በሐዋሳ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

0
604

በደቡብ ኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ ሐዋሳ ጨምሮ በሲዳማ ዞን በተለያዩ ከተሞች ሰሞኑን በደረሰው ደም አፋሳሽ ግጭት የተጠረጠሩ ዘጠኝ ሰዎች ዓርብ፣ ሐምሌ 26 ፍርድ ቤት ቀረቡ። በግጭትና ግድያው ተጠርጥረው ከተያዙና ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጌታሁን ደጉዬ፣ ምክትላቸው ታሪኩ ለማና አንድ የቦርድ አባል ይገኙባቸዋል።

ፖሊስ ሐምሌ 26 ሐዋሳ ላስቻለው የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት እንዳመለከተው ሰዎቹ ባለፈው ሐምሌ 11 እና በተከታታይ በነበሩት ቀናት በተከሰቱ ኹከቶች ለጠፋው ሕይወትና ንብረት ተጠያቂዎች ናቸው ብሎ ይጠረጥራል። በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ለመመስረት መረጃዎችን ለማሰባሰብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠውም ፖሊስ ጠይቋል። ተጠርጣሪዎቹ የፖሊስ ክስና አቤቱታን አልተቀበሉትም። የተያዙበትም ከሕግ ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው፣ ምናልባትም በከፍተኛ ባለሥልጣናት ትዕዛዝ የተፈፀመ ነው ብለው እንዲሚያስቡ ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል። በምርመራው ሒደትም ዛቻን ጨምሮ የተለያዩ በደሎች እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል። ፍርድ ቤቱ የእስረኞቹ ይዞታ እንዲሻሻል አሳስቦ ፖሊስ በዐሥር ቀን ውስጥ ምርመራውን አጠናቅቆ እንዲያቀርብ አዝዞ፣ ለነሐሴ 6/2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የሲዳማ ዞን ፖሊስ እንዳስታወቀው ዞኑ የክልል መስተዳድርነት ሥልጣን ባሰቸኳይ እንዲኖራት የሚይጠይቁ ወጣቶች ባበቀሉት ረብሻ ሰበብ በትንሹ 53 ሰው ተገድሏል፣ ከ50 በላይ ቆስሏል፣ መጠኑ በውል ያልታወቀ ፋብሪካ፣ ሆቴል፣ መደብሮች፣ መኖሪያና መሥሪያ ቤቶች ጋይተዋል፤ ውድመትም ደርሶባቸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here