በድሬዳዋ በሥነ ምግባር ጉድለት የተቀነሱ ፖሊሶች ወደ ሥራ መመለሳቸው ቅሬታ አስነሳ

0
652

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በአለፉት ዓመታት የሥነ ምግባር ጉድለቶች ታይቶባቸዋል በሚል ከሥራ እና ከኀላፊነት ያገዳቸውን የኮሚሽኑ የፖሊስ አባላትን ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረጉን ተከትሎ ከነዋሪዎች ቅሬታ ቀርቦበታል። ወደ ሥራ የተመለሱት የፖሊስ አባላት፥ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ ከተማ ወንጀሎች እንዲበራከቱ እና በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ በወንጀል ተሳታፊ የነበሩ ናቸው ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

አያይዘውም ከዚህ ቀደም በወንጀል እና በሥነ ምግባር ጉድለት የተሰናበቱ የፖሊስ አባላትን ወደ ሥራ ገበታቸው መመለስ የቀደመውን ወንጀል የተበራከተባቸውን ጊዜያት መመለስ በመሆኑ ለደኅንነታችንም እንሰጋለን ሲሉ አስታውቀዋል። አዲስ ማለዳ በስልክ ያነጋገረቻቸው ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚገልፁት፤ ፖሊሶቹ በስርቆት፣ በቤት ሰብሮ ስርቆት፣ በሴት መድፈር፣ እንዲሁም በሕገ ወጥ የንግድ ዝውውር እንዲሁም በሙስና እና በመሳሰሉት ወንጀሎች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መሳተፋቸው ታምኖበት ከስራ ገበታቸው እንዲነሱ እንደተደረጉ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን ይሔ ሁሉ ጥፋት የተገኘባቸውን ያውም የሕግ አስከባሪ አካላት ወደ ሕግ ማቅረብ እየነበረበት ወደ ሥራ መመለሱ ትልቅ ስህተት ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ እንደሚሉት የፖሊስ አባላቱን መመለስ ኅብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው ያደርጋል ሲሉ ሥጋታቸውን አንጸባርቀዋል።
የተነሳውን ቅሬታ በሚመለከት የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዋና ሳጅን ባንተዓለም ግርማ ለአዲስ ማለዳ ምላሽ ሰጥተዋል።

በእርግጥ በፖሊሶች ላይ የተለያዩ እና ተደጋጋሚ የሥነ ምግባር ጉድለቶች ታይተውባቸው እንደተቀነሱ ይሁንና በኅብረተሰቡ ከፍተኛ ወንጀሎችና ተደራጁ ስርቆቶች ላይ ግን የተገኘ ፖሊስ አባል እንዳልነበር አስታውሰዋል። ለሰባት ቀናት በተከታታይ በሥራ ገበታ ላይ አለመገኘት የፖሊስ አባላቱ ከተሰናበቱበት የሥነ ምግባር ችርግ ውስጥ አንዱ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ባንተዓለም ቀጥለውም መንግሥት በአገር ዐቀፍ ደረጃ የጀመረውን የይቅርታና የመደመር አካሔድ ተከትለው፥ የይቅርታ ደብዳቤ በማስገባታቸው የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመነጋገር ኹለተኛ ዕድል በመስጠት ወደ ሥልጠና ካምፕ እንዲገቡ እንደተደረገ አስታውቀዋል። ተመላሾቹ አባላት መንግሥትንና ሕዝብን ለመካስ ዝግጁ ነን፣ ከጥፋታችንም ታርመናል በሚል የይቅርታ ደብዳቤ ካስገቡ 174 የተቀነሱ የፖሊስ አባላት ውስጥ 114 ለሚሆኑት የአስተዳደሩ ፖሊስ ኪሚሽን ጥያቄያቸውን የተቀበለ ሲሆን ስድሳ የሚሆኑትን ግን ስላላመነባቸው ውድቅ እንዳደረገው ጨምረው ገልፀዋል። ምክንያቱ ደግሞ ይቅርታ የጠየቁ ፖሊሶች መንግሥት በሚገኙበት አካባቢ የፖሊስ ጣቢያዎችን በማነጋገር በእርግጥ ከወንጀል መራቃቸውን በማረጋገጡ እንደሆነ ታውቋል።

የይቅርታ ደብዳቤያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ማሰልጠኛ የገቡት ተመላሽ ፖሊሶች በቀጥታ ወደ ስራ ይመለሳሉ ማለት ሳይሆን ወታደራዊ እና የንድፈ ሃሳብ ሥልጠናዎችን በሚወስዱበት ጊዜ ብቃታቸው እየተመዘነ ሊሰናበቱ የሚችሉበት አጋጣሚ እንደሚኖርም ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here