1.3 ሚሊዮን ዜጎች የጎርፍ እና የድርቅ አደጋ ተጋርጦባቸዋል

0
735

የአደጋ ሥጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤንኦቻ) ጋር በጋራ በመሆን ባካሔዱት ጥናት በዚህ የክረምት ወቅት ቁጥራቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ለአደጋ መጋለጣቸውን አስታወቁ።

ጥናቱ በሰባት የኢትዮጵያ ክልሎች ማለትም በአማራ፣ አፋር፣ ሱማሌ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ ኦሮሚያ እና ድሬዳዋ የተካሔደ ሲሆን በእነዚህም ጉዳት ይደርስባቸዋል ተብሎ ከታመነው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 331 ሺሕ የሚሆኑት ከቤት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉ ጥናቱ ያትታል።

በግንቦት መጀመሪያ እና በሰኔ አጋማሽ አካባቢ ጥናቱ በሸፈናቸው አካባቢዎች ውስጥ 38 ጣቢያዎች ላይ በሰባቱም ክልሎች የጎርፍ አደጋ መከሰቱንም በተጨማሪ የተብራራ ሲሆን የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ ተከትሎም 42 ሺሕ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ታውቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የቁም እንሰሳት መሞታቸውን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ጥናቱ ከተካሔደባቸው ክልሎች ውስጥ በአፋርና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የጉዳቱ መጠን ከፍ እንደሚል ለማወቅ ተችሏል።

ከተከሰተው ጎርፍ በተጨማሪ በአፋርና በደቡብ ክልሎች ጎርፉን ተከትሎ ድርቅ ይከሰታል የሚል ግምት እንዳለም አዲስ ማለዳ ከአደጋ ሥጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። በዚህም መንግሥት በጥናት ተደግፎ የደረሰውን መረጃ ወደ ተግባር በመቀየር የሚቻለውን ርብርብ እንደሚያደርግና የሚከሰተውን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ለመረዳት ተችሏል።

በተያዘው የክረምት ወቅት በኹሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተመጣጣኝ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር አዲስ ማለዳ ከብሔራዊ የአየር ትንበያ ኤጀንሲ ያገኘችው መረጃ ያመለከተ ሲሆን አንዳንድ አካባቢዎች ግን ከወትሮው ለየት ባለ በኩል ከፍ እና ዝቅ የሚል የዝናብ ስርጭቶች ሊታዩ እንደሚችሉም ተጠቁሟል። ከዚህም በተጨማሪ የብሔራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን በጥናቱ እንዳስቀመጠው፤ ጥናት ከተደረገባቸው 20 የምሥራቅ ሐረርጌ ዲስትሪክቶች ውስጥ ዘጠኝ የሚሆኑት እና በምዕራብ ሐረርጌ 15 ወረዳዎች ውስጥ ሰባቱ ከሚጠበቀው በታች የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው እና የድርቅ ሥጋትም እንደሚያጋጥማቸው ጨምሮ አስታውቋል።

በአጠቃላይ ከሰኔ 2011 እስከ መስከረም 2012 ድረስ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ የነብስ አድን ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ለማወቅ ተችሏል። ይህንም የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ 10 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ አፋጣኝ የቅድመ መከላከልና የዕርዳታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ታውቋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here