ንግድ ባንክ የደረጃ ዕድገት እንዳይሰጥ እግድ ተጣለበት

0
708

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ ማኅበር በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ቦርድ መስርቶ በነበረው ክስ ምክንያት ባንኩ ክርክሩ እስኪያልቅ ድረስ ማንኛውንም ዓይነት የሥራ ደረጃ ዕድገት እንዳይሰጥ እግድ ተጣለበት። በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር በተዋቀረው አስተዳደራዊ ችሎት ሐሙስ፣ ሐምሌ 18 በተሰጠው የእግድ ትዕዛዝም ባንኩ የደረጃ ዕድገት ማስታወቂያዎችን እንዳያወጣ እና ማንኛውንም የሥራ ዕድገት ሒደት እንዳያከናውን ታግዷል።

ከ28 ሺሕ በላይ የሚሆኑት የባንኩ ሠራተኞች በማኅበራቸው አማካኝነት በመሰረቱት የወል ክስ ባንኩ በኅብረት ስምምነቱ ላይ በተጠቀሱ ስድስት መስፈርቶች ላይ ብቻ ተመስርቶ ዕድገት ይፈፅም የሚል ሲሆን ባንኩ በበኩሉ የሠራተኞችን አቅም የምለካበት አዲስ አሠራር በጥናት ለይቻለሁ፤ የኅብረት ስምምነቱ ላይ ባሉ መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ አልስማማም በማለት ሲከራከር ቆይቷል።

በክርክሩ መሐልም ንግድ ባንክ አዲስ የዕድገት ሒደት በመጀመሩ የሠራተኛ ማኅበሩ ባንኩ የኅብረት ስምምነቶቹን አላከበረም ሲል እገዳ እንዲጣልበት አመልክቷል። በችሎት የተገኙት የባንኩ ጠበቃ እግዱን ተቃውመዋል። እስካሁንም የእግድ ትእዛዙ በጽሁፍ እንዳልደረሳቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረው ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

የሠራተኛ ማኅበሩ ከባንኩ ጋር ባለው የኅብረት ውል ስምምነት መሰረት የድርጅቱ ሠራተኞች የሥራ ሰዓት በሳምንት 41 ሰዓት እንዲሆን የሚደነግግ ቢሆንም ባንኩ ግን በሳምንት 48 ሰዓት እንዲሠሩ ማድረጉ ሌላው የክሱ ይዘት ነው።

35 ሺሕ ገደማ ሠራተኞች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2011 በጀት ዓመት 19 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል።
በ1960 የሠራተኞችን መብት ለማስከበር የተቋቋመው ማኅበሩ በአጠቃለይ ለተከታታይ ዓመታት ለአባላቱ የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች በማቅረብ ይታወቃል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here