የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ማባከኑ ታወቀ

0
778
  • ፋብሪካው ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ እዳ አለበት ተብሏል

በአገዳ ግብዓት እጦትና የኀይል እጥረት ሥራ ካቆመ ስድስት ወራት የሆነው በአፋር ክልል የሚገኘው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ2011 የበጀት ዓመት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ማባከኑ ታወቀ። ተቋሙ በየወሩ ለሠራተኛ ደሞዝ 35 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በአጠቃላይ የተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግድብ፣ የቤት ፕሮጀክቶችን እና የእርሻ ልማቱን ጨምሮ እስካሁን ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትና 232 ሚሊዮን ዶላር የውጭ እዳ እንዳለበት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፋብሪካው አንድ የሥራ ኀላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ካለሥራ በየወሩ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ለደመወዝ ክፍያ ወጪ ማውጣቱ አገራዊ ኪሳራ እንደሆነም አስታውቀዋል።

አፋር ክልል አሳይታ ወረዳ የሚገኘው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ2007 ወርሃ ጥቅምት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ተጠናቆ የሙከራ ምርት መጀመሩ ከተነገረለት አራት ዓመታት አስቆጥሯል።በመጀመሪያው ምዕራፍ ፋብሪካው ወደ ሙሉ አቅሙ ሲገባ በየቀኑ 13 ሺሕ ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ያመርታል ቢባልም፣ የሙከራ ምርት ማምረቱ ከተነገረበት ዓመት ጀምሮ በታቀደው መጠን አለማምረቱ ታውቋል። ባለፈው ዓመት 80 ሺሕ ቶን ያመረተው ፋብሪካው፣ በተጠናቀቀው የ2011 በጀት ዓመት 49 ሺሕ ቶን ስኳር ብቻ ማምረቱን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

እንደኀላፊው ገለጻ፣ ለሥራ ማቆሙ ምክንያት ደግሞ የባዮጋዝ ወይም ከስኳር አገዳ ገለባ የሚመነጭ ኀይል እጥረትና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩበትም ለሥራ ማቆሙ ቁልፉ መንስኤ ግን በአግሮኢኮሎጂ፣ በድርቅና የሸንኮራ አገዳ ማሳዎች በእንስሳት መጠቃት ሳቢያ የአገዳ እጥረት መከሰቱ ነው።

ፋብሪካው ወደ ፊትም ወደ ምርት ለመግባት የግድ የአገዳ ግብዓት ማግኘት የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ አገዳ ተክሎ ለምርት ለማድረስ ቢያንስ አንድ ዓመት ይፈጅበታል ተብሏል። በዚህም ቢያንስ ለቀጣይ አንድ ዓመትም ወደ ስኳር ምርት ሊመለስ እንደማይችል ነው ኀላፊው የሚናገሩት።

በአዋሽ ወንዝ ላይ በተሠራው ተንዳሆ ግድብ የሚያለማው የአገዳ ማሳ በተለይም በድርቅ ወራት አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ወደአገዳ ማሳው ስለሚያሰማሩ የሚተከለውን አገዳ ለምርት ማድረስ አለመቻሉን አዲስ ማለዳ ከስኳር ኮርፖሬሽኑ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽንና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ጋሻው አይችሉህም ችግሩ መኖሩን ሳይክዱ “በጉዳዩ ላይ የሚመለከተውን አካል መረጃ እንዲሰጥ አመቻቻለሁ” ቢሉም የተባለውን መረጃ ማግኘት አልተቻለም።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here