ሂጅራ ባንክ አራት በመቋቋም ላይ የነበሩ ባንኮችን ጠቀለለ

0
1401

ከአንድ ወር ተኩል በፊት ሼር ለመሸጥ ፍቃድ ያገኘው ሂጅራ ከወለድ ነጻ ባንክ በአዲስ አበባ ባለሀብቶች እና ዱባይ ባሉ ኢትዮጵያዊያን በመመስረት ላይ የነበረውን ሰላም ባንክን ጨምሮ ሌሎች አራት ቡድኖች ጋር እንደተዋሐደ አስታወቀ።

ሰላም ባንክ ሥያሜውን ጨምሮ ሌሎች የሰነድ ሥራዎችን አጠናቆ ለምዝገባ ወደ ብሔራዊ ባንክ መሔድ ብቻ ሲቀረው ዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት ላይ ነው ከሂጅራ ባንክ ጋር በመዋሐድ ለመሥራት ስምምነት ላይ የደረሰው። በተጨማሪም በአማራ ክልል ባለሀብቶች፣ በተለይም በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ እና በመንገድ ግንባታ ላይ ተሰማርተው ባሉ ባለሀብቶች ለመመስረት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ የነበረ አንድ ቡድንም ባንኩን ለመቀላቀል መቻሉን የሂጅራ ባንክ የግንኙነት አስተባባሪ አሕመዲን ጀበል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሐረር አካባቢ ጥናት በማካሔድ ላይ የነበረ ቡድንም ሂጅራን ከተቀላቀሉት መካከል ሲሆን ውሕደቱም ሰፊ አገራዊ ተደራሽነትን ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የባንኩ አደራጆች ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ተናግራዋል።

“ጥቂት የአዲስ አበባ ሀብታመች የመሰረቱት እና የነእከሌ ባንክ የሚባል ባንክ ሳይሆን በትክክልም የሕዝብ ባንክ መመስረት ዓላማችን ነው” ያሉት የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አህባቡ አብደላ አክለውም “ምንም እንኳን የብሔራዊ ባንክ የአንድ ሰው ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ ከባንኩ ካፒታል እስከ 5 በመቶ ቢፈቅድም እኛ ግን ጥቂቶች የበላይነት እንዳይኖራቸው ዝቅተኛውን 2 በመቶ በመውሰድ ጣሪያ እንዲሆን ተስማምተናል” ብለዋል።

የአክሲዮን ሺያጩም እሁድ፣ ሐምሌ 14/2011 በጎልፍ ክለብ የእሰልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት እና የዑለሞች ምክር ቤት ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ በተገኙበት በችግኝ ተከላ የተጀመረ ሲሆን ከሰኞ፣ ሐምሌ 15/2011 ጀምሮም በ 11 ባንኮች የአክሲዮን ሽያጭ በመካሔድ ላይ መሆኑንም የባንኩ አደራጆች ተናግረዋል። የአንድ አክሲዮን ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ሲሆን አንድ ሰው እስከ 30 አክሲዮን በአንድ ጊዜ መግዛት ይችላል። በአንድ ጊዜም አንድ ሰው ለመግዛት ከወሰነው የአክሲዮን መጠን ላይ 50 በመቶውን የመክፈል ግዴታ ያለበት ሲሆን ጠቅላላ ሊገዛ ቃል የገባውን አክሲዮን ዋጋ 5 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ እንደሚፈፅምም ታውቋል።

“የአክሲዮን ሺያጩ ዝቅተኛው ማኅበረሰብ ጭምር ሚያሳትፍ በመሆኑ የሼር ሽያጩን ከጀመርንበት ቀን ጀምሮ በሽያጭ ቦታዎች ሰልፎችን አስተውለናል” ሲሉ አህባቡ ተናግረዋል። “በ3 ወር ውስጥ የመጀመያውን ዙር የሼር ሽያጭ አጠናቀን ባንኩ ሥራ እንዲጀምር ለማድረግ ርብርብ ላይ ስንሆን ቀሪውን በስድስት ወር ውስጥ እናሟላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል እና በ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቀው ሂጂራ ባንክ 38 አደራጅ ኮሚቴ አባለት ሲኖሩት ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ሴቶች ናቸው። የአደራጅ ኮሚቴው ሲጀመር ስምንት እንደነበር የተናገሩት አህመዲን ከተለያየ ዓለማት የተለያዩ ባለሞያዎች በመሰባሰብ ቁጥሩ መጨመሩን ተናግረዋል። በተለያዩ የዓለም አገራት ውስጥ ባሉ የወለድ ነፃ ባንኮች አማካሪ የነበሩ፣ የኢንቨስተመንት አማካሪ የነበሩ እንዲሁም በዘርፉ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የተማሩ መሆናቸው ተገጿል።

ከወለድ ነፃ ባንክ አባልነትም ሆነ አገልግሎት ለማኛውም ሰው ክፍት እንደሆነ ያስታወቀው አደራጅ ኮሚቴው የሼር ሽያጭ ቢፈቀድም ባንኮቹን ወደ ሥራ የሚያስገቡ ሌሎች ሕጎች እና መመሪያዎች ግን ገና በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ገልጾ በአጭር ጊዜ ሕጎቹ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

ከወለድ ነፃ ባንኮችን የማቋቋም ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስተሩ እንደፈቀ ተደርጎ የሚነሳው ሐሳብ ስህተት እንደሆነ የተናገሩት አህመዲን ከ7 ዓመት ተፈቅዶ በአንድ መመሪያ የተከለከለ መሆኑን ገልፀው የተለያዩ ባንኮች በመስኮት ደረጃ አገልግሎቱን ሲሰጡ መቆታቸውነም አስታውሰዋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here