የአበበ ተክለ ኃይማኖት (ሜ/ጀ) በራስ ላይ አመፅ! በ“የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?”

0
1028

ባለፈው ሳምንት በገበያ ላይ የዋለውን የአበበ ተክለ ኃይማኖት (ሜጀር ጀነራል) “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት? የደኅንነት ማስጠንቀቂያ ደውል” መጽሐፍ ተገቢ ቦታ አልተሰጠውም በሚባለው የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ትኩረት አድርጓል። ይነገር ጌታቸው መጽሐፉን በማንበብ ጠንካራ ጎኖች ያሏቸውን እና ጸሐፊው ከዚህ ቀደም ያራምዱት የነበረውን አቋማቸውን ለመተቸት አለመሳሳታቸውን በማድነቅ እንዲሁም የመጽሐፉ ደካማ ጎኖች ናቸው ያሉትንም ጉዳዮች ጠቁመዋል።

“የባሕር በር ጥያቄን የሚያነሱ ሰዎች የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያጎናጸፈውን አነቀጽ 39 እና የኤርትራን ነጻነት የማይቀበሉ ጦርነት ናፋቂ የፊውዳል ስርዓትና ወታደራዊ አምባገነኑ ደርግ ርዝዥ ናቸው አስተሳሰብ ነበረን።……ቀደም ሲል ለምን ያንን ዓይነት አቋም እንዳራመድን ታሪክ የሚመልሰው እንቆቅልሽ ነው። ለእኔ ግን የእብሪትና የድንቁርና ቅልቅል ነው።” (ገጽ 150-151)

ለራስ ተግሳፅ አይሰስቱም። ለትናንት ስህተታቸው አይራሩም። በልባቸው አሁንም እንደትናንቱ ወጣት ይመስሉኛል። እንዲያ ባይሆን ኖሮ አረጋዊ ትሁኖ ከታሪክ መብሰልሰል እንዴት ይመለጣል። አበበ ተክለ ኃይማኖት (ሜ /ጄነራል) በተለያዩ መድረኮችም ይሁን የኅትመት ውጤቶች ላይ እንደ ወዳጆቻቸው በኢሕዴግ ተገፋሁ እያሉ ሙሾ ማውረድን አለመዱም። ከዛ ይልቅ ስለ ነገ ይጨነቃሉ። ስለ አገር ያወራሉ። ለዚህ ደግሞ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?” የተሰኘው መጽሐፋቸውም የምስክር ወረቀት ነው።

ከጆቤ ጋር ሽርሽር
ከአበበ ተክለ ኃይማኖት ጋር ሽርሽር ልንወጣ ነው፤ 367 ገፆችን አብሮ ለማዝገም። ጸሐፊው ብዙም ምሁራዊ ውይይት ያልተደረገበትን አገራዊ የደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ መቃኘት ላይ አተኩረዋል። ለዚህ እንዲረዳም ስለ ደኅነነት ንደፈ ሐሳባዊ ዳር አስቀምጠዋል። ይህ የቀድሞው ዓየር ኃይል አዛዥ አፃፃፍ ስልት አንድም መጽሐፉን ምርምራዊ መልክ እንዲኖረው ሲያደርግ አንድም በጸሐፊውና በተደራሲው መካከል በጉዳዩ ላይ መቀራረብ እንዲኖር አግዟል። “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?” የተሰኘው ድርሳን የደኅነትን ምንነት በውሉ ከበየነ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ፖሊሲ ለመፈተሸ ይጥራል። በ1995 ተግባራዊ መሆን የጀመረውን የውጭ ጉዳይና የደኅነነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ጠንካራና ደካማ ጎኖችም ተደጋግመው ከሚሰሙ ትችቶች በራቀ መልኩ ለማየት ሞክሯል። ፖሊሲው ሕገ መንግሥቱን እና ብዝኀ ባሕል ያላትን አገር በአግባቡ አለመጠቀሱንም ክፈተት አድርጎ ይጠቅሳል። ጸሐፊው ከዚህ በተቃራኒው በፖሊሲው የተካተተው የደኅነታችን ዋና ሥጋት ድኅነት ነው መባሉን ተገቢ አድርገው ይወስዳሉ።

ከዚህ በመነሳትም የኢትዮጵያን ደኅነት የማስጠበቅ ጉዳይ ከውጫው ይልቅ በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያስረዳሉ። አበበ ተክለኃይማኖት (ሜ/ጄነራል) ደኅንነት ማለት ህላዌ፣ የተሸለ ኑሮ፣ ነፃነትን ማስጠበቅና ማንነትንን ማስከበር መሆኑን ደጋግመው ይገልፃሉ። የኢትዮጵያን ደኅንነት የሚጠበቀውም እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በሠራነው ሥራ መሆኑን ያሰምራሉ። የጸሐፊው ሙግት ዘልማዳዊ የሚባለውን ደኅንነትን ከውጫው ሥጋት ጋር አስተሳሰሮ የማየት መንገድን የሚሽርና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአንበሳውን ድርሻ ለያዙበት የአገራችን የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲ የሚያደላ ነው። ይህ ዓይነቱ አካሔድ ደግሞ ጸሐፊውን የደኅንነትን ጉዳይ እጅጉን አገራዊ ፖለቲካ የተጫነው አድረገው እንዲመለከቱት በር ከፍቷል። አበበ (ሜ/ጀነራል) ከሚያነሱት ሐሳብ ጋር የተራራቀ የመሰለውን የመጽሐፋቸውን ርዕስ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?” እንዲሉ የጋበዛቸው ምክንያትም ከዚህ የሚቀዳ ይመስላል።

የትግል ጓዶቻቸው ጆቤ በሚል ቅፅል ሥም የሚጠሯቸው የቀድሞው የዓየር ኃይል አዛዥ ከፊል ዕድሜያቸውን በውትድርና የቀረውን ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማ ያሳለፉ እንደመሆናቸው መጠን በኹለቱ የሕይወት ፈለግ ውስጥ ያገኙትን ነገር ለአንባቢያን ለማድረስ ጥረዋል። በዘርፉ ያሉ ታላላቅ ምሁራንን ሐሳብ በመዋስ የተለያዩ ምክረ ሐሳቦችን የሚለግሱት ጸሐፊው የራሳቸውን ተሞክሮ በመጥቀስም ኢትዮጵያ ከትናንት ስህተቷ መማር እንዳለባት ይለፋሉ። እዚህ ላይ አበበ ደጋግመው የሚጠቅሱት የደኅንነት ፖሊሲ አስተዳደር ጉዳይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። በዚህ በኩል መጽሐፋቸው ልብ ያልተባላና ሳይቃጠል በቅጠል የሚሉትን ብሂል የሚያስታውስ አዲስ ሐሳብ ያጫረ መሆኑ አያጠያይቅም። ኢትዮጵያ የደኅነነት አስተዳደር የሌላት አገር በመሆኗ በኢትዮ ኤርትራም ይሁን ከዛ በኋላ በመጡ አለመረጋጋቶች ውስጥ መሪዎቿ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ተግባራት ውስጥ ሲዘፉቁ ኑረዋል። ዛሬም ከዚህ አዙሪት ባለመላቀቃችን የዜጎችን መብቶች የሚጨፈልቁ ውሳኔዎች በማይመለከታቸው አካላት ሳይቀር እየተላለፉ ይገኛሉ። ሰሞነኛው የአገሪቱ ደኅንነት ምክር ቤት በደቡብ ክልል ያቋቋመው ኮማንድ ፖስት ውሳኔም ለዚህ ዓይነቱ ሐሳባችን ማስረጃ የሚሆን ይመስላል።

አበበ ተክለ ኃይማኖት ከፊል ሕይወታቸውን በውትድርና የቀረውን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደማሳለፋቸው መጠን ትናንት እውነት ያሉትን ነገር በጊዜ ሒደት በማወቅ እየናዱት ሔደዋል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ላይ ያራምዱት የነበረውን አቋምም እብሪትና ድንቁርና ነበር ሲሉ በትናንት ማንነታቸው ላይ አምፀዋል። የኤርትራ ጦረነት መነሻ ላይም በከፊል ፀፀት የድርጅታቸውን ግትርነት (እሳቸው “ተቸካይነት” ይሉታል) እና የእኔ እውነት ልክ ነው ስሜት ያወሳሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት እስከዛሬ በድፍረት የማይነገረውን በኹለቱ አገራት ጦርነት የሞቱ የኢትዮጵያ መደበኛ ወታደሮች ቁጥር 35 ሺሕ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

የአበበ ተክለኃይማኖት “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?” መጽሐፍ በዕድሜ ሐዲድ ተሳፍሮ ረጅም እንደተጓዘ ሰው ከዛሬ ደጃፍ በመድረስም ቀዩ የአመፅ ጎርፍ በሚል ሰለቄሮና ፋኖ ትግል ያወሳል። አሁን የተያያዝነውንም የፖለቲካ ፍኖት ኹለተኛው የሽግግር ወቅት ይሉታል። የትናንቱ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱን ማከበር ባለመቻሉ ተገርስሷል፤ የዛሬውም ካለፈው ስህተት ካለተማረ መዳረሻው ተመሳሳይ መሆኑ አይቀርምም ሲሉ ይሞግታሉ።

በራስ ላይ ከአማመፅ ወዲህ!
አበበ ተክለኃይማኖት በትናንት ታሪካቸው ላይ ሙሉ በሙሉ ያመፁ ሰው አይደሉም። በዚህ የተነሳም ጥቂት የማይባሉ ጉዳዮችን አሁንም አለባብሰው ያልፋሉ። ዋናውን ችግር ወደ ዳር በመግፋት የራስ እውነትን መፍጠር ላይ ይባትላሉ።ጥቂት ማሳያዎችን ላቅርብ። ጸሐፊው ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ከተረከበ በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ ተስፋ ሰጭ ነገር ነበረው ይላሉ። የተበላሸውም በጊዜ ሒደት ነው ሲሉ ደጋገመው ያነሳሉ። በርግጥ ሕወሓት መራሹ ጦር በደርግ ላይ ድል ካስመዘገበ በኋላ ከሌሎች አገራት ወታደራዊ ቡድኖች በተለየ መልኩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም አደርጓል።

የሚኒስትርነት ቦታዎችንም ለተቀናቃኙ ኦነግ አካፍሏል። እንዲህ ያለው እውነት ግን የትናንት የዴሞክራሲ ጅምራችን የሚያሰቀና ነበር ወደሚል ድምዳሜ አያደርሰንም። ዴሞክራሲ በሕዝብ፣ ለሕዝብ ከሕዝብ የተመረጠ አስተዳደር የሚሰፍነበር ስርዓት ነው። ከዚህ አንጻር ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆናጠጠ በኋላ ያካሔደው የመጀመሪያ ምርጫ አበበ በመጽሐፋቸው አምርረው ከሚተቹት ምርጫ 2002 የሚለይ አልነበርም። በ1985 በተካሔደው የወረዳና የቀበሌ ተወካዮች ምርጫ ገዥው ፓርቲ 99.6 በመቶ ድምፅ ማግኘቱን አስታውቆ ነበር። ይህ ዓይነቱ ሀቅ አበበ በዴሞክረሲ ጅማሮው ጥሩ ነበር ያሉትን ወቅት እውነታ በጋሃድ የሚሳይ ይመስለኛል። የጸሐፊውንም የዘመን ውግንና እሳቸው የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከነበሩበት ጊዜ ጋር እንድናስተሳስረው ያደርገናል።

አበበ ቀዩ የአመፅ ጎርፍ በሚል የሚጠሩት ከ2008 ጀምሮ የተካሔደው የወጣቶች ትግል አሮጌውን ኢሕአዴግ አንኮታኩቶ አዲሱን ኢሕአዴግ እንደፈጠረ ይናገራሉ። ወቅታዊውን የፖለቲካ ትግልም በአዲስ ትውለድ የሚመራ ሲሉ ደጋግመው ይጠቅሳሉ። እዚህ ላይ ኹለት መሰረታዊ ጥያቄዎች ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል። ጸሐፊው “አሮጌ” እና “አዲስ” የሚሉትን ቃላት የሚጠቀሙት በምን አግባብ ነው? አዲሱ ኢሕአዴግም ሆነ አዲሱ ትውልድ የዘመን መልካቸው ምንድን ነው? ለእነዚህ ሐሳቦች ትክክለኛ ምላሽ ለማግኘት የድሮው ምን መልክ አለው? ዛሬስ ምኑን ቀየረው ብሎ መነሳቱ ተገቢ ነው።

የቀደመው ኢሕአዴግ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የወለደው እንደመሆኑ መጠን የብሔርና የመሬት ጥያቄን ዋና አጀንዳ ያደረገ መሆኑ የሚታበል አይደለም። ይህ ኀይል የአንበሳውን ድርሻ የያዘበት ሕገ መንግሥት መሰረታዊ መለያውም ሆነ ድጋፍና ተቃውሞ የሚቸረውም በዚህ ጉዳይ መሆኑ አያከራክርም። ከዚህ አንፃር ከግለሰብ በዘለለ ስለአንድ የፖለቲከ ፓርቲ የምናወራ ከሆነ መነሻችን የሚሆኑት እነዚህ የድርጅቱ ርዕዮት ዓለማዊ አዕማዶቻ ናቸው። እንዲህ ያለው ነገር ደግሞ ኢሕአዴግ ከትናት የተለየ ርዕዮተ ዓለማዊ ለውጥ አምጥቷ ወይ እንድንል ያስገድደናል። በእኔ ግምት ገዥው ግንባር ከትናንት ለመሸሽ ሞከረ እንጅ መሉ በሙሉ አዲስ ማንነት አልፈጠረም። ባለፉት ዐሥራ አምስት ወራት የነበሩት እንቅስቃሴዎችም የለውጥ ፖለቲካ ወቅታዊ ባሕሪያት እንጅ ለድሮና ዘንድሮ ድንበር ማበጀት አይሆኑም። አበበ 1983 የነበረውን የፖለቲካ ሽግግር አንድ ብለው በመቁጠር የዛሬውን ለኹለተኛ ጊዜ የምንሞክረው መሆኑንም ደጋግመው ይጠቅሳሉ።

ይህም ቢሆን አሳማኝ መከራከሪያ አይመስለኝም። 1983 የነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ሥር ነቀል (አብዮታዊ) የሚባል ነው። ዛሬ እየተጓዝነበት ያለው የፖለቲካ ሒደት ግን ከሥር ነቀል ይልቅ የአስተዳደር ዘዬን መቀየርና ጥገናዊ በሚባል መልኩ የተቃኘ ነው። ጸሐፊው ለኢሕአዴግ ብቻም ሳይሆን ለትውልዱም ድንበር አበጅተው ያኛው ይሔኛው ሲሉ ይታያሉ። የ1960ዎቹን ትውልድና ቀዩ የአመፅ ጎርፍ በሚልም መገለጫ ያላቸው አስመስለው ለማቅብ ይጥራሉ። ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትውልድን ከሥነ ሕይወታዊ መገለጫ ውጭ በሥነ ልቦናዊ መከፈል የሚቻል አይደለም። የዛሬ ወጣት ልክ እንደትናንቱ ሁሉ ከአሸናፊና ተሸናፊነት ትርክት አልወጣም፤ ሰጥቶ መቀበልንም አልለመደም። በ1960ዎቹ የነበረው ወጣት በህሊናው የሳላት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በግትርነት በየቦታው ተፋልሟል፤ አልፏል። የዛሬውም ትውልድም ያን የመንፈስ ውርስ ተጎናፅፏል።

እዚህ ላይ የታዋቂውን የሥነ ልቦና ምሁር ካርል ዮንግ ሐሳብ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል። ዮንግ የሰው ልጅ ባሕሪያት እጅጉን በቀደምቶቹ የተጠመቀ ነው ይላል። የእኛም እውነት ከዚህ አያመልጥም። ልዩነታችን የዕድሜ እንጅ የፖለቲካ ሥነ ልቦናችን አይደለም። ደግሞስ ማኅበረሰባዊ ቅራኔዎቻችን በውሉ ሳይፈቱ እንደ ትውልድ የወል ሥነ ልቦና እንዴት ልንገነባ እንችላለን? አበበ በመጽሐፋቸው ውስጥ የዘነጉት አንድ ትልቅ ጉዳይም ከዚህ የሚመነጭ ነው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከፖለቲካ ባሕሏ ውጭ መረዳት ያዳግታል። “ገዳይ እውዳለሁ ተኳሽ፥ የማልጠላ” እያለ የሚያዜም ሕዝብ ከኢሕአፓ፣ መኢሶንና ደርግ የተሻለ ተተኪን ማፍራት የሚችል አልነበርም።
“የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?” አብዮታዊው ትውልድ (1960ዎቹን) ለዴሞክራሲ የማይመች ሲል ይጠቅሰዋል። በእኔ ዕይታ ችግሩ አብዮታዊነቱ አይደለም።

በምሥራቅ አውሮፓ የነበረው ሶሻሊስታዊ አብዮት ያነደደው ትውልድ እኮ በክሮሽያና በሌሎቸ አገራት ዴሞክራሲያው ስርዓትን ተክሏል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከ1960ዎቹ አጋማሽ በኋላ የፓርቲ ቅርፅ ይዞ በፅንፍ የቆመ መሆኑ በጋሃድ ታዬ እንጅ ችግራችን ሥር የሰደደ ነው። መነሻችንም የፖለቲካ ባሕል ስሪታችን ነው። ጆን ማርካኪስ እንደሚለው የምዕተ ዓመት ታሪካችን በተለያዩ መልኮች ህልው ሆነ እንጅ ከአማራ፣ ትግራይና ኦሮሞ አተካራ አላመለጠም። ከጠቅላይና ተገንጣይነት ትርክት አልሸሸም።

ይህ ሐሳብ ጸሐፊው የሚመኙት የጠንካራ ክልሎች እውን መሆን ኢትዮጵያዊነትን ያለመልማል መከራከሪያም ላይ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል። በርግጥ ክልሎች በሕገ መንግሥት የተሰጠቸውን ሉዓላዊ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ በቢተገብሩ ኢትዮጵያን ዛሬ በዚህ ቅርፅ እናገኛት ነበር? አይመስለኝም።

አበበ ተክለ ኃይማኖት የቀድሞ ጓዳቸው በረከት ስምዖን “ትንሳዔ ዘ-ኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ያነሷቸውን የኢትዮጵያ ተስፋና ሥጋቶች ቢጋሩም ምንጭ ከመጥቀስ ግን ወደኋላ ይላሉ። “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?” “በትንሳኤ ዘ-ኢትዮጵያ” ላይ የሰፈሩትን ተስፋና ሥጋቶች ከሞላ ጎደል የያዘ ቢሆንም በዋቢ መጽሐፍትም ሆነ ሐሳቡ በተጠቀሰበት ቦታ ዕውቅና ሊሰጥ አለመፈለጉ ግርምትን ያጭራል። ጸሐፊው ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ ከፊል ምርምራዊ ሥራን ለኅትመት ለማብቃት እንደማሰባቸው መጠን ከእሳቸው በፊት በጉዳዩ ላይ የተሠሩ ሥራዎችን በአግባቡ አለማያታቸው ካዩም አለመጥቀሳቸውም ትልቅ ስህተት ይመስላል። የባሕር በርን ጉዳይ በዓለም አቀፍ መድርክ ዛሬም ማስመለስ እንደሚቻል ደጋግሞ የሚሰብከው “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?” ለዓመታት በዚህ ዘርፍ ተጠቃሽ የነበረውን የያቆብ ኃይለ ማሪያም (ዶ/ር) “አሰብ የማን ናት?” መጽሐፍ አንድም ቦታ ላይ አለመጥቀሱም አካዳሚያዊ ወንጀል መሥራቱን ያሳያል።

አበበ ምርምራዊ መጽሐፍን ለማቅረብ እንደሞከረ ሰው ከእሳቸው በፊት የተሠሩትን ሥራዎች በአግባቡ መፈተሸ፤ ከዛም የጎደለውን ነገር ለመሙላት ቢመጡ መልካም ይሆን ነበር። ይሁን እንጅ ጸሐፊው ተደጋግመው የተነሱ ፀንሰ ሐሳቦችን ካለምንም ማዘመን ብዙ ቦታ ላይ በሰፋፊ ምዕራፎች ለመዳሰስ ሞክረዋል። ይህም መጽሐፉ ጥቂት ብቻ አዲስ ነገር እንዲኖረው አድርጎታል። የምዕራፎቹ አደራደርም በውሉ የተካሔደ ባለመሆኑ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?” ከፍ ያለ የቅርፅ ችግር የሚስተዋልበት ሥራ እንዲሆን አድርጎታል።

ፖለቲካችንም ሆነ የደኅነነት ጉዳያችን ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰም በአግባቡ ማሳየት ተስኖታል። የመፅሀፉ መሰረታዊ ጭብጥም ምን እንደሆነ ግራ ያጋባል። መጽሐፉ በዛሬው ፖለቲካችን ውስጥ ህልውናቸው ያከተሙ ጉዳዮችንም እንደ ሥጋት ሲመለከት ይታያል። የአንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሕዝብና አንድ አገር ፍላጎት ያላቸው ወገኖች በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሥጋቶች አስመስሎ ማቅረቡም ከዚህ ይመነጫል ።

ላክን የተባለው ፈላስፋና ሐያሲ ሁል ጊዜም ጸሐፊውን እንደ ሌለ አስቦ መናገር አለበት ይላል። ይህም ነገሮችን በነፃነት ለማንሳት ከማገዙም በላይ የጸሐፊውን ሰብዕና ከመጽሐፉ ለይተን እንድናወራ ይረዳናል። እኔ የሔድኩበት መንገድም በዚህ የተቀነበበ ነው። ተመራማሪው፣ መምህሩና ወታደሩ አበበ ተክለ ኃይማኖትን (ሜ/ጄነራል) በዘርፉ ያላቸው ልምድና እውቀት ባያጠራጥም እሱን ለእኛ ያስተላለፉበት መንገድ ግን ከትችት የሚፀዳ አይደለም ።

ይነገር ጌታቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በመሥራት ላይ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። በኢሜል mar.getachew@gmail.com አድራሻቸው ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here