ብሔራዊ ሎተሪ በታሪኩ ከፍተኛውን ትርፍ አስመዘገበ

0
702

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በያዝነው በጀት ዓመት የተጣራ 192 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ በማስመዝገብ በታሪክ ከፍተኛ የሆነውን ገቢ ከማግኘቱ ባሻገር በዓመቱ አገኘዋለሁ ብሎ ካቀደው 171 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ጋር ሲነጻጸርም ከዕቅዱ በላይ የ12 በመቶ ጭማሪም አሳይቷል።

በ2010 በጀት ዓመት 152 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ያስመዘገበው አስተዳደሩ በ39.9 ሚሊዮን ብር ብልጫ አስመዝግቧል። ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ26 በመቶ ብልጫ መኖሩን አስተዳደሩ ለአዲስ ማለዳ የላከው ሪፖርት ያሳያል።

የግማሽ ዓመት ትርፉም ትልቁ የነበረ ሲሆን በቀጣይ 6 ወራትም ተመሳሳይ ትርፍ አሳይቷል። በዚህ የበጀት ዓመት አጋማሽ ላይም ለተመዘገበው ከፍተኛ ትርፍ የወረቀት ሎተሪ ሽያጭ መጨመር እና ከተዛማጅ ጉዳዮች የሚሰበሰቡ ገቢዎችንም በአግባቡ መሰብሰብ ስለታቸለ መሆኑ ይታወቃል። በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ዕጣ ነክ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠርና ከዘርፉም እስከ 15 በመቶ ገቢ የሚያገኝ ሲሆን ፋብሪካዎች እና ከባንኮች በኩል ለተጠቃሚዎች ከሚደረሱ ሽልማቶች የዕቃዎቹን ጠቅላላ ዋጋ 15 በመቶ የሚሆነውን መሰብሰቡም ታውቋል።

በ2011 ዐሥራ ኹለት የሎተሪ ዓይነቶችን ገበያ ላይ በማዋል ከተጨማሪ እሴት ታክስ በፊት 885.6 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ለማከናወን ታቅዶ 757.98 ሚሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 85.59 በመቶ ሽያጭ መከናወኑን ሪፖርቱ አመላክቷል። ይህንን እቅድ ለማሳካትም እንቅፋት ከነበሩበት ጉዳዮ አንዱ ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከፍተኛ ዕጣ ያላቸው ሎተሪዎች እና የመደበኛ ሎተሪ የትኬት ኅትመት በተደጋጋሚ ጊዜ በመዘገየቱ ሲሆን በተጫማሪም በውጪ ለሚታተሙ ኅትመቶች ደግሞ የውጪ ምንዛሬ ያለመፈቀድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

አስተዳደሩ በራሱ ከሚያከናውናቸው የሎተሪ ሽያጭ ውጭ በግሉ ዘርፍ ላሉ እና ሎተሪ በማጫወት ሥራ ላይ ለተሰማሩ፣ የልማት ማኅበራት ሆነው ቶምቦላ ሎተሪ ለሚያዘጋጁ እና ገቢ ለማሰባሰብም ፈቃድ እንደሚሰጥ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ከኳስ ስፖርት ጋር በተያያዘ ለሚሠሩ አቋማሪ ድርጅቶች ፈቃድ ምስጠቱንም ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ብሔራዊ ሎተሪ ከጠቅላላ ገቢው 43 በመቶ የሚሆነውን መልሶ ለሎተሪ ባለ ዕድለኞች ለሽልማት እንደሚያውለው የታወቀ ሲሆን እንዲሁም ከጠቅላላ ገቢው በየዓመቱም 21 በመቶ የሚሆነውን ወደ መንግሥት ካዝና ፈሰስ የሚያደርግ ሲሆን ተጠሪነቱም ገቢዎች ሚኒስቴር ነው።

በበጀት ዓመቱ አስተዳደሩ ከሎተሪ ሽያጭ 958 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በፈቃድ ከሚካሔዱ ሎተሪዎች የኮሚሽንና ፈቃድ ክፍያ እና ከልዩ ልዩ ገቢ 994 ሚሊዮን ብር ገደማ ለማሰገባት እንዲሁም 822 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 171 ሚሊየን ብር ገደማ ትርፍ ለማስመዝገብ ታቅዶ ነበረ ሲሆን በበጀት ዓመቱ አሰተዳደሩ የእቅዱን 112.20 በመቶ በማሳካት መቻሉን አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here