዎች ለሕዝቡ እየደረሱ የነበረበት ጊዜ እንደሆነና በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ጥናት ተደርጎበት ለሕዝብ ፍጆታ እንዲውል መደረግ እንዳለበት ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ከተፈጥሮ ደን በተጨማሪ በግለሰብ፣ በማኅበር እንዲሁም በመሥሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ደረጃ በጋራ እና በተናጠል የሚተከሉት ችግኞች ለአገሪቱ የደን ሽፋን ዋነኛ አዎንታዊ ምክንያቶች ናቸው። በዚህ ረገድ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ አገራዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች እና መነሳሳቶች ታይተዋል። ይሁን እንጂ የችግኝ ተከላዎች በተካሔዱበት ፍጥነት ግን አገራዊ የደን ሽፋኑ የሚፈለገውን ያህል እመርታ እንዳላሳየ ብዙኀኑ የሚስማማበት ጉዳይ ነው። ከቅርብ ጊዜው አገራዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ብንነሳ ከ12 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የኹለተኛው ሺሕ ዓመታት አገባዳ የሦስተኛውን ሺሕ ዓመታት ለመቀበል ሽር ጉድ በምትልበት ዋዜማ “ኹለት ዛፍ ለኹለት ሺሕ” በሚል መሪ ቃል አገራዊ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህ የችግኝ ተከላ ወቅትም 60 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል እንደተቻለ አዲስ ማለዳ ከአካባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
እንደ ኮሚሽኑ ገለፃ በቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለ ማሪያም ደሳለኝ የተጀመረ በብሔራዊ ደረጃ የሚተገበር የችግኝ ተከላ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል። በዚህም የተነሳ ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጀምሮ ኮሚሽኑ በዓመት አንድ ሚሊዮን ሔክታር የሚሆን መሬት በደን ለመሸፈን አቅዶ ይንቀሳቀስ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ይህንም ለማሳካት በርካታ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያዘጋጅና እስካሁንም በታሰበው መንገድ እየተሔደ እንደሆነም ታውቋል። አንድ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ 5 ሚሊዮን ሔክታር በደን እንደሚሸፈን ዕቅድ ይዘው እንደሚንቀሳቀሱም ተጠቁሟል።
“4 ቢሊዮን በአንድ ክረምት፥ 200 ሚሊዮን በአንድ ጀንበር” ችግኝ ተከላ
በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትልቅን ተስፋ ሰንቀው ባስጀመሩት የ4 ቢሊዮን ብሔራዊ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዚህ መርሃ ግብር ታዲያ አንድ ግለሰብ በነፍስ ወከፍ 40 ችግኞችን የመትከል ኀላፊነት እንደሚኖረው ተነግሯል። የዚሁ የ4 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ አካል የሆነው እና ሐምሌ 22/2011 “አረንጓዴ አሻራ” በሚል መሪ ቃል የሚካሔደው የ200 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከፍተኛ ግምት ተጥሎበታል። በዚህ መርሃ ግብር ላይ ከኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተወጣጡ ግለሰቦች ተሳታፊ እንደሚሆኑና ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸውን ተቆርቋሪነት ያሳያሉ ተብሏል።
ይሁን እንጂ ዩሐንስ አበራ (ዶ/ር) በዚህ መርሃ ግብር ላይ አንድ ጥርጣሬ አላቸው። “ከዚህ በፊት በርካታ አገራዊ መነቃቃቶች ውጤታቸው ሳይታወቅ ተድበስብሰው ነው የቀሩት” ሲሉ ጥርጣሬ የተቀላቀለበት ሥጋታቸውን ገልጸዋል። ችግኞቹ ጸድቀውና አድገው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ካልተደረገ ፋይዳ የለውም ያለት ዩሐንስ፥ ኅብረተሰቡ ለመትከል ያሳየውን ተነሳሽነት በመንከባከቡም ላይ መድገም እንደሚገባው አመላክተዋል።
የአንድ ዓመት ጊዜ ገደብ የተያዘለት የ4 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ከቀደሙት አገራዊ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴዎች ለየት የሚያደርገው ግለሰቦችም ሆኑ ማኅበራት እንዲሁም ሌሎች አካላት ችግኞችን ከተከሉ በኋላ የመንከባከብ ኀላፊነት እንዳለባቸው የሚያሳስብ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። ስለዚህ ጉዳይ የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዱ፤ ችግኝ የሚተክሉ አካላት ግለሰቦችም ሊሆኑ ይችላሉ ማኅበራት የችግኝ መትከያ ሥፍራ ከሰጣቸው የመንግሥት አካል ጋር ሕጋዊ ውል እንደሚፈራረሙና የተከሏቸውን ችግኞች የመንከባከብ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ አካል እንደሚኖር አስታውቀዋል።
በቀጣይም መንግሥት የችግኝ ተከላውን ወደ ንግድ የማዘዋወር አቅጣጫን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች። በዚህም አካሔድ እንጨቶችንና እንጨት ውጤቶችን ለገበያ የሚያቀርቡ ትላልቅ ኩባንያዎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉና ለሚገጥማቸው የገበያ ፍላጎትን ለማርካት በሚቆርጧቸው ዛፎች ቦታ እጥፍ ቁጥር ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ የችግኝ ተከላውን ወደ ኢንዱስትሪ ከፍ ለማድረግ የአጭር ጊዜ ዕቅድ እንደሆነ ታውቋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች እስከ ሱዳን ድረስ የሚዘልቅ ከፍተኛ የባሕር ዛፍ ንግድ እንዳለ እና አርሶ አደሮች አርሰው ከሚያገኙት እና ምርቱን ለሽያጭ አቅርበው ከሚያገኙት በበለጠ ገቢ እያገኙ እንደሆነ ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
እንደ አካባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት ብቅ ብለው በሕዝቡ ዘንድ የችግኝ ተከላውን እንቅስቃሴ አነቃንቀው የከሰሙት ዘመቻዎች በርካታ ችግኞች እንዲተከሉ የተደረጉበት ነበር። በዚህም ረገድ በአገር ዐቀፍ ደረጃ በአማካኝ የተተከሉት ችግኞች የመጽደቅ ዕድላቸው 70 በመቶ እንደሆነ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከእንክብካቤ እጥረት እና ከሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ቀሪ 30 በመቶ ችግኞች መጽደቅ እንዳልቻሉ እንዲሁም 30 በመቶ ውስጥ ተተክለው ሳይደርቁ ግን ቀንጭረው የተገኙ አብረው በመመደባቸው እንደብክነት እንደሚቆጠሩም ለማወቅ ተችሏል።
ከዚሁ በተመሳሳይ ደግሞ የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስቴር እንደሚገልፀው ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ የደን ሽፋኗ እየተመናመነ እንደሚገኝና ይህንም ለመመለስ ሚኒስቴሩ ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል። በዚህም ረገድ ግብርና ሚኒስቴር በ2038 የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተራቆተው መሬት ውስጥ 22 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነውን በደን ለማልበስ ትልቅ ህልም ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ተጠቁሟል።
የግብርና ሚንስትር ዲኤታ ሳኒ ረዲ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ መንግሥት በዋናነት የግብርና መር ደን ጥበቃን ወይም “አግሮ ፎረስትሪ”ን እንደሚያበረታታና ይህም አካሔድ በርካታ ተጠቀሚታዎችን እያስገኘ እንደሆነ ጠቁመዋል። አያይዘውም በችግኝ ተከላው ረገድም ቢሆን አመርቂ ሊባል የሚችል አካሔድ ቢኖርም ነገር ግን ከዛው በበለጠ ደግሞ የደን ጭፍጨፋው ከልክ ያለፈ እንደሆነ ጠቁመዋል። “በእርግጥ ዛፎች ተተክለው ለጥቅም ሊውሉ ይገባል፤ ነገር ግን በተቆረጡት ፋንታ መትከል ይኖርብናል። በዚህም መሰረት አንድ ዛፍ ሰው ሲቆርጥ ኹለት ችግኝ መትከል ይኖርበታል” በማለት አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሚተከሉት ችግኞች የሚተከሉበት አካባቢን ያላማከሉ መሆናቸው ላለመጽደቃቸው እንደምክንያት እንደሚወስዱትም ሳኑ ረዲ ያስረዳሉ። “ችግኞች ሲተከሉ የአካባቢው የአየር ሁኔታ፣ በአካባቢው ያሉ እንስሳት አመጋገብ እንዲሁም አስፈላጊው ጥበቃ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው” ሲሉ አብራርተው የበረሃማ አካባቢ ተክሎችን በደጋ ቦታ መትከል ማባከን እንደሆነ ጠቁመዋል። አያይዘውም ሚኒስቴር ዲኤታው በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው አገር በቀል ዛፎች የሚተከሉ ሲሆን የውጭ አገር ዝርያዎችም በስብጥር እንደሚተከሉ አስታውቀዋል። በዚህም ረገድ በ4 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ውስጥ ‘አኬዢያ ዲከረንስ’፣ የፈረንጅ ጽድ፣ የሐበሻ ጽድ፣ ወይራ፣ ግራር እና መሰል ችግኞች እንደሚተከሉ ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ይፋ ባደረጉት የ4 ቢሊዮን ችግኝ ተከላን መሰረት አድርገው ለሕዝብ እንደራሴዎች ንግግር ባደረጉበት ወቅት ጠቀሜታውን አስረድተው ነበር። “ችግኝ በመትከል ዓመቱን ሙሉ ዝናብ ማግኘት እችላለን” ሲሉም ተደምጠዋል። አገሪቱ ወቅታዊ ዝናብን ተመርኩዛ ያለች በመሆኗ እና የዝናብ መጠን በቀነሰ ቁጥር ከኀይል ማመንጫዎች እስከ ግብርናው ድረስ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንደሚወድቅ ተናግረው ነበር። ለኀይል ማመንጫነት ውሃን የምትጠቀመው ኢትዮጵያ የተለየ እና የተሻለ አማራጭ እስከትጠቀም ድረስ ችግኝ በመትከል መጀመሪያ በውሃ እጦት የሚከሰተውን የኀይል መቆራረጥ በተጓዳኝም ደግሞ በየጊዜው ዓመታትን እየቆጠረ የሚጎበኘውን ድርቅ እስከ ወዲያኛው ማሰናበት ለነገ የሚባል ሥራ እንዳልሆነ ማስረገጣቸው የሚታወስ ነው።
የአየር ንብረት ምሁሩ ዩሐንስ አበራ በ2016 በዓለም የምግብ ድርጅት ይፋ የሆነውን የጥናት ውጤት አንስተው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ ከ1982 እስከ 2002 ባሉት ኻያ ዓመታት ውስጥ 18 በመቶ የደን ሽፋን መውደሙን ገልፀዋል። ይህንም ተከትሎ 2 ነጥብ 8 ሔክታር መሬት መራቆቱን ጠቁመዋል።
ዩሐንስ ቀጥለውም 219 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርቦን መጠን በአሁኑ ሰዓት ባለው የደን ክምችት ውስጥ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ሙያዊ አስተያየታቸውን ሲያስቀምጡም፥ የችግኝ መተከል ምንም ወደ ኋላ የሚባልበት ጉዳይ እንዳልሆነና ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠኑ እየቀነሰ የመጣውን የከርሰ ምድር ውሃንም ከመጠበቅ አንጻር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አስታውቀዋል። ለዚህ ደግሞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዓለም ከተማ የሚገኘውን የጓሳ ሳር አንስተው “ለዘመናት ውሃን በውስጡ አከማችቶ በመያዙ አካባቢው በከርሰ ምድር ውሃ ሀብቱ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ዩሐንስ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 125 ሺሕ 400 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ያህል እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ በማጠቃለያ ሐሳባቸው ጠቁመዋል።
አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011