በቄለም ወለጋ ዞን ፍርድ ቤቶች ወደ ሥራ መመለስ ጀመሩ

0
471

በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጨምሮ ለወራት ሥራ አቁመው የነበሩ ፍርድ ቤቶች ወደ ሥራ መመለስ መጀመራቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ። በአካባቢው ያለውን ያለመረጋጋት ተከትሎ የዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤቶችን ጨምሮ የወረዳ እንዲሁም የዞን ፍርድ ቤቶች ለስድስት ወራት ሥራ አቁመው የነበሩ ሲሆን ባለፈው አንድ ወር ውስጥ አብዛኞቹ ሥራ መጀመራቸው ታውቋል።

ስድስት ወረዳዎች ሲቀሩ ሌሎቹ ወደ ሥራ መመለሳቸውን የገለፁት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኑኘት ኀላፊ ጎንፋ አቶማ የምዕራብ ወለጋ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ወደ ሥራ ከተመለሱት ፍርድ ቤቶች መካከል እንደሆነ ጨምረው ገልፀዋል።

“በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ብዙ ጥቃቶች ሲፈፀሙ ዳኞች ላይ ግን ምንም ጉዳት አልደረሰም” ያሉት ጎንፋ በአካባቢው እየሰፈነ በመጣው አንፃራዊ ሰላም ፍርድ ቤቶቹ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በተያያዘም የክልሉ ፍርድ ቤት ባለፈው አንድ ዓመት ባካሔደው የለውጥ ሥራ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አዋጁን በማሻሻል የዳኞች የሥነ ምግባር ጥፋት ጉዳይ በዞን ደረጃ እንዲታይ እና ውሳኔም እንዲሰጥበት በመደረጉ ከ300 በላይ በሚሆኑ ዳኞች ላይ አስተዳዳራዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረው ከእነዚህም 21ዱ ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጉን አክለዋል።

“ከዳኝነት እንዲነሱ ከተደረጉት መካከል አብዛኞቹ በሙስና ምክንያት ሲሆን ሌሎቹ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል” ያሉት ኀላፊው “በዚህ ዓመት የሥነ ምግባር ችግሮች ላይ በወሰድነው ጠንካራ አቋም የሥነ ምግባር ጉዳዮችን የሚከታተል አዲስ ዳይሬክቶሬት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ ተዋቅሯል” ሲሉ ተናግረዋል። ዳይሬክቶሬቱ ሕገወጥ ድርጊቶች ከተፈፀመ በኋላ ሕጉን ተከተሎ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ከማገዝ ባሻገር ድርጊቶቹ ሳይፈፀሙ በፊት የመካለከል ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመትም በአጠቃላይ በክልሉ 600 ሺሕ መዝገቦች የታዩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 93 በመቶው እልባት ማግኘታቸውን እና ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ ሔደው የተሻሩት ውሳኔዎች ከኹለት በመቶ እንደማይበልጡ ጎንፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ይህንን አፈፃጸም ለማምጣትም ዋነኛውን ድርሻ ወጣት ዳኞች እንደሚወስዱ የተገለፀ ሲሆን በሥነ ምግባር በኩል በክልሉ በሰፊው ሲታይ የነበረውን ክፍተትም እነዚህ ወጣት ዳኞች በከፍተኛ መልኩ እንዳሻሻሉትም ተጠቅሷል። በክልሉ ካሉ ዳኞች አብዛኛው በ20ዎቹ ውስጥ እንደሆኑ የተናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው በተያዘው ዓመት ብቻ ከ200 በላይ ዳኞች በጨፌው መሾማቸውን ተናግረዋል። ጨፌው ከኹለት ሳምንት በፊት ባካሔደው ስብሰባም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሸሙት ዳኞች ከኹለቱ በቀር ሌሎቹ በሰላሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ መሆናቸውንም ለማሳያነት ጎንፋ አንስተዋል።

በጡረታ በተገለሉ እና ወደ ፌደራል ፍርድ ቤቶች ሹመት ባገኙ ዳኞች ምትክ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተሸሙት ዳኞች መካከልም 12 ወንዶች ሲሆኑ አንዷ ወጣት ሴት ዳኛ መሆናቸው ታውቋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here