ባለፉት አራት ወራት 544 ሰዎች ምሕረት አግኝተዋል

0
786

አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ ስለምሕረት አዋጁ አፈፃፀም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልፀዋል

ለስድስት ወራት እንዲቆይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቀው የምሕረት አዋጅ ያለፉት አራት ወራት 544 ግለሰቦች የምሕረቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡ የምህረት አዋጁ የሚመለከታቸው ግለሰቦች በቀሪው ጊዜ ቀርበው ከምህረቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 13/2010 የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት፤ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማሳደግና እየተካሔደ ያለውን ለውጥ ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለመድረግ በሚል፣ በተለይም ተከስቶ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ወቅት የወንጀል ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦችን የወንጀል ተጠያቂነት ለመሰረዝ የምሕረት አዋጅ ቁጥር 1096/2010ን ማፅደቁ ይታወቃል፡፡
የምሕረት አዋጁ ምሕረት ማግኘት ይችላሉ ብሎ በዝርዝር ከገለፃቸው ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የሚፈለጉ፣ ምርመራ ላይ ያሉ፣ ክስ የተመሰረተባቸው እና ውሳኔ ያገኙ ግለሰቦች አዋጁ ከፀደቀበት ጊዜ አንስቶ በስድስት ወራት ውስጥ ቀርበው ሪፖርት ማድረግ እንደሚኖርባቸው፤ ይህ ካልሆነ ግን ከምሕረቱ ተጠቃሚ መሆን እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡ አዋጁ ከፀደቀ አራት ወራት ያለፉት ሲሆን እስከ ሕዳር 6/2011 ድረስ ሪፖርት በማድረግ የምሕረት ሠርተፊኬት የወሰዱት 544 ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
የፌዴራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ በተለይ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት የምሕረቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል 250 የሚሆኑት በወንጀል ተፈርዶባቸው ማረሚያ ቤት የነበሩ ናቸው፡፡
ይህ ቁጥር ከወታደራዊ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ጉዳያቸው የታየላቸውን እንደማይጨምር የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በድረ ገፅ እየተሰጠ ባለው አገልግሎት በተለይም በውጭ አገራት ያሉ ግለሰቦች የምሕረት አዋጁ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስም በድረ ገፅ ያለውን የምህረት አሰጣጥ ሂደት በመጠቀም 31 ሰዎች፤ በአካል በመቅረብ ደግሞ 263 ሰዎች ሪፖርት እንዳደረጉ ተነግሯል፡፡
ምሕረት አሰጣጡ በክልል የፍትህ ቢሮዎች በኩልም በውክልና እየተሰጠ ሲሆን የምሕረት አዋጁ የሚመለከታቸው ግለሰቦች የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወይም የክልል የፍትህ ቢሮዎችና በድረ ገፅ እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት ራሳቸው ወይም በወኪላቸው በኩል ማግኛት ይችላሉ ተብሏል፡፡
አቶ ዝናቡ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በወንጀል ያልተጠረጠሩ እንዲሁም ያልተፈረደባቸው ግለሰቦች ጭምር ከውጭ አገራት የምሕረቱ ተጠቃሚ ለመሆን እያመለከቱ ይገኛሉ፡፡ ግለሰቦቹ በነበረው የፖለቲካ ምሕዳር መጥበብ የተነሳ ከአገር የወጡ መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ እነዚህ ግለሰቦች የወንጀል ምርመራምና ክስ የሌለባቸው በመሆኑ ምንም የምሕረት አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ማለፍ ሳያስፈልጋቸው ወደ አገር ቤት መመለስ እንደሚችሉ አስገነዝበዋል፡፡
ሆኖም አዋጁ የሚመለከታቸው ግለሰቦች የምሕረት አዋጁ ተፈፃሚ የሚሆንበት የጊዜ ገደብ እየተገባደደ በመሆኑ ባለው ቀሪ ጊዜ ቀርበው ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸውና ጊዜው ካለፈ በኋላ አዋጁ ተፈፃሚ መሆን እንደማይችል አውቀው ከመጉላላት እንዲድኑ አቶ ዝናቡ ቱኑ መክረዋል፡፡
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ያነጋገራቸው የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ስለ አዋጁ አፈፃፀም ሁኔታ በተለይም በስድስት ወር ሪፖርት መደረግ ስለሚኖርበት አግባብ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት በተለይም አፋኝ የሆኑት የፀረ ሽብርተኝነት እና መሰል ሕጎች ላይ የሕጋዊነት ጥያቄ አንስተው ለዓመታት ሲታገሉ መቆየታቸውን በመግለፅ፤ በግላቸው ከነዚህ ሕጎች ጋር በተያያዘ የተከፈቱ ክሶች ሕጋዊነት የላቸውም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ እስከ አሁን ድረስ የድርጅቱ አባላትና አመራሮችን በተመለከተ ምን ያህሉ የምህረት ሠርተፊኬት እንደወሰዱ መረጃ እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ስለምሕረት አዋጁ አፈፀፀም ግንዛቤ እንደሌላቸው አሳውቀዋል፡፡
የምሕረት አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካልተራዘመ በስተቀር፤ ከመጋቢት ስምንት በኋላ የወንጀል ምርመራና ክስ እያለባቸው ሪፖርት ያላደረጉ ሰዎች በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ከአዋጁ መረዳት ይቻላል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here