እስራኤላዊው ባለሀብት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አግባቢነት ከእስር ተፈቱ

0
431

እስራኤላዊው የመንገድ ግንባታ ድርጀት ባለቤት ሜናሼ ሌቪ ላለፉት አራት ዓመታት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በአዲስ አበባ በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ ሰኔ 2011 መጨረሻ ላይ ከእስር ተለቀው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ታወቀ።

በኹለቱ አገራት መሪዎች መካከል ዘለግ ያለ ድርድር ከተደረገ በኋላ ኢትዮጵያ ግለሰቡን ለመልቀቅ መስማማቷን እና ግለሰቡም 345 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ከፍለው ከእስር መላቀቃቸው ታውቋል። ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ከጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ተነጋግረው ግለሰቡ ወደ አገሩ መመለሱን ግለሰቡን ያነጋገረው ጀሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።

ዐቃቤ ሕግ በወቅቱ ሰባት ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ግብር በመሰወር፣ በሕገወጥ መልኩ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ እንዲሁም ለፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን የሥራ ኀላፊዎችን በማሞሰን ወንጀል ክስ እንደመሰረተበት ይታወሳል። በኩባኒያቸው የትድሃር ኤክስቬሽንና ኤርዝ ሙቪንግ አማካኝነት የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ላይ ከ 2001 ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራዎችን ሲያከናውኑ የነበሩት ግለሰቡ በሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በማዕከላዊ እንዲሁም በቃሊቲ ማረሚያ ቤቶች መቆየታቸው ይታወቃል።

እስራኤላዊው ሜናሼ ሌቪ ከ6 ኪሎ- ፈረንሳይ ለጋሲዮን የመንገድ ፕሮጀክት በመሥራት ላይ እያሉ በሙስና እና ታክስ ወንጀሎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለ ማሪያም ደሳለኝ ጋር በተደረጉ ድርድሮች ለመፈታት ጫፍ ደርሰው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥራ መልቀቅ ምክንያት እንደአዲስ ድርድር እንደተጀመረም ለጄሩሳሌም ፖስት ተናግረዋል።

በተከሳሹ ጠበቆችና በእስራኤል ዐቃቢ ሕግ በተደረገ ከፍተኛ ጫና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንያሚን ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ ላይ ከፍተኛ ጫና ማድረጋቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

ሜናሼ በቃሊቲ እያሉ በአንድ “ፀረ አይሁድ እስረኛ” መደብደባቸውን ተከትሎ የአይሁድ አክቲቪስቶች ጉዳዩን ከታክስ ስወራ ወንጀል ወደ ፀረ ሴማዊነት ትግል በማሸጋገር በመገናኛ ብዙኀን አጀንዳ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል። ከቻድ መነሻውን ያደረገውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ተሳፍሮ የነበረ አንድ ተሳፋሪ ከአንድ እስራኤላዊ ጋር በፈጠረው ግብ ግብ ምክንያት በቁጥጥር ሥር ውሎ ሜናሼ ወዳረፈበት እስር ቤት በመላኩ ከፍተኛ አካላዊ ድብደባ በማድረሱም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበረም ለጄሩሳሌም ፖስት ተናግሯል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባወጣው መረጃ መሰረት በተደረገ የወንጀል ምርመራ ምክንያት በእስር ላይ የቆዩት ሜናሼ በመጨረሻም የወንጀል ክሶቹ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንደተደርገላቸው ጄሩሳሌም ፖስት አስታውቋል። አዲስ ማለዳም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ካሉ ምንጮቿ ለመረዳት እንደቻለችው ከአንድ ወር በፊት ክሱ በምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ መቋረጡን አረጋግጠዋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here