በወለጋና በጉጂ ዞን ከ3 ሺሕ በላይ ተፈናቃይ ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ተነጣጥለዋል

0
1037

በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ እንዲሁም በጉጂ ዞን ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩና ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ ከ3 ሺሕ በላይ ተፈናቃይ ቤተሰብ አልባ ሕፃናት መኖራቸው ታወቀ።

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ከቤኒሻንጉል ክልል ተፈናቅለው የመጡ በምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ የሚገኙ 1130 ሕፃናት (1000 ወንዶች እና 130 ሴቶች)፣ እንዲሁም ከጌዲዮ ዞን ተፈናቅለው በጉጂ ዞን ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል 1919 (1027 ሴቶች/ 892 ወንዶች) የሚሆኑት ሕፃናት በአሁኑ ወቅት ቤተሰቦቻቸው ከጎናቸው አይገኙም።

እነዚህ ሕፃናት በስደት ወቅት በነበረው ግርግር ሳቢያ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ በሞት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ መሆናቸውን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት ላይ ገልጿል። ከእነዚህ ሕፃናት መካከል 416 የሚሆኑትን (197 ሴት/ 219 ወንድ) ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት መቻሉንም ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል።

ከእነዚህም መካከል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከቦሎጅንፎይና ያሶ ወረዳ ተፈናቅለው በቡረ እና ሀሮ ሊሙ ተጠልለው የነበሩ ዜጎች ውስጥ ያሉ ሕፃናት እንደሚገኙበት ታውቋል።

በመስከረም 2011 ከቦሎጅንፎይና ያሶ ወረዳ ተፈናቅለው በቡረ እና ሀሮ ሊሙ እንዲሁም ነቀምት ተጠልለው የነበሩት ተመላሽ ሕፃናቱ ለርሃብ እና ለመቀጨጭ (Malnutrition) መጋለጥ፣ በሞራል እና በማኅበራዊ እሴቶች ተገንብቶ ያለማደግ፣ ወላጅ አልባነት በሰፊው ተጋላጭ መሆናቸውንም ኮሚሽኑ አክሎ ገልጿል።
ሕፃናቱ የተመጣጠነ ምግብ ችግር እንደነበረባቸውና ያንንም ችግር ለመቅረፍ ከዩኒሴፍና ከሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በጋራ በተሠራው ሥራ ፋፋና ሌሎች ተመጣጣኝ ምግቦችን በማቅረብ ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል። ችግሩ ከወለጋ ወደ ቀድሞ ቀያቸው የተመለሱ የቤኒሻንጉል ተፈናቃዮች ላይ መከሰቱንም ሪፖርቱ አትቷል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታረቀኝ ተሲሳ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት በሕፃናቱ ላይ አለ የተባለውን ችግር አምነው፣ ከብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚቀርብላቸውን አልሚ ምግቦች በተገቢው መልኩ ለሕፃናቱ ማቅረብ ጀምረዋል። በተለይ ቤተሰብ አልባ ሕፃናት ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት። ዘግይተው የነበሩ ለተፈናቃዮቹ የሚቀርቡ ድጋፎችም አሁን ሙሉ ለሙሉ ማዳረስ መቻላቸውን ጠቁመዋል።
እንደታረቀኝ ገለጻ፣ በቂ የሆነ እርዳታ በክልሉ አለ፤ ነገር ግን በቡረ አና ሀሮ ሊሙ ወረዳ ለተጠለሉት ሰዎች ዕርዳታው ሳይደርስ 15 ቀን ዘግይቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ዕርዳታውን በአግባቡ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር ሰብኣዊ ድጋፍ ለሁሉም ተፈናቃዩች እንዲዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስታወቁት ታረቀኝ፣ የክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ችግሮቹን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ለሕፃናቱ በቂ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here