ኢዜማ የመጀመሪያው የፖሊሲ ሐሳብ ጥናት ላይ ውይይት አካሔደ

0
314

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) 40 በሚሆኑ ምሁራን በዐሥር በተለያዩ ዘርፎች ያስጠናው ጥናት የመጀመሪያ ዙር መጠናቁን እና በጥናቱ ላይም ከዛሬ ሐምሌ 27 ጀምሮ ለኹለት ቀናት የሚቆይ ውይይት ማካሔድ ጀመረ።

መድረኩ የተለያዩ አገር ለማስተዳደር የሚጠቅሙ የፖሊሲ አማራጮች ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና ምሁራን ተሳታፊ የሚያደርግ መድረክ መሆኑንም ፓርቲው አስታውቋል። ጥናቱን ያደረጉት ምሁራን፣ ኢዜማ የቆመላቸውን መርሆች፣ ዜግነትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካና ማኅበራዊ ፍትሕ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰፍን ሊያስችሉ ይችላሉ የተባሉ የፖሊሲ አማራጮችን ዓላማ አድርገው ሲያጠኑ መቆታቸውን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዐሥር ከተከፋፈለው እና ባለ 145ቱ “ግርድፍ ረቂቅ” ቅድሚያ የሰጠው አማራጭ የምጣኔ ሀብት መርሃ ግብሮች ላይ ሲሆን የነፃ ገበያ እንዲሁም የመንግሥት መር የምጣኔ ሀብት አማራጮች ላይ ያተኩራል። የነፃ ገበያን አማራጭ እና የልማታዊ መንግሥትን አካሔድ በተከታታይ “አንዱ ምናባዊ ሌላኛው ልማደዊ፤ አንዱ ከውጭ የሚጫንብን ሌላኛው በልምድ የተገኘና ሌላው ከለሙ አገሮች ስልት የዘየደልን። አንዱ የትም ያልነበረ፤ በተሞከረበት ጥቂት አገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ የነበረውን እንዳልነበር አክስሞ ኅብረተሰቡንና አገሩን ለሰቆቃ የዳረገ ስልት ነው” ሲል ጥናቱ አስቀምጧቸዋል።

የነፃ ገበያ ሥርዓት አማላይ ሆኖ ኅልውናው በሐሳብ ደረጃ የተወሰነ ነው የሚለው ጥናቱ ማንም አገር በዚህ ሒደት ያደገ፣ የለማ፣ የሰለጠነ የለም በማለት ያብራራል። ምጣኔ ሀብታችሁን ለነፃ ገበያ አስረክባችሁ ተንቀሳቀሱ የሚሉን አገሮች ይህንን ስልት አልተከተሉም የሚለው ረቂቁ ለደሩሱበት ሥልጣኔ፤ ለሚኖሩት የተቀናጣ ኑሮ የበቁት በነፃ ገበያ አመራር ሳይሆን በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር፣ በመልካም አስተዳደር፣ ገበያን በመግራትና በመምራት፣ ዓላማ ሰንቆ በርትቶ በመሥራት፣ ችግር ፈቺና የለማ ሁለንተናዊ ስብዕናን ገንቢ ዕውቀትና ክህሎትን በማዳበር መንግሥትና ሕዝብ ተባብረው የደረሱበት ለመድረስ ወስነው ጠንክረው በመሥራት ነው ሲልም ይደመድማል።

“እንደ እኛ ልማት ጀማሪ አገርን በልማት ከበሰሉ አገሮችና ግዙፍ ድርጅቶች ጋር በነፃ መድረክ ተወዳደር ማለት የዓለም የቦክስ ሻምፒዮናን ከጨቅላ ሕፃን ጋር ማወዳደር እንደ ማለት ነው” ሲል ጥናቱ ስለ መጀመሪያው የነፃ ገበያ አማረጭ ያብራራል። አክሎም “85 በመቶ ለሆነው ሕዝባችን የኅልውና መሠረት የሆነው የግብርና ዘርፍም ሆነ ከኢንዱስትሪ አልባነት ወደ ከፍተኛ የማምረቻ ተቋማት ባለቤትነት ሽግግር መነሻ ይሆኑናል ብለን ተስፋ የጣልንባቸው ጥቃቅን፤ አነስተኛና መካከለኛ የኢንዱስትሪ ማዕከላቶቻችን ያለአንዳች ከለላ፤ እገዛና እንክብካቤ ለውድድር ይጋለጡ ቢባል በአንድ ሌሊት ደብዛቸው እንደሚጠፋ የታወቀ ነው” ሲል የውድድሩን ፍትሐዊነት ለማስጠበቅ አማራጭ ያቀርባል።

መንግሥት ሙሉ በሙሉ ከገበያው መውጣት የለበትም የሚለውን ክርክር የሚያብራራው ሰነዱ ለምጣኔ ሀብት ዕድገትና ለሕዝብ ልማት እጅግ አስፈላጊ በሆኑ ዘርፎችና ተግባራት የግሉ ክፍል በአቅም ማነስ ወይም አዋጭነቱ ባለመረጋገጡ ምክንያት ተሳትፎውን በሚያቅብበት ወቅት መንግሥት በእነዚህ ተግባራት እንደሚሳተፍ ያትታል። ተሳትፎው ለብቻው ወይም ከአገር ውስጥና ከውጭ ባለሀብቶችና ድርጅቶች ጋር በሽርክና ሊከናወን እንደሚችልና ከእነዚህ ተግባራት ኀይል ማመንጨት፣ መንገድ መዘርጋት እና ትላልቅ የማምረቻ ድርጅቶችን መገንባት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ይገልፃል።

ናትናኤል ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት በውይይቱ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እና የፖሊሲ አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ሐሳቦች በተለያዩ ባለሙያዎችም ትችት ይቀርብባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ጥናቱም ከዚህ በፊት ያሉትን የፖሊሰ ሐሳቦች ሙሉ ለሙሉ እንደማያስቀር ነገር ግን በጎነታቸው ተፈትሾ መልካም ጎኖቻቸውን የመውሰድ መርህ መኖሩንም ናትናኤል ተናግረዋል።

በግብርና፣ በማኅበራዊ፣ በተፈትሮ ሀብት ትምህርት እና ጤና እንዲሁም ባሕል ጨምሮ በዐሥር ዘርፎች የተለያዩ ሐሳቦችን በማብራራት ሰነዱ አቅርቧል።
“ውይይቱ የተለያዩ ግብዓቶችን እንድናገኝ ይጠቅመናል” ያሉት ናትናኤል “ጽሑፉን የሚያቀርቡት ምሁራን ያልሸፈኑት እና የዘነጉት ነገር ካለ እሱን ለመለየትም ይጠቅመናል” ብለዋል ናትናኤል። “ከዚህ በተረፈ ጥናት አቅራቢ ባለሙያዎቹ ይዘው የሚመጡት ነገር፣ የተለያየ አተያይ እንዲኖረውና ሙሉ የፖሊሲ አማራጭ ሆኖ እንዲወጣ ይጠቅማልም” ብለዋል።

ጽሁፍ አቅራቢ ምሁራኑ በዜግነት ፖለቲካ ላይ መሰረት ባደረገ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ፍትሕ ላይ ትኩረት ሰጥተው የፖሊሲ አማራጭ ለመቅረጽ ፈቃደኛ የሆኑ በተለያየ ደረጃ በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በሌሎች ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ምሁራን (አንዳንዶቹ የኢዜማ አባላት የሆኑ) እና የኢዜማ አባላት መሆናቸውንም ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

“ሕዝቡም ከዚህ በፊት እንደነበረው፣[ኢዜማ] ዝም ብሎ በመቃወም ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን በጥናት የተደገፈ፤ አሁን ያሉትን የአገሪቱ ተጨባጭ ችግሮች ባገናዘበ መልኩ መፍትሔ መስጠት የሚችል አማራጭ የያዘ ፓርቲ እንደሆነ እንዲገነዘብ እንፈልጋለን” ሲሉ ናትናኤል ተናግረዋል።

እንደ ኢዜማ ማብራሪያ፣ ከውይይቱ የሚወጡት የፖሊሲዎች አማራጮች በዜጎች መካከል ያለ የኑሮ ልዩነት ብዙም የሰፋ እንዳይሆንና ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል ዕድል የሚያገኝበትን የሚያመቻችበት ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል የፖሊሲ አማራጭ ነው የሆናል ብለው እንደሚያስቡ ጨምረው ገልጸዋል።

ኢዜማ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ችግር ቅድሚያ ይሰጣል፤ በመሆኑም ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያግዙ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ትኩረት ያደርጋል ያሉት ናትናኤል፥ የፖሊሲ አማራጭ ውይይቶቹ በመጀመሪው በዝግ መድረክ ይካሔዳሉ፤ በመዝጊያው ዝግጅት ላይ ግን ለመገናኛ ብዙኀን ክፍት እንደሚሆንም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here