የአልሸባብ ማንሰራራት እና የኢትዮጵያ የደኅንነት ሥጋት

0
1272

ራሱን የምሥራቅ አፍሪካ አልቃይዳ ክንፍ በማለት የሚጠራው አል ሸባብ ውልደት የዚያድ ባሬ መንግሥት መውደቅና የተፈጠረውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ተጠናክሮ የወጣ የሽብር ቡድን ነው። አንድ ጊዜ ጠንከር ሌላ ጊዜ ደግሞ ደከም ብሎ የሚታየው አልሸባብ፥ ኢትዮጵያ ላይ ባወጀው ተደጋጋሚ ጂሃድና በደቀነው የአገር ደኅንነት ምክንያት የኢትዮጵያ መካላከያ ሠራዊት ሶማሊያ ድረስ በመግባት በወሰደው እርምጃ ቡድኑን አዳክሞታል፤ ብሎም ህልውናውን ወደ ማክሰም ደረጃ አድርሶት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ይሁንና አል ሸባብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፍሪካ ቀንድ ሥጋት በመሆን ከማንሠራራት አልፎ ወደ ማጥቃት ተሸጋግሯል። ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ አካል በመሆኗ አገር ሰላም ደኅንነትን እንዲሁም የአካባቢው ፀጥታ ከማስጠበቅ አንፃርና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ርዕሱን የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

የአል ሸባብ – ውልደት፣ ዕድገትና መዳከም
ምሥራቅ አፍሪካን በስፋት በሽብር ቀጠናነት ካስፈረጇትና ቀጠናውን የሥጋት ብሎም የጦርነት ቀጠና ካደረጉት በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል በሶማሊያ ወጣቶች የተመሰረተው “አል ሸባብ” የተሰኘ የሽብር ቡድን ነው። አል ሸባብ ሕንድ ውቅያኖስን ተንተርሶ የአፍሪካን ቀንድ በሥጋት ውሎ እንዲያድርና በምዕራባውያን ዘንድ “የሞት ቀጠና” እስከመባል የደረሰበት የሰላምና መረጋጋት እጦት ምንጭ መሆኑንም በርካቶች ይስማሙበታል።

ይህ ቡድን ውልደቱ ታላቋን ሶማሊያን ለመመስረት አስቦ ቅርብ ያደረውን የሶማሊያን አምባገነን መሪ ዚያድ ባሬ ከሥልጣን መወገድ ተከትሎ አገሪቱ ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነቶች በመግባቷ ነበር። 1983 ግብዓተ መሬቱ የተፈፀመው የዚያድ ባሬ መንግሥት ሶማሊያን ግን ወደማትወጣበት እና የዕድሜ ልክ የቤት ሥራ አሸክሟት ነበር የሔደው።

በቀዳሚነት ሶማሊያን እና ጎረቤት አገራትን በተለይም ደግሞ ኬንያን እና ኢትዮጵያን የጦርነት ዓውድማ በማድረግ ግንባር ቀደሙ አል ኢትሃድ አል ኢስላሚያ የተባለው የዚያድ ባሬ መንግሥት ርዝራዥ ነበር። ይህንን ቡድን አሸባሪ ነው ብሎ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለመፈረጅ አሜሪካንን የቀደማት አልነበረም። ጊዜው ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር መንበረ መንግሥቱን በያዘበት ወቅት ላይ ነበር። ይህ እስላማዊ አክራሪ ድርጅት ኢትዮጵያን ለማተራመስ የቁጣ ሽመሉን በምሥራቁ የአገራችን ክፍል ማሳረፍ የጀመረው። ለጦርነት እምብዛም አዲስ ያልነበረው የያኔው ኢሕአዴግ የጥቃት ቅልበሳውን በተሳካ ሁኔታ አሳክቶ በኦጋዴን አሸዋማ መሬቶች ላይ የአል ኢትሃድ አል ኢስላሚያን ግብዓተ መሬት ፈጽሟል።

የአል ኢትሃድን መዳከም ብሎም ወደ መቃብር መውረድ ተከትሎ ከደቡባዊ ሶማሊያ “አል ሸባብ” (የቃሉ ትርጉሙ ወጣቶቹ ማለት ነው) ጉልበቱን አጠንክሮ ብቅ አለ። ይህ ቡድን ከመንግሥት እኩል ግብር ይሰበስባል፣ የራሱ ምጣኔ ሀብት መደጎሚያ የንግድ ስርዓት አለው፣ በሕንድ ውቅያኖስ የሚያልፉ የኀያላን አገራት ንብረት የሆኑ የንግድ መርከቦችን ሳይቀር በማገት ተደራድሮ በርካታ ዶላሮችን ያፍሳል። ይህ ብቻ ሳይበቃው በሶማሊያ በተለይም ደግሞ ከመናገሻዋ ሞቃዲሾ እስከ ወደብ ከተማዋ ኪስማዮ ድረስ ጠንካራ መረቦችን ዘርግቶ የተለያዩ የኑሮ ስርዓቶችን በመገንባት የሕዝቡን ኑሮ በስቃይ የተሞላ እንዲሆን ማድረጉ የሚታወስ ነው።
አል ሸባብ በአገር ውስጥ ብቻ ሳያበቃ በኢትዮጵያ ላይ ከአንዴም ሰባት ጊዜያት ጅሃድ (“ቅዱስ ጦርነት”) አውጇል።

አል ሸባብ ኢትዮጵያን የማጥቃት የዘመናት ህልም አለው የሚሉት የቀድሞው ፖለቲከኛ ሙሼ ሰሙ፣ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይል በኢትዮጵያውያን ላይ ጀሃድ አውጇል ብለዋል። በውስጡ “የታላቋ ሶማሊያ ምሥረታ” የዚያድ ባሬ መንፈስ እየተቀሰቀሰ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ወገኖችን ጨፍልቆ ለመውሰድ ከመቋመጡም ባሻገር፣ “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት” በሚለው ያረጀና ያፈጀ መፈክር አንግቦ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን “ነፃ ማውጣት” እንደ ግብ እንዳስቀመጠም የሚነገር እውነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ የአልቃይዳ ክንፍ በማለት ራሱን ከአልቃይዳ ጋር የሚያስተሳስረው አል ሸባብ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2000 ግን ቀጥተኛ እና የተደራጀ ጦርነት ኢትዮጵያ ላይ በማወጅ እብሪቱን ጎረቤቱ በሆነቸው አገር ላይ አሳይቷል።

በዚህ ጊዜ ግን እንደቀደሙት ዓመታት ወራሪው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ እስኪገባ አልተጠበቀም። የጦርነቱ ዓውድማ በራሱ በአል ሸባብ ሜዳ ላይ ለማድረግ የኢፌዲሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሙሉ ትጥቁን ይዞ ወደ ሶማሊያ ተመመ። በርካታ ወታደሮችን ኢትዮጵያ መስዕዋት ብታደርግም፥ አል ሸባብ በስፋት ተቆጣጥሮት ከነበረው ሞቃዲሾ እና አካባቢዋ ለመሸሽ በመገደዱ ወደ ትውልድ አገሩ ኪስማዩ አፈግፍጓል።

በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ምርምሮችን በማካሔድ በቀጠናው ጉዳይ ላይ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑት የቀድሞው የቢቢሲ ጋዜጠኛና የአፍሪካ ዴስክ አርታዒ የነበሩት እንዲሁም በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ላይ በርከት ያሉ መጻሕፍት በመጻፍ የሚታወቁት ማርቲን ፕላውት በበኩላቸው በጎረቤት አገራት ከሚገኙ ሶማሊያውያንና በዘር የሚገናኙ ሱማሌዎች ከሚገኘው ድጋፍ ባለፈ የኤርትራን ድጋፍ ማቆም ተከትሎ ከአፍሪካ ቀንድ በኩል ከመንግሥታት የሚደረግለት ድጋፍ ማሽቆልቆሉንም ለአል ሸባብ መዳከም በምክንያትነት ተጠቃሽ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለቀጥታ ፍልሚያ ሶማሊያ የገበው የኢትዮጵያ ጦርም ሶማሊያን በማረጋጋቱ ረገድ ከፍተኛ ሥራ በመሥራትና የአገሪቱን የፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት በመመልመል እና በማሰልጠን በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ነፃ የወጡ መሬቶችን በማስረከብ ወደ መንግሥት አስተዳደር እንዲገቡ አድርጓል።በእነዚህ ዓመታት ግን ኢትዮጵያ ከአልሸባብ ጋር ባደረገችው የሞት ሽረት ትግል በርካታ የሰራዊት አባላትን ገብራለች፣ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብም ወጪ አድርጋለች።

የአል ሸባብ መልሶ ማንሰራራት
ከዓመታት በኋላ የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ከፍተኛ ተልዕኮ ያለውን የሰላም አስከባሪ ጦር በማዝመት የሶማሊያን ዘላቂ ሰላም ለማጎናጸፍ ያላሰለሰ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ይሁን እንጂ ይህ የሽብርተኛ ቡድን በቀደሙት ዓመታት የነበረውን የተዳከመ አቅም አሰባስቦ እያንሰራራ ብሎም እየጎለበተ ይመስላል። የገጠር ትግሉን በመተውም ከተማ ላይ በማተኮር የትርምስ ተግባሩን እያጧጧፈ ይገኛል።

“የአል ሸባብ አቅም ተዳክሟል ወይም በርትቷል የሚለው ነገር በአንድ ጊዜ የሚመለስ ጉዳይ ሳይሆን ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው” ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰላምና ደኅንነት ተቋም መምህርና ተማራማሪ ዳንኤል ከበደ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ ከጊዜ ወዲህ በዋና ዋና ከተሞች ላይ በዛው በሶማሊያ የሚያደርሰውን ጥቃት በተመለከተ ከዚህ ቀደም ወደ ገጠሩ አካባቢ የነበረው ይዞታው በአሚሶም እና ጥምር ኀይሎች ስለተወሰደበት ወደ ከተማ አባላቶቹን አስርጎ በማስገባት ጥቃቶች እየፈፀመ እንደሚገኝ ነው የሚናገሩት ዳንኤል “እኔ በነበርኩበት በፈረንጆች 2014/15 ቡድኑ በበርካታ አካባቢዎች ግብር የሚሰበስብበት አጋጣሚዎች እንደነበሩ ተመልክቻለሁ” ይላሉ። እነዚህ ግብር የሚሰበስብባቸውና የሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ስለተወሰዱበት ወደ ከተማ ሰርጎ የገባ ቢሆንም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን ለማሳየትም በከተማ የሚያደርጋቸው ጥቃቶች የበለጠ ትኩረት ሰጥቷል።

በቅርቡ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የከንቲባ ቢሮ አቅራቢያ በአንዲት እንስት አጥፍቶ ጠፊ በተፈፀመ ጥቃት የተማዋ ከንቲባ በፅኑ ጨምሮ በርካቶች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሶ እንደነበር አለም አቀፍ የዜና አውታሮች እየተቀባበሉ ሲዘግቡት የነበረ ጉዳይ ነው። ጥቃቱንም ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን የወጣቶቹ ቡድን አልሸባብ አፍታ ሳይቆይ መውሰዱን አስታውቋል።

በዚህ ጥቃት የሞቃዲሾ ከተማ ከንቲባ አብድረህማን ኦማር ኡስማንን እስከ ወዲያኛው እንዲያሸልቡ አድርጓል። ከንቲባው ጥቃት በደረሰባቸው ወቅት ለተጨማሪ የሕክምና ዕርዳታ ወደ ኳታር አቅንተው የነበረ ቢሆንም ሐምሌ 25/ 2011 ከወደ ዶሃ ዜና ዕረፍታቸው ተሰምቷል። የአፍሪካ ሕብረት መራሹ የሰላም አስከባሪ አሚሶም በስፋት በሚንቀሳቀስበት ወቅት ይህን አይነት ከባድ ጥቃት ያውም በከፍተኛ መንግስት ሹም እና መስሪያ ቤት ላይ ማድረሱን ዳንኤል አሚሶምን መነሻ አድርገው ይናገራሉ።

ዳንኤል የአሚሶምን የሰላም ማስከበር ቁመናም ሲገመግሙት ልዩ ተልዕኮው በተገቢው ሁኔታ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ። ከአሚሶም የሰላም ማስከበር ጦር ውስጥ 20 በመቶ የኢትዮጵያ መከላከያ ኀይል የተወጣጣ ቢሆንም 63 በመቶ የሚሆነውን የሰላም ማስከበር አካባቢውን ደግሞ የሚሸፍነው ይኸው 20 በመቶው የኢትዮጵያ ኀይል እንደሆነም ይጠቁማሉ። እንደምክንያት የሚያስቀምጡት ደግሞ አል ሸባብ ከቀጥተኛ ውጊያ ይልቅ የደፈጣ ውጊያን ስለሚከተልና የኢትዮጵያ ጦርም ለዚህ አዲስ ባለመሆኑ በቀላሉ ሊቆጣጠረው እንደሚቻለው ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ እንደ የሰላምና ደኅንነት መምህርና ተመራማሪው ዳንኤል አስተያየት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከአል ሸባብ ጥቃት ኢትዮጵያ በብቃት ራሷን መከላከል ትችላለች ብለው ለማመን እንደሚቸገሩ ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል። “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድንበር ላይ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት እየተሳበ ወደ መሃል አገር እየተመለሰ ነው የሚገኘው ምክንያቱ ደግሞ በአገር ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ስለሚገኝ አል ሸባብ ጥቃት ለማድረስ መግቢያው ከመቼውም በተለየ ክፍት ስለሚሆን” የሚሉት ምሁሩ አል ሸባብ በዋናነት እንደመግቢያ የሚጠቀመው ምሥራቃዊውን ክፍል በተለይ ደግሞ ሱማሌ ክልልን በመሆኑ አንድ ባሕል፣ አንድ ጎሣ፣ አንድ ሃይማኖት ባለው ኹለት ሕዝብ ውስጥ ሰርጎ መግባት ቀላል እንደሚሆነው ይጠቁማሉ።

በሰላምና ደኅንነት ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎችም ከዳንኤል ጋር ይስማማሉ፤ ሌሎች ምክንያቶችንም በምሁራኑ ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሔደ ካለው ለውጥ ጋር በተያያዘ የደኅንነት መዋቅሩ መዳካም ለሰርጎ ገቦች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ሆነው ወደ ክልሉ በመግባት የደኅንነት ሥራን የሚሠሩ ሰዎችንም ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ። በተጨማሪም በሱማሌ ክልል የሚገኙ ያኮረፉ ቡድኖች ለውጭ ኀይሎች መጠቀሚያም የሚሆኑበት አጋጣሚዎች ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ነው ይላሉ።

ዳንኤል በሶማሊያ አሁን የሚገኘው የመንግሥት ቁመና መሰረት አድርገውም ሲናገሩ፤ የሶማሊያ መንግሥት መሣሪያ እንኳን እንዳይገዛ ዓለም ዐቀፍ ማዕቀብ ስላለበት በቀጥታ ለመታጠቅም ስለሚቸገር አል ሸባብን ለመዋጋት ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚኖርበት ገልፀው በተባበሩት መንግሥታት በኩል ትጥቅ እንደሚያገኙም ተናግረዋል።
ማርቲን ፕላውት የዳንኤልን ሥጋት ይጋራሉል። በእርግጥም የሶማሊያ መንግሥት መዳከም ብቻ ሳይሆን አል ሸባብም እየተጠናከረ እንደመጣ ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ የሶማሊያ መንግሥት አል ሸባብን ለመዋጋት ያለው ቁርጠኝነት መቀነሱ በቀዳሚ ደረጃ የሚጠቀስ ሲሆን ሌላው ነጥብ ደግሞ አል ሸባብ የውጭ ዕርዳታ በተጠናከረ መልኩ ማግኘቱ ተጠቃሽ ነው። በዚህም ረገድ ከኳታር መንግሥት ቀጥተኛ ዕርዳታ እንደሚደርሰው የኒው ዮርክ ታይምስን ዘገባ መሰረት አድርገው ማርቲን ምላሻቸውን በማስረጃነት አስደግፈዋል።

ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች አል ሸባብ ከመስከረም አንዱ (አሜሪካ) ጥቃት ከነበረበት በላይ አሁን ጠንካራ ነው በሚል ስለሚነገረውጉዳይ ማርቲን ፕላውት የዳንኤልን ሃሳብ በመጋራት ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ለመሆን ጥናት ያስፈልጋል ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። በሰላም ማስከበሩ ረገድ የተሰማሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦራቸውን መጠን በአንድ ሺሕ ለመቀነስ በዚሁ ዓመት መጀመሪያ ላይ መወሰኑን ጠቅሰው ይህ ደግሞ አል ሸባብ ተመልሶ ቀድሞ ያጣቸውን ቦታዎች ለመያዝ ከፍተኛ ዕድል እንደሚሰጠው ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

ማርቲን ፕላውት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ኦጋዴንን ለመጠቅለል ታስቦ በነበረው ጦርነት ሶማሊያ ጦር በለስ ባይቀናው እና እንደተዳከመ ቢቆይም አሁኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብሔርን መሰረት ያደረገ መከፋፈል የቀደመውን የሶማሊያን ምኞት ሊያሳካ የሚችልበትን ዕድል ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን በማስቀመጥ የወደፊቱን መገመት በርግጥ ከባድ መሆኑን ግን አልሸሸጉም።

ኢትዮጵያ እንደዒላማ
አይኤስ ነፃ የሚያወጣቸውንና ካሊፌቱን የሚያውጅባቸውን አገራት በገለጸበት ካርታ ላይ እንዳስቀመጠው፣ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ዒላማ ናት። Ethiopia’s Strategic Importance: US National Security Interests at Risk in the Horn of Africa September 12 በሚል ርዕስ ላይ እንደሚነበበው ትንታኔ፣ ለአልቃኢዳ የሚታዘዘው አል ሸባብም ሆነ፣ አይኤስ ከኢትዮጵያ ግዛቶች ቆርሶ በመውሰድ ታላቋን ሶማሊያ መፍጠር ላይ ልዩነት የላቸውም። ኹለቱም እንግሊዞች ቀብረውት የሔዱትንና ኋላ ላይ ዚያድ ባሬ ሊያፈነዳው የሞከረውን የታላቋ ሶማሊያ ፕሮጀክት ይደግፉታል።

ይሁን እንጂ አል ሸባብ ከአይኤስ በበለጠ የኢትዮጵያን ወጣቶች ለመማረክ እየሠራ ነው። ለዚህም ከቡድኑ የሥራ ቋንቋዎች አንዱ አፋን ኦሮሞ እንዲሆን ወስኖ በዚሁ ቋንቋም የተለያዩ መግለጫዎችን እያወጣ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት አል ሸባብ በፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎቹ ለወትሮው ከሱማሊኛ በተጨማሪ ይጠቀም የነበረው ቋንቋ እንግሊዝኛ፣ አረብኛና ስዋሒሊ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አፋን ኦሮሞም ተጨምሯል። ምናልባትም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉና የተከፉ ወጣቶችን ትኩረት ለመሳብ የተከተለው ዘዴ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

በዚህ ረገድ አይኤስ ግልጽ ነገር የለውም። በሚታወቁት ልሳኖቹ (‘አማቅ’ እና ‘ዊላያት’) በሶማሊያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የለቀቃቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ሆኑ ጽሑፎች አዘውትሮ ከሚጠቀምበት ቋንቋ ተሻግሮ እንደ አል ሸባብ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች ሲጠቀም አልተስተዋለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አል ሸባብ ከፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጎን ለጎን ወደ ጥቃት ማድረስ መሸጋገሩን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። ለምሳሌ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ጥር 10/2011 በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተግባር ላይ የነበሩ ወታደሮች ኮንቮይ ላይ የአል ሸባብ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸውን ያስታወቀው ማስታወስ በቂ ነው።

የአገር መከላከያ ሠራዊት አራት መኪኖች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ የሠራዊቱ አባላት ተገድለዋል የሚል ዘገባ የወጣ ቢሆንም፣ የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ጥቃቱ ምን ያክል ጥፋት እንዳደረሰ አልገለጸም። ይሁንና ሠራዊቱ የአል ሸባብን ጥቃት ተከትሎ ጠንካራ የማጥቃት እርምጃ ወስዷል።

የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ እንዳመለከተው “በሠራዊቱ ላይ ጥቃት የደረሰው ወታደራዊ የአጀብ ጉዞ (ኮንቮይ) ከቡራሃካባ ወደ ባይዶአ በመጓዝ ላይ እያለ ሲሆን፣ ሠራዊታችን ጥቃቱን በጽናት በመመከት ኮንቮዩን ባይዶአ ይዞ ገብቷል” ብሏል።

ሠራዊቱ ካሁን ቀደም በርካታ የአል ሸባብ ጥቃቶችን በመመከት አል ሸባብን ያዳከመው መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው፣ በአሁኑ ጥቃትም አል ሸባብ በቀቢፀ ተስፋ የሠራዊቱን ንቅናቄ ለመግታት ሙከራ እንዳደረገ ማስታወቁ ይታወሳል።

የመከላከያ ሚኒስቴር በተቋሙና በሠራዊቱ ላይ ሁለንተናዊ የሪፎርም ሥራ እያከናወነ መሆኑን፣ ይኼንንም አስመልክቶ የ2011 ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሣሥ 30/ 2011 ባቀረበው ሪፖርት ላይ፣ የወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ እና ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ መግለጻቸው ይታወሳል።

በሶማሊያ መሽጎ የሚገኘው የአሸባሪው አል ሸባብ ቡድን በአገሪቱ ተሰማርቶ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ አደጋ ለማድረስ ዝግጅት አድርጎ እንደነበር ተገልጾ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሊሰነዘርበት የነበረውን ጥቃት መመከቱን አብሮ ተገልጿል።

ሙሼ አሁን ባለው ሁኔታ የአል ሸባብን ጥርስ ረግፏል ብሎ መዘናጋት አያስፈልግም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። ማሸበሩ ባይሳካለትም የአክራሪነትና የጽንፈኛ አስተሳሰቡ ከሰላማዊ የሃይማኖት አስተሳሰቦች ጋር እየተቀላቀለ በመራገቡ ይህንና መሰል ኀይሎችን ነጥሎ ማጋለጥና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እንዲናበብ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከሶማሊያ መፈርጠም ጀምሮ የነበረው አል ሸባብ መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔ (ከሦስት ዓመት በፊት በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ተገድሏል) በ2016 (እ.ኤ.አ.) የሰጠው መግለጫ አባባሉን ያረጋግጣል። አል ሸባብ ሶማሊያዊያንን አስታጥቶ ለፍጅት ከመዳረጉም በላይ ከአፍጋኒስታን፣ ከፓኪስታን፣ ከአሜሪካና ከጀርመን እየመለመለ ባስገባቸው ሽብርተኛ ጀሌዎቹ በመመካት በተለይከዘጠኝ ዓመታት በፊት በተፈፀመው እና በዋናነት የኢትዮጵያ የባህል ምግብ አዳራሽን ኢላማ ባደረገው የኡጋንዳዋ መናገሻ በሆነችው ከካምፓላው ቦምብ ጥቃት በኋላ እንዲህ ብሏል። “በካምፓላ የደረሰው ጥቃት የመጀመርያው ነው። ገና ምን ዓይታችሁ ጦርነቱን በኬንያና በኢትዮጵያ ምድር እናደርገዋለን። አይደለም እዚህ ጎረቤት አሜሪካም እንድትለበለብ እናደርጋለን። ሸሪዓ በመላው ዓለም አገሮች ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ ጦርነቱ ሊያበራ አይችልም” ነበር ያለው።

አል ሸባብ – የአፍሪካ ቀንድ ሥጋት
መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ያደረጉ የምዕራብ አገራት ኢምባሲዎች፤ ዜጎቻቸውን ወደ ሶማሌ ክልል እንዳይጓዙ የሚከለክል ደኅንነት ማስጠንቀቂያዎችን ማውጣታቸው በስፋት እየተነገረ ይገኛል ለዚህ ደግሞ አሜሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ አገር ናት። አሜሪካንም ተከትሎ ካናዳና እንግሊዝ ጋምቤላን ጨምሮ አፋርና ሶማሌ ክልል እገታ፣ ሕዝባዊ አመፅ፣ የቦንብ ጥቃት ይኖራል በሚል የጉዞ ክልከላዎቻቸውን ለዜጎቻቸው አስተላልፈዋል። ይህን በሚመለከት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐምሌ 25/2011 በጽሕፈት ቤታቸው ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹በየጊዜው የውጭ አገር ኢምባሲዎች እንደዚህ ዓይነት መግለጫ ያወጣሉ›› ሲሉ ጀምረው ዜጎቻቸውን በደድንበር አካባቢ እንዳይሔዱ ያስጠነቀቁበት ያልታሰቡ ጥቃቶች ይኖራሉ ብለው በማሰባቸው እንደሆነና የኢትዮጵያ መንግስትም በቅርበት እየተነጋገረ ነገሮችን በማረጋጋት የጉዞ ዕጋዳዎችን እንዲያነሱ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በምሥራቃዊ ጎረቤት አገር ከ20 ዓመታት ለበለጠ ረጅም ጊዜ የአገሪቱ ዜጐች ብቻ ሳይሆኑ ቀጣናውንም ሲታመስ የከረመው አል ሸባብ ልክ እንደ አልቃይዳ፣ አይኤስ፣ ቦኮ ሐራም፣ የአፍጋኒስታን ታሊባንና ሌሎችም ሁሉ ተቀራራቢ ጽንፈኛና አውዳሚ ዓላማን የሰነቀ ቡድን ነው።

በሶማሊያ የነበረውን ግብረ ሽብር ከእስልምና ፍርድ ቤቶች ሸንጐ የተረከበው አል ሸባብ እንደቀደሙት ሁሉ በጎረቤት አገሮች ላይ ጅሃድ በማወጅ ሶማሊያውያንን መፈናፈኛ ያሳጣ ሲሆን፣ እስከ 60 ሺሕ የሚደርሱ የታጠቁ ሸማቂዎች እንደነበሩትም ሲነገር ቆይቷል። ይህ ኀይል የሶማሊያን ወደቦች በመቆጣጠር የዓለም መንግሥታትን ትኩረት ስቧል። ይፋዊ ትስስር መኖሩ በመረጃ ባይገለጽም ከአልቃይዳ ጋር በነበረው የግብረ ሽብር መስተጋብር ምዕራባውያንን (በተለይም አሜሪካን) ዋነኛ ጠላት አድርጎ በመንቀሳቀስ በኬንያ፣ በታንዛኒያና በኡጋንዳ የሽብር ተግባራትን ፈጽሟል። ኢትዮጵያ ላይም ዝቷል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት ዕውቅና ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ በማዝመት የሶማሊያውያንን ጣርና ስቃይ ከመነቀስ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረውንም ሾተል ለመመለስ ተንቀሳቅሳለች። ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ “አሚሶም” በተሰኘው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኀይል ውስጥ ተቀላቅላ የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ነው። ከወራት በፊት ጥምር ኀይሉ በተለይም ከሶማሊያ የሽግግር መንግሥት የፀጥታ ኀይሎች ጋር በመሆን በወሰዳቸው ዕርምጃ፣ አክራሪው የአል ሸባብ ኀይል በርካታ ይዞታዎቹን ከመልቀቁም ባሻገር እንደተዳከመም ይታወቃል።

ኢትዮጵያን አሁንም ለሽብር ተጋላጭ አገር ያደረጋት ተጠናክሮ የቀጠለው የዓለም ዐቀፍ እስላማዊ ሽብርተኝነት ዒላማ ውስጥ ያለች በመሆኗ ነው። ለዚህም በአንድ በኩል ያለንበት ቀጣና አስተዋፅዖ ያደረገ ሲሆን፣ ጽንፈኞች “የክርስቲያን ደሴት” በሚል ታፔላ የምዕራባዊያንና የጽዮናዊያን እህት አገር አድርገው በመሳላቸው እንደሆነ ሙሼ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ይህንን መመከት የምትችለው በየክልሎቹ የሚታዩትን ቀውሶች በመቅረፍ፣ ደኅንነቱንና መከላከያውን በማጠናከር መሆኑን የሚያወሱት ሙሼ፣ በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ የሚታዩት ቀውሶችና አለመረጋጋቶች የደኅንነቱ ክፍል መሳሳት መሆኑን ይገልጻሉ። አክለውም፣ መንግሥት አሁንም የደኅንነት መዋቅሩን በፍጥነት ማስተካከል ካልቻለ፣ የቀጠናው አለመረጋጋት ለኢትዮጵያ ወላፈን ሊሆንባት እንደሚችል ያስገነዝባሉ። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን በራሳችን ጉዳይ ልዩነቶች ቢኖሩንም በውጪ ኀይሎች ላይ ግን ሁሌም አንድ ስለሆንን ማንኛውም ጠላት ይህንን በሚገባ የሚያውቀው ይመስለኛል ሲሉ ሙሼ አስተያየታቸውን አጠቃልለዋል።
ኤፍሬም ተፈራ እና ሳምሶን ብርሃኔ ለዚህ ጽሑፍ አስተዋፅኦዖ አድርገዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here