27 የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሕጉ ፀረ-ዲሞክራሲያ ፅንሰ ሐሳብ አለው አሉ

0
550
  • የሕዝብ ተወካዮችንም ሆነ የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ አሻሽሎ ለተወካዮች ምክር ቤት የላከው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅ ለፓርቲዎች ምዝገባ መመዘኛነት እና ለእጩ ተወዳዳሪዎች የቀረበው መስፈርት ተቀባይነት የሌለውና የመድብ ፓርቲ ስርዓትን የሚጨፈልቅ ነው ሲሉ 27 የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቀሱ። ፓርቲዎቹ፣የምርጫውን አሸናፊ አስቀድሞ የሚበይን የፀረ ዲሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብ የያዘ መሆኑ አገሪቱን ወደ አልተፈለገ የፖለቲካ ውዝግብ የሚወስድ ሕግ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል።

ፓርቲዎቹ በተናጠል እና በቡድን ሆነው ያቀረቧቸውን ሐሳቦች ወደ ጎን በመተው ለጥቂቶች ብቻ የታሰበ በሚመስል ሁኔታ አሻሽሏል ሲሉ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል። ሐምሌ 25/2011 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፣ ከዚህ ቀደም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በከፊል የተስማሙበት እንደነበረ እና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን ያላቸውን አቋም በጽሑፍ ለቦርዱ ቢያስታውቁም፣ ስምምነቶችንና ማሻሻያዎችን ቦርዱ ወደ ጎን አድርጓቸዋል ብለዋል።ይህ ረቂቅ አዋጅም የሕዝብ ተወካዮችንም ሆነ የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ አግኝተነዋል ሲሉ አስታውቀዋል።

አንኳር እና ወሳኝ የሆነውን የምርጫ ስርዓት ሳይነካ፣ የሕዝብ ተወካዮችም ሆነ የክልልም/ቤቶች መቀመጫ ብዛት ሳያሳስበው በሕገ መንግሥት ሽፋን አሳሳቢውን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ማለፉ ሌላው የረቂቅ ሕጉ አፋኝነት ማሳያ ነው ሲሉም አክለዋል። እንዲሁም የአገሪቱ የዜጎች ቁጥር እና በየአካባቢው ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሻቅቦ ባለበት በአሁኑ ወቅት “ረቂቅ አዋጁ ከስምምነታችን ውጭ ስለሆነ፣እንደገና በስፋት እንድንወያይበትና የተሰማማንበት ስምምነት እንዲካተት፤ አሁን እንዲፀድቅ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከፓርቲዎች ሐሳብና ስምምነት ውጪ በመሆኑ የሚንስትሮች ምክር ቤት ጉዳዩን በጥሞና እንዲመለከተው” ሲሉ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል። በረቂቅ አዋጁ ላይ በግልፅ የሚታዩ የሕግ ክፍተቶች እና አፋኝ አንቀፆች ተለይተው ሳይስተካከሉና ሳይሰረዙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ረቂቁን ወደ ውሳኔ እንዳያቀርበው ጠይቀዋል።

መግለጫውን ከሰጡት 27 ፓርቲዎች መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና አንድነት ፓርቲ ይገኙበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here