የኒያላ ኢንሹራንስ የዐረቦን መጠን ከሩብ ቢሊዮን ብር በላይ ቀነሰ

0
1091

በኢትዮጵያ የግሉን የኢንሹራንስ ዘርፍ በቀዳሚነት በመምራት የሚታወቀው ኒያላ ኢንሹራንስ በ2011 በጀት ዓመት ሰበሰበው የዐረቦን መጠኑ በ300 ሚሊዮን ብር መቀነሱ ታወቀ። ኢንሹራንሱ ከደንበኞቹ የሚሰበስበው የዐረቦን መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ ካስመዘገበው 769 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወደ 469 ሚሊዮን ብር አካባቢ መደረሱ ታውቋል።

ኒያላ ኢንሹራንስ ለተከታታይ ዓመታት የግል ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን በገበያ ድርሻ በመምራት የሚታወቅ ሲሆን በ2010 በጀት ዓመት ከነበረበት የኹለተኛ ደረጃ በመውረድ በ2011 በጀት ዓመት ስምንተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል። ኒያላ በአጠቃላይና በሕይወት መድን የነበረው ደረጃ በተመሳሳይ ዝቅ ማለቱን የተገኘው መረጃ ያሳያል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ኒያላ ኢንሹራንስ ከ2010 በጀት ዓመት ከነበረው የ8 ነጥብ 6 በመቶ የአጠቃላይ መድን የገበያ ድርሻ ከፍተኛ ቅናሽ በማሳየት በ2011 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 5 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኒያላ ኢንሹራንስ በሕይወት መድህን ዘርፍ የሰበሰበው የዐረቦን መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ ብልጫ ያሳየ ቢሆንም ከአንድ እስከ ዐሥር ባለው ደረጃ ግን ቀድሞ ከነበረበት የኹለተኝነት ደረጃ በአንድ ደረጃ ወርዶ ሦስተኛ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። ኩባንያው በ2010 በጀት ዓመት 69 ሚሊዮን ብር የሕይወት መድህን ዐረቦን ሰብስቦ እንደነበረ የሚታወስ ነው። በ2011 በጀት ዓመት ደግሞ 74 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ የሕይወት መድሕን የዐረቦን መጠኑን ማሳደግ እንደተቻለ ለመረዳት ተችሏል።

በ2011 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንደስትሪው በኢትዮጵያ መነቃቃት የታየበት እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። በዚህም ረገድ በ2011 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ዐረቦን መጠን በማስመዝገብ የቀዳሚውን ደረጃ የያዘ ሲሆን በኢንሹራንስ ገበያ ድርሻውም 38 በመቶ እንደሆነ የታወቀ ሲሆን የአምናው ተመሳሳይ ወቅት ካስመዘገበው 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ከፍተኛ ጭማሪ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል። የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን በመከተል አዋሽ ኢንሹራንስ እና አፍሪካ ኢንሹራንስ በኹለተኛ እና በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን 691 ነጥብ 3 ሚሊዮን እና 537 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በቅደም ተከተል መሰብሰባቸው አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

ኒያላ ኢንሹራንስ በ1987 መንግሥት የመድህን ዘርፉን ለግል ባለሀብቶች ክፍት ማድረጉን ተከትሎ የተቋቋመ ሲሆን የተከፈለ ካፒታሉ ከ340 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን 141.3 ሚሊዮን ብር ትርፍ በ2010 በማግኘት በግል ኢንሹራንስ ዘርፍ ቀዳሚ መሆን ችሎ ነበር። ከኩባንያው ዐረቦን መቀነስ ጋር በተያያዘ የድርጅቱን ማርኬቲንግና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኀላፊ ተገኔ ማስረሻ አዲስ ማለዳ ላቀረበችላቸው ጥያቄ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here