ከሴት ሕፃን ልጅና ከችግኝ፡ የማን ሕይወት ይበልጣል?

0
974

ሴት ሕፃናትን “አስገድዶ” በመድፈር ወንጀል የፈጸሙ አንድ አዛውንትንና ችግኞችን በመንቀል በተከሰሰ ግለሰብ ላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈባቸውን ቅጣት በማነፃፀር ጽሑፋቸውን የሚጀምሩት ቤተልሔም ነጋሽ፥ የሴት ሕፃናትና ሴቶች ደኅንነት ለመንግሥት አንገብጋቢ አይደለም ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። ሐሳባቸውንም ለማጠናከር አሳማኝ ያሉዋቸውን ማስረጃዎች ጠቃቅሰዋል።

ገና ርዕሱን ስታዩ “የምን ቀልድ ነው?” ልትሉ ትችላላችሁ። አልያም “ሰውና ችግኝ ታወዳድሪያለሽ?” ግጥም አድርጎ ሴት ልጅ! ርዕሱን የወሰድኩት አንድ ሰው ከለጠፈው ትዊተር ላይ ባለፈው ሰሞን በአገራችን የተከናወኑ ኹለት ድርጊቶችን ያነጻጸረ ስላቅ ያዘለ አገላለጽ ነው። አገላለጹ አብሮ የቀረበው አራት ታዳጊ ሴት ሕፃናትን በደፈሩ የ81 ዓመት አዛውንት ላይ ፍርድ ቤት የ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንደተፈረደባቸው ከሚገልጸው ዜና ጋር ነበር። ሌላኛው የታሪኩ ማንጸሪያና የዚህ ጽሁፍ ርዕስ ላይ ያለው ድርጊት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ችግኝ ነቀለ የተባለ ሰው በስድስት ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቱ ነው።

ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ በኹለቱ ፍርዶች መካከል ያለው ልዩነት በእኔ አመለካከት የመጀመሪያው የአራቱ ሴት ሕፃናት ጉዳይ መንግሥት ብዙም ትኩረት የማይሰጠው የወንጀል ጉዳይ ሲሆን ኹለተኛው የተከሉትን ችግኞች የመንቀል ድርጊት መንግሥትን “የመድፈር” የመቃወም ተደርጎ ተወሰደ። ነገር ግን ካየነው የማንንም ሰብኣዊ መብት የማይጥስ የተንኮል ድርጊት ነው።

ከመድፈር ድርጊቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ዜና በፊት (እኔ ባገኘሁበት ቅደም ተከተል) የቀደመው በፋና ዜና ሐምሌ 13 የተዘገበውና “ችግኞችን የነቀለው ግለሰብ በስድስት ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ” የሚለው ሲሆን ድርጊቱ የተፈጸመው በምዕራብ አርሲ ዞን ሄበን ወረዳ ሲሆን ደጋጋ ቀበሌ የወረዳው ፍርድ ቤት ሐምሌ 12 በዋለው ችሎት 177 ችግኞችን የነቀለው ግለሰብ በስድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ተገልጧል።

በመሰማት ቅደም ተከተል ኹለተኛው የአዛውንቱ ሕፃናቱን የመድፈራቸውና የቅጣቱ ዜና ዝርዝር የደረሰኝ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጋርቶ ሲሆን በተለይ እንድመለከተው ሰዎች ሥሜን በጠሩበት በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ በወጣው ዜና ነው።

“በሕፃናት ልጆች ላይ የአስገድዶ መድፈር የፈፀመው አዛውንት በጽኑ እስራት ተቀጣ” ይላል ዜናው ቀጥሎም ፍሬ ነገሩ፡-
“የ81 ዓመት አዛውንት የሆነው ተከሳሽ ሰኢድ አብዱልሃቢብ ሰኔ 27/2008 በአራዳ ክፍለ ከተማ በ12 ዓመቷ ታዳጊ ሕፃን ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በመፈፀሙ፣ በተመሳሳይ ቦታ ግንቦት 2009 እና ጥር 2009 ሰባት ዓመት በሆናቸው ሦስት ሕፃናት ላይ ግብረ ሥጋ በደል የሚመስል ወንጀል በመፈጸሙ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 627/1/ እና 627/3/ የተደነገጉትን በመተላለፉ ክስ እንደተመሰረተበት ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪና የተለያዩ በሽታዎች ያሉበት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የቅጣት ማቅለያዎች ተይዞለት ሰኔ 2/2011ም በዋለው ችሎት 10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል” ይላል።

አስገድዶ መድፈርና የወሲብ ጥቃት በሴቶችና ላይ ከሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ሁሉ አስከፊው ነው። ሴቶች በመደፈር ምክንያት አካላዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ሥነ ልቦናው እና ስሜታዊ ጉዳት ይገጥማቸዋል። በመደፈር ላይ የሚሠሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት መድፈር ወንዶች በሴቶች ላይ ያላቸውን የበላይነት በኀይል ለማስረገጥ የሚጠቀሙበት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው። የሴትን ሰውነት የመቆጣጠር፣ የማዋረድ፣ ዝቅ የማድረግ አስከፊ ድርጊትም ነው፤ ለዚህም ነው ሰውነትን ብቻ ሳይሆን ስብእናንም መድፈር ነው የሚባለው።

በዚህ ረገድ ከላይ በጠቀስኩት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገጽ ላይ የሰፈረው ሐተታም “ተከሳሽ በአራቱም የግል ተበዳይ ሕፃናት ላይ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት ሆኗል” ይላል።

ነገር ግን በአብዛኛው ማኅበረሰቡ ለሴቶች በሚሰጠው ዝቅተኛ ግምትና ቦታ ምክንያት እንዲሁም በተለይ በልጆች ላይ የሚያደርሰውን ከባድ የሥነ ልቦና ጫናና በወሲብ ሕይወታቸው በአጠቃላይ በስብእናቸው ላይ ጥሎ የሚያልፈውን ከባድ ጠባሳ ባለመረዳት ነገሩን በሽምግልና ለመጨረስ፣ ገመናችን ይወጣን ሰው ምን ይለናል (በተለይ ለልጆቹ ዘመድ የሆኑ ወይም ቅርበት ያላቸው ሰዎች ወንጀሉን በሚፈጽሙበት ወቅት) በሚል ሪፖርት ከማድረግ ይቆጠባሉ። በዚህም ወንጀለኞቹ ሳይቀጡ መቅረት ብቻ ሳይሆን ከላይ እንደተጠቀሰው አዛውንት በአንዱ ሳይያዝ (ሳይቀጣ ሲቀር) የሦስት ተጨማሪ ሕፃናትን ሕይወት (ለተከታታይ ወራት ድርጊቱን በመቀጠል) ለማበላሸት እድል ያገኛል።

እንደምታውቁት የወንጀለኛ መቅጫ ሐግ በ2005 ከተሻሻለ ወዲህ አስገድዶ መድፈርን በሚመለከት መሻሻሎች ተደርገው (በጥናት የተደገፈ ማስረጃና ተሳትፎ በሕግ ማሻሻል ሒደቱ ላይ አስተዋጽዖ ያበረከቱት እንደ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ያሉ ተቋማትና ግለሰቡች ምስጋና ይግባቸውና) የተሻለ ሕግ ሆኖ፣ ዝቅተኛ ቅጣት ተቀምጦለት እንደ ተበዳዮቹ ዕድሜና ሁኔታ፣ እንዲሁም ከበዳዩ ጋር እንዳላቸው ዝምድና (አስተማሪ፣ ሞግዚት፣ ጠባቂ፣ በሕፃናቱ የሚታመን ሰው፣ ሊጠብቃቸው ኀላፊነት ወዘተ) ከ5 እስከ 25 ዓመት የሚስቀጣ ወንጀል ሆኗል።

ነገር ግን ማስረጃ አቀራረብ፣ በሕግ አስፈፃሚ አካላት ዘንድ ባለ አስተሳሰብ እና በሌሎችም ምክንያቶች ድርጊቱን መፈጸማቸው የተረጋገጠባቸው ሳይቀር ተገቢውን ፍርድ ሲያገኙ አይታይም። ይህ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ፍትሕ ፍለጋ ሳይመጡ የሚቀሩ ሰዎችን ቁጥር ስንጨምርበት በአስገድዶ መድፈር ላት ፍትሕ ገና ነው እንድንል ያደርገናል።

ነገሬን ሳጠቃልል ከላይ የጠቀስኩት ማንጸሪያ ምሳሌ የሴት ሕፃናትና የሴቶች ደኅንነት ለመንግሥት አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም ለምንለው ክስ እንደማጠናከሪያ ማሳይ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ይህን የምለው ደግሞ የእነዚህ አራት ሴት ሕፃናት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች መገናኛ ብዙኀን ታሪካቸውን ያወጣላቸው ሕዝብ ያወቃቸው በሴት ሕፃናትና አዋቂ ሴቶች ላይ የደረሱ ጥቃቶችን ጨምሬ በማንሳትም ነው። በሐረር አስገድዶ መድፈርና በአሲድ መቃጠል ደርሶባት ለኹለት ወራት በየካቲት 12 ሆስፒታል ተሰቃይታ የሞተችው የ14 ዓመት ታዳጊ ጫልቱ ጉዳይ ምንም ፍድር አልተሰጠበትም፤ ጭራሽ በዳዩ ከእስር ቤት ውጪ በነፃነት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል እየተባለ ነው። ወደድኩሽ ተብላ በሥራ ባልደረባዋ በጩቤ ሥራ ቦታዋ ላይ ተወግታ ተሰቃይታ የሞተችው መዓዛ ካሳ ገዳይ ከፖሊስ ካመለጠ ቆየ።

ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመምህራን፣ ከሐኪም እስከ ጠበቃና ወጣት የኅብረተሰብ ክፍሎችን በየተራ ችግራችሁን ንገሩኝ እንወያይ ባሉበት (በእነዚህ ስብሰባዎች የሴቶችን ቁጥር መቼም አይታችኋል) ቀጠሮ ያዙልን ብለው ለጠየቋቸው የሴቶችን ጥያቄ እናንሳ ያሉ በራሳቸው የተሰባሰቡ ድርጅቶችና ግለሰቦች በጽሁፍ ላስገቡት ጥያቄ እስከዛሬም መልስ አልሰጡም።

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ሴቶች ፍትሕ የሚሰጡ፣ ችግሮቻቸውን በተዓምር የሚፈቱ አስማተኛ ናቸው ተብሎ ባይታሰብም ከጥቃት ጥበቃ የሚያደርጉና ፍትሕን የሚያረጋግጡ ተቋማትና በአግባቡ ሥራቸውን የሚሠሩ የሴቶች ጉዳይ መዋቅሮች መኖራቸውን ለማረጋገጥ፣ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ግን የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here