አንዳንዶች ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የተሰጠው የአንድ ዓመት ማራዘሚያ ጊዜ ተጠናቋል ይላሉ። እስካሁንም ከመንግሥት የምክር ቤት ምርጫ ስለማድረግ አሊያም የምክር ቤቱን የሥራ ዘመን ስለማራዘም በይፋ የተነገረ ነገር የለም። የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ካልተራዘመ ታከለ ዑማ ምክትል ከንቲባ ሆነው መቀጠል የሚያስችላቸው ሕጋዊ መሰረት አይኖራቸውም የሚሉ ወገኖች የመኖራቸውን ያክል፥ የከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊነት በሰኔ 30/2011 ተጠናቋል የሚባለው ሐሰት ነው፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቁርጥ ቀነ ገደብ አላስቀመጠም የሚሉም አሉ። በዚህ ዙሪያ ሕጉ ምን ይላል? ቀጣዩስ የአስተዳደሩ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ ይመለከታቸዋል ያላቸውን ባለሙያዎችንና የአስተዳደሩን ሹማምንት በማነጋገር ርዕሰ ጉዳዩን በሐተታ ዘ ማለዳ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕጋዊነት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1995 የወጣውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደር መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ መጋቢት 2010 በኋላ በወራት ልዩነት የከተማውን ቻርትር አዋጅ ማሻሻሉ ይታወሳል። የቀደመው የከተማ አስተዳደሩ ቻርተር አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 1094/2010 ተተክቷል።
በቀድሞ አሠራር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባና ምክትል ከንቲባ ሆኖ ለመሾም የከተማው ምክር ቤት አባል መሆን ይጠበቅበት ነበር፤ በአዲሱ አዋጅ ይህ መስፈርት ማሻሻያ ተደርጎበታል። በዚህም መሰረት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አንቀጽ 14 ላይ ማሻሻያ በማድረግ የከተማው ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤት ውጪ መሾም እንዲችል ተፈቅዷል። በመሆኑም በተሻሻለው የከተማው ቻርተር መሰረት ታከለ ዑማን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ካለፈው የከተማና የአካባቢ ምርጫ በኋላ የሥራ ዘመኑ ተጠናቆ፣ በ2010 በወቅቱ በአገሪቱ ምርጫ ለማካሔድ አልተቻለም በሚል፣ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ለአንድ ዓመት እንዲራዘም መደረጉ ይታወቃል። ይህ የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክሮበትና አምኖበት ነው።
ይሁን እንጂ የምክር ቤቱ ውሳኔዎች ሕጋዊ አግባብነት የላቸውም የሚሉ ጥያቄዎችና ቅሬታዎችም አስነስቷል። ምክር ቤቱም ሆነ አጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊ ዕውቅና ኖሮት ከተማዋን ሊያስተዳድር አይችልም የሚሉም አካላት አሉ።
ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ ከተማ የባላደራ ምክር ቤት የሥራ አሥፈጻሚ አባል እና በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት ሄኖክ አክሊሉ አንዱ ናቸው። የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 (2) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል የሚለውን አንቀጽና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 365/1995 በማስታወስ፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው አስተዳደር የተቀመጠለትን የሕግ ማዕቀፍ መሰረት ያላደረገ ነው በማለት ሄኖክ ይከራከራሉ።
አዲስ አበባ ላይ የሚመረጥ መንግሥት አምስት ዓመት የሥራ ዘመን እንዳለው በግልጽ መቀመጡን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ሄኖክ፣ የከተማው ሥራ አስፈጻሚ አካል፤ የከንቲባ ጽሕፈት ቤቱን ጨምሮ የሥራ ዘመናቸው አምስት ዓመት መሆኑን ያወሳሉ።
እንደ ሄኖክ ገለጻ፣ ምክር ቤቱ ባለፈው 2010 የአምስት ዓመት የሥራ ዘመኑን ጨርሷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያራዘመውንም የአንድ ዓመት ጊዜም አብቅቷል። ስለዚህ ከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን እንዲያስተዳድር የተፈቀደለት የጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ ተቀባይነት የላቸውም ባይ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አበበች ነጋሽ ግን በሄኖክ ሐሳብ አይስማሙም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 365/1995ን ማሻሻል በማስፈለጉ ከአንድ ዓመት በፊት በአዋጅ ቁጥር 1094/2010 እንደተሻሻለ አስታውሰው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑን ተከትሎ፤ ምርጫ ተደርጐ በምርጫው መሠረት አዲስ አስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤት እና አጠቃላይ የከተማው አስተዳደር በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል ሲል ማወጁን ያስረዳሉ።
የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 1094/2010 የከተማ አስተዳደሩና ምክር ቤት በሥራ ላይ የሚቆይበትን ቀነ ገደብ እንዳላስቀመጠ የሚያወሱት አበበች፤ የማሻሻያ አዋጁ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤት አባል ውጪ እንዲሾም የሚፈቅድ ስለመሆኑም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትና የከተማው አስተዳደር የሥልጣን ዘመን አብቅቷል በማለት የሚነገሩት አሉባልታዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን በማስረዳት፣ በአንዳንድ ሰዎች ፍላጎት ወሬው እንዲስፋፋ መደረጉንም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) አበበች ተሳስተዋል ይላሉ። እንደ ሲሳይ ገለጻ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ምርጫውን ሲያራዝም፣ ለአንድ ዓመት አራዝሜያለሁ አለ እንጂ ላልተወሰነ ጊዜ አላለም። አንድ ዓመት ማለት ደግሞ ገደብ እንዳስቀመጠለት ማሳያ አሁን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የተሰጠው የአንድ ዓመት ማራዘሚያ ተጠናቋል። የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን የማይራዘም ከሆነ፣ ታከለ ዑማ ምክትል ከንቲባ ሆነው መቀጠል የሚያስችላቸው ሕጋዊ መሰረት አይኖራቸውም። ከሰኔ 30 በኋላ ሌላ የማራዘሚያ ውሳኔ እስካልተወሰነ ድረስ፣ የከንቲባው ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል ማለት ነው።
ሲሳይ እንደሚሉት፣ የተሻሻለው ቻርተር ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤት ውጪ እንዲሾም ፈቀደ እንጂ፣ የምክር ቤቱን የመሾምና ሹመቱን የማጽደቅ ሥልጣንን አልነጠቀም። ስለዚህ ታከለ ዑማ የምክር ቤቱ ሥልጣን ካልተራዘመ በሥራ ላይ ሊቆዩ አይችሉም ብለዋል።
አዋጅ ቁጥር 1094/2010 ምን ይላል?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫን ላልተወሰነ ጊዜ ያራዘመውና የአዲስ አበባ ምክር ቤትም ባለበት እንዲቀጥል የወሰነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 365/1995ን በአዋጅ ቁጥር 1094/2010 በማሻሻል ነው። በዚህ አዋጅ ላይ ከሚነሱት አወዛጋቢ ክርክሮች መካከል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ አስተዳደሩን የሥራ ዘመን የማራዘም ሥልጣን አለው ወይ የሚለው ይገኝበታል።
ይህንን ጥያቄ ከሚያነሱት ሰዎች መካከል አንዱ ሄኖክ ናቸው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ አስተዳደሩን የሥራ ዘመን የማራዘም መብት ሳይኖረው፣ በዚህ አዋጅ አማካኝነት የከተማ አስተዳደሩን የሥራ ዘመን እንዲራዘም መደረጉ አሁን ያለው የከተማው አስተዳደርና ምክር ቤት የሕግ አግባብነት እንደሌለው ማሳያ ነው ሲሉ ጠበቃው ይሞግታሉ ይሞግታሉ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባን ምክር ቤት የሥራ ዘመን የማራዘም መብት የለውም ሲሉም የመከራከሪያ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ።
በአዋጁ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሥራ ዘመንን ያራዝማል በሚል የተጠቀሰ ቦታ የለም የሚሉት ሄኖክ፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ 49 (2) ከተማ አስተዳደሩ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል፤ ዝርዝሩም በሕግ ይወሰናል የሚል ሐሳብ መያዙንም ይገልጻሉ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትን የሥራ ዘመን ማራዘም አይችልም፤ እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 1094/2010 ሕጋዊ አግባብነት የለውም በሚለው ሐሳብ የማይስማሙት አበበች፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1094/2010 ማጽደቅ አይችልም ከተባለ፤ “በዚህ ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም። እኛ ግን አዋጁን በሕጋዊ መንገድ ተግባራዊ እያደረግን ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
የሕግ ባለሙያ የሆኑት ኤፍሬም ታምራት ለቢቢሲ አማርኛ በሰጡት ምላሽ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን ማራዘም እንደሚችል ያስረዳሉ።
ኤፍሬም ሲገልጹ፣ “በሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ 49 ሥር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግሥት መሆኑና የከተማ አስተዳደሩ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን ለመደንገግ ዝርዝር ሕግ ይወጣል ይላል። ዝርዝር ሕግ ተብሎ ከተጠቀሰው መካከል አንዱ ቻርተሩ ነው። በቻርተሩ ላይ ደግሞ በግልጽ የፌደራሉ መንግሥት በራሱ አነሳሽነት ቻርተሩን ሊያሻሽለው እንደሚችል ተገልጿል።”
የከተማ መስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 365/1995 ያወጣው የፌደራል መንግሥቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል መንግሥቱ አንደኛ አካል ነው ይላሉ ኤፍሬም።
አክለውም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥቱ ነው ሲባል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ይመለከታል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ሥልጣን የተቀዳለት ከፌደራል መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ የከተማ አስተዳደሩን የሥራ ዘመን ሊያራዝም እንደሚችልም በአፅንዖት ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን መቼ ይጠናቀቃል?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2010 ያሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አንቀጽ 15 (2) ሥር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ጊዜ እንዲራዘም የወሰነ እንደሆነ፣ ምርጫ ተደርጎ በምርጫው መሠረት አዲስ አስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤት እና አጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩ በነበረበት ይቀጥላል ይላል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተርን ባሻሸለበት አዋጅ የከተማው ምክር ቤትን ምርጫ ከማራዘሙ በተጨማሪ፤ ምርጫ ተደርጐ አዲስ አስተዳደር እስኪደራጅ ድረስ በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤትና አጠቃላይ የከተማው አስተዳደር በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል ብሏል።
አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ምክር ቤት ባገኘችው መረጃ መሰረት፣ የከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊነት በሰኔ 30/2011 ተጠናቋል የሚባለው ሐሰት ነው፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለምርጫው የጊዜ ገደብ አላስቀመጠም ብለዋል።
የአስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን ከተጠናቀቀ ከአንድ ዓመት በላይ ቢሆነውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሻሻለው ቻርተር ላይ የጊዜ ገደብ ባለማስቀመጡ፤ ምርጫ እስከሚካሔድ ድረስ አስተዳደሩ ከተማዋን መምራቱን እንደሚቀጥል የከንቲባው ፕረስ ሴክሬታሪያት ፌቨን ተሾመ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን እንዲያደርግ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጣለት መመሪያ እንደሌለም ፌቨን ተናግረዋል።
የከተማው ምክር ቤትን የሥራ ዘመን በድጋሜ በሕግ ማራዘም ግን ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ምንጮቻችን አፅንዖት ሰጥተው ነግረውናል። ይህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ለእረፍት ከተበተነበት ለአስቸኳይ ስብሰባ መጥራት ሊያስፈልግ ይችላል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ መቼ ይካሔዳል?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለው ነባራዊ ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምርጫን ማካሔድ አይቻልም በማለት ምርጫው በ2011 ላይ እንዲካሔድ ማራዘሙ ይታወቃል። በውሳኔው መሰረትም ዓመቱ ሳይጠናቀቅ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ሊያከናውን እንደሚችል ሲጠበቅ ነበር። ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ምርጫ ማካሔድ እንደማይችል አስታውቋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሶሊያና ሽመልስ፤ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደታሰበው ምርጫውን ማካሔድ እንደማይችል ተጠቅሶ ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት በደብዳቤ አሳውቋል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ “የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤቶች ምርጫን ጨምሮ የአካባቢ ምርጫን ለማከናወን የሚያስፈልጉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላና ሥልጠና ለመስጠት፣ ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎችን በየክልሉ በተዋረድ አጠናቆ ለማስፈጸም ጊዜ አለመኖሩንና ዓመቱ እየተጠናቀቀ በመምጣቱ ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ደብዳቤ ተልኳል” ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ መውጫ
ሲሳይ እንደሚሉት፣ መፍትሄ የሚሆነው አንድም ፓርላማው እንደገና ተጠርቶ አሁንም ተጨማሪ የማራዘሚያ ጊዜ መስጠትና ሥራውን እንዲሠራ ማድረግ፣ ካልሆነም ባለአደራ ማቋቋም ሌላው አማራጭ ነው የሚሆነው። ይሄንንም መወሰን የሚችለው የተወካዮች ምክር ቤት ነው። ምን መሆን አለበት የሚለውን እንዲወስን የሕዝብ
ተወካዮች ምክር ቤት ዕድሉን ማግኘት አለበት፤ ምክር ቤቱ እንዲወስን ደግሞ ጥያቄው ሊቀርብለት የሚገባው ከአስፈጻሚው አካል ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት ያለ አይመስልም። ጊዜውን ዳግመኛ አለማራዘሙ ስህተት ነው።
በአሁኑ ወቅት ያለው የከተማዋ አስተዳደር የሥልጣን ዘመኑ አብቅቷል አላበቃም መቋጫ ባይበጅለትም የከንቲባውና የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ጉዳይ አሁንም እያነጋገረ ይገኛል። ይሁንና ምርጫ ለማካሔድና በሕዝብ የተመረጠ አስተዳደር ለማቋቋም አመቺ ሁኔታዎች እንደሌሉ እየተገለጸ ነው።
ለዚህ ደግሞ በ2012 ይደረጋል ተብሎ የሚታሰበውን አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ መጠበቅ የግድ ሳይሆን አይቀርም የሚሉም አልጠፉም። ይህ ደግሞ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ከተቀረው የአገሪቱ ክፍሎች ምርጫ ተነጥሎ ለብቻው ሲካሔድ የነበረውን የአዲስ አበባ ምርጫ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
“የሥራ ዘመኑ ካለፈ መፍትሔ የሚሆነው ምርጫ ማካሄድ ነው። ምርጫ ማካሐየድ የማይቻል ከሆነ ኅብረተሰቡ የእኔ ናቸው የሚላቸውንና የሚያከብራቸውን ወደ ሥልጣን ማምጣት ነው” በማለት ሄኖክ አስረግጠው ይናገራሉ።
ሄኖክ በቅድሚያ ባላደራ ምክር ቤትን ማቋቋም ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ “ገፊ የሆኑ ወቅታዊ ሁኔታዎች ይገኙበታል” ይላሉ።
ሄኖክ ለባላደራ ምክር ቤት መቋቋም ወቅታዊ ጉዳዮች ናቸው ከሚሏቸው መካከል፣ አሁን ያለው አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የከተማውን ነዋሪ ባገለለ ሁኔታ የጥቂት ሰዎችን ፍላጎት ለማሳካት እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል የሚለው ይገኝበታል። ሌላው፣ እስከታችኛው የሥልጣን እርከን ድረስ አንድ አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎችን ብቻ ወደ ሥልጣን ያመጣል የሚሉ ምክንያቶች እና ከተማዋን እያስተዳደረ ያለው አካል ሕጋዊ ዕውቅና የለውም የሚሉት ምክንያቶች ለባልደራስ ምክር ቤት መፈጠር ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።
ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቼ ሰማሁ ብሎ ባቀረበው ዘገባ ላይ ደግሞ፣ የሥልጣን ጊዜው ተጠናቆ ለአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ በሥልጣን ላይ የቆየውን የአዲስ አበባ አስተዳደር አሁንም ለተጨማሪ ጊዜ በሥልጣን እንዲቆይ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል። ለምን ያህል ጊዜና በምን የሕግ ማዕቀፍ የሚለውን ግን እስካሁን ጥርት ያለ ምላሽ አላገኘም ሲል ዘግቧል።
የሕግ ትርጓሜ ክፍተትን ተጠቅሞ የአስተዳደሩን ሕጋዊ አድርጎ ማቆየት አስቸጋሪ መሆኑን ምክረ ሐሳብ ያቀረቡ ባለሙያዎች መኖራቸውና ጉዳዩ ላይ ተከታታይ ምክክሮች ተደርገው እንደነበር ዋዜማ ሬዲዮ በዘገባው ላይ አስፍሯል።
የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን የማይራዘም ከሆነ ምርጫ በቅርቡ ይካሔዳል ተብሎ ስለማይታሰብ የከተማዋ ዕጣ ፈንታ በባለአደራ አስተዳደር መቀጠል ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው የነገሩንም አሉ ሲል ምንጮቹን ዋቢ አድርጓል።
አዲስ አበባ አመሰራረትና ከንቲባዎቿ
አዲስ አበባ በዳግማዊ አፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት በእቴጌ ጣይቱ ብጡል በ1879 እንደተመሰረተችና መጠሪያ ሥሟን እንዳገኘች በታሪክ ተመዝግቧል። የከተማዋ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እና የቆዳ ስፋት እያደገ መምጣት፣ እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ባለጉዳዮችን በአግባቡ ለማስተናገድ በማስፈለጉ በ1909 የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት መቋቋሙን ዊክፒዲያ ድህረ ገጽ አስታውቋል።
በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የአዲስ አበባን ዘመናዊነት እንቅስቃሴዎች ዘላቂ ልማት ያሸጋገረበት ጊዜ ነበር። የማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ከተቋቋመም በኋላ፣ ሊሎ ሽፋኑ በተባለ ፈንረሳዊ እና አድለቢ በተባለ ሶሪያዊ ግፊት ማዘጋጃ ቤቱ አድዋ ሲኒማ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ እንዲመሰረት ተደረገ። ማዘጋጃ ቤቱም የከተማው “የማኅበር ቤት” ተብሎ ይጠራ ነበር።
ይህ ሥያሜ የተሰጠውም ማዘጋጃ ቤቱ እንዲመሰረት ግፊት ሲያደርጉ በነበሩት በሶሪያው እድሊቢ ነው። ቀድሞ “የከተማ ማኅበር ቤት” የሚለው ሥያሜ municipality የሚለው የእግንሊዘኛ ቃል አዲስ አበባን አይወክልም በሚል፣ በህሩይ ወልደ ሥላሴ አማካኝነት በ1920 ማዘጋጃ ቤት የሚል ሥያሜ እንደተሰጠው በታሪክ ሰፍሯል። በወቅቱ ለአዲስ አበባ ከተማ ዕድገትና ለከተማዋ ሕዝብ ደኅንነት ሲባል በ1926 የሚያከናውናቸውን ተግባራት በ16 ዋና ዋና ክፍሎች ከ250 ባልበለጡ ሠራተኞች የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት
ሥራውን ያከናውን ነበር።
የሥራ ክፍሎቹም የከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የርስት ክፍል፣ የካርታ ማንሳትና የግምት ክፍል፣ የዳኝነት ክፍል፣ የአራዳ ዘበኛ የተሽከርካሪና የመንጃ ፈቃድ (የቁማር ጨዋታ ቁጥጥር ክፍልን ጨምሮ)፣ የጽዳት ክፍል የገንዘብና የሥራ መቆጣጠሪያ ክፍል፣ የምስጢር ክፍል፣ የሕክምና ክፍል (ልዩ ጓዳ)፣ የውል ክፍል፣ የእሳትና አደጋ መከላከል ክፍልና የጋራዥ ክፍል የተባሉት ነበሩ። እነዚህ የሥራ ክፍሎች ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ እያንዳንዱ ክፍል ንዑስ ቅርንጫፎች ነበሩት። ማዘጋጃ ቤቱ ከላይ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ክፍሎች ይኑሩት እንጅ ለከተማዋ ዕድገት የነበረው አስተዋጾዖ አመርቂ እንዳልነበር የተለያዩ ጽሁፎች ያስረዳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ የመጣውን የነዋሪዎች ችግር ለማሻሻል እና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀት እና ሕንጻ በማስፈለጉ ዛሬ በማገልገል ላይ የሚገኘውን ማዘጋጃ ቤት ሕንጻ እንዲገነባ ተወሰነ።
አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011