በቀን የ35 ሺሕ ሰዎችን ያህል የመመ’ገብ አቅም ያለው የአንበጣ መንጋ ኢትዮጵያን ያሰጋል

0
577

በምሥራቅ አፍሪካ ከባድ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የበርሃ አንበጣ መንጋ በሶማሌ ክልል ከሳምንታት በፊት መከሰቱ ታወቀ። አንበጣዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉ መሆናቸውን የገለጸው የግብርና ሚኒስቴር፥ አሁንም በተለያዩ ክልሎች መንጋው እንዳይከሰት ሥጋት መኖሩን ጨምሮ አስታውቋል።

በጣም አነስተኛ ሚባለው የበረሃ አንበጣ መንጋ እስከ ዐሥር ኪሎ ሜትር ሊረዝም እንደሚችል እንዲሁም በቀን 35ሺሕ ሰዎች ሊመገቡት የሚችሉትን ያህል የመመገብ አቅም እንዳለው ጥናቶች ጠቁመዋል። አንድ የበርሃ አንበጣ በየቀኑ ከኹለት ግራም በላይ ወይም የራሱን ክብደት ያክል ምግብ ይወስዳል። በአንድ ሳምንት ውስጥ 3 ጊዜ እንቁላል የመጣል አቅም ያለው አንበጣው፥ በአንዴ ከ80 እስከ 120 እንቁላሎችን ከመፈልፈሉም ባሻገር አዳዲሶቹ አንበጣዎችም ከትልልቆቹ አንበጣዎች በብዙ እጥፍ የበለጠ ምግብ ይመገባሉ።

ሶማሌ ክልል፣ የምሥራቅ ኦሮምያ ዞኖች፣ ድሬድዋ፣ አፋር፣ አማራ እና ደቡባዊ ትግራይ ለመራባት ምቹ በመሆናቸው ክፍተኛ ተጋላጭነት ሊኖራቸው እንደሚችል በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ዘብዲዮስ ሰላቶ ለአዲስ ማለዳ አሰታውቀዋል። አንበጣው ሊራባ የሚችለው ዝናባማ የሆነ አየር ሲኖር እና አረንጓዴ ዕፅዋት በሚበዛበት አካባቢ ሲሆን እነዚህ አከባቢዎች ላይ ሊፈጠር የሚችለው መንጋ ቀድሞ መከላከል ካልተቻለ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችልም ጨምረው ገልጸዋል።

መንጋውን በከፍተኛ ርብርብ በ24 ሰዓታት ውስጥ መቆጣጠር ካልተቻለ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ በቀላሉ በመዛወር አደጋውን የከፋ ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ዘብዲዮስ አስጠንቅቀዋል።

በአገሪቱ እንዲሁም በቀጠናው ያለውን የግብርና ምርት ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ የጣለው መንጋ፥ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያትም የበለጠ የመራባት እና ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩሉለት እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በመሆኑም ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ በቀጠናው የግብርና ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማሳደር የአገራትን የምግብና የኑሮ ሁኔታ ፈታኝ በማድረግ በአካባቢው ያለው ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴን ሊጎዳ እንደሚችል ዘብዲዮስ ጨምረው ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት መሰል የአንበጣ መንጋ በርካታ የሰሜን ምሥራቅ አካባቢዎችን ያጠቃ ሲሆን ከፍተኛ የሰብል ጉዳት ማድረሱም ታውቋል። ሥጋቱ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያንና ሰሜን ሶማሊያን እኩል በሚባል ደረጃ ተጋላጭ ሊያደርጋቸው ስለሚችል የዓለማቀፍ ማኅበረሰብ እገዛ ከወዲሁ ያስፈልጋልም ተብሏል።
በተለይ በዝናብ ወቅት አንበጣ እንዲራባ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል የሚባል የአየር ንብረት ካላቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

በግንቦት ወር መንጋው ከየመን ተነስቶ መዳረሻውን ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርግ ይችላል የሚል መረጃ ደርሶናል ያሉት ዘብዲዮስ፥ ከዚህ ቀደም በ2006 በተመሳሳይ ከየመን ተነስቶ ወደ ሶማሌ ክልል፣ ጎጃም፣ ትግራይ እና በተለያዩ አካባቢዎች ገብቶ ከፍተኛ የሆነ አደጋ አድርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።
ሰለሆነም በወቅቱ የተከሰተው አደጋ መደገም የለበትም ብሎ መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here