አዲስ አበባ ፊንፊኔ – ሸገር – በረራ

0
1711

የዋና ከተማይቱ የባለቤትነት ውዝግብ

መንደርደሪያ
ሚካኤል መላክ መሐል አዲስ አበባ፣ ፒያሳ ተወልዶ ያደገ፣ በወጣትነትና ጉልምስና ዕድሜ ክልል የሚገኝ በቀላሉ ከሰዎች ጋር መግባባት የሚችል ጨዋታ አዋቂ አዲስ አበቤ ነው። ሚካኤል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አሀዱ ያለው በቀድሞ አጠራሩ በላይ ዘለቀ ጎዳና በሚባለው ከአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሰሜን ማዘጋጃ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው ቤተልሔም ትምህርት ቤት ሲሆን የከፍተኛ ትምህርቱን በስዊዘርላንድ በንግድ አስተዳደር እና በመልክዓ-ምድራዊ ንድፍ ዘርፎች አጠናቋል። ስለ አዲስ አበባ ማውራት የማይጠግበው ሚካኤል “ፒያሳ ተወልደን፣ በዙሪያዋ ኬክ በልተን፣ አትክልት ተራ የምግብ አስቤዛ አድርገን፣ አሮጌ መጽሐፍት ፍለጋ ወደመርካቶ ሔደን፣ ለመዝናናት ድግሞ ቦሌ ሔደን ነው አዲስ አበባ ላይ ያደግነው” ይላል።ሚካኤል እንደው ዝም ብሎ በነቢብ ብቻ አይደለም የአዲስ አባባ ፍቅሩን የሚገልፀው፤ በንግግር ብቻ ስለማይወጣለት በሚሠራበት የሙያ ዘርፍ በከተማይቱ አንዳንድ ቦታዎች የራሱን አሻራዎች እንደሳረፈ ይናገራል። አፍሪካ ጎዳና በሚል ስያሜ የሚታወቀው ከመስቀል አደባባይ ወደ ቦሌ ዓለም-ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስደው የከተማችን ትልቁ ጎዳና አሻራውን ካሳረፈባቸው ቦታዎች አንዱ ሲሆን፥“ዓለም ሲኒማ ጋር ወደ ቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ ያለው የእገረኛ ማቋረጫ በብዙ የከተማይቱ ሰዎች ዘንድ ‹ማይክ ዜብራ› ተብሎ እንደሚጠራ” ሚካኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። ምክንያቱም የራሱ የሥራ ውጤት በመሆኗ ነው። በተጨማሪም የአፍሪካ ጎዳና ጫፍ ላይ የሚገኘው የመንገደኞች መተላለፊያና ውቡ የአትክልት ስፍራ የአዕምሮው ትሩፋት ከሆኑ የከተማዋ መስህቦች ውስጥ ተጠቃሽ እንደሆነ ሚካኤል ይናገራል።
47 አገራትን በሥራ እና ሕይወት አጋጣሚ እንደጎበኘ የሚናገረው ሚካኤል፣ በሔደባቸው አገራት ውስጥ የሚገኙ አያሌ ከተሞችን አይቷል። አዲስ አበባ በንጽጽር ከተቆረቆረች ወዲህ እንዳስቆጠረችው ረጅም ዕድሜ፣ እንዲሁም የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ለምን ሥሟንና ደረጃዋን በሚመጥን ቁመና ላይ አልተገኘችም የሚለው ጉዳይ ሚካኤልን ሁል ጊዜ ያስቆጨዋል፤ ያበሳጨዋል። “ከኢትዮጵያም አልፋ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በማዘጋጃ ቤት አገልግሎቷ ደካማ ነች። የሌሎችን አገራት ዋና ከተማ ትተን ከጎረቤታችን ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ጋር እንኳን መወዳደር አትችልም”ይላል በዘርፈ ብዙ ችግሮች ስለ ተበተበችው አዲስ አበባ ሲናገር። “ምሳሌ መዘርዘሩ ያደክም እንደሆነ እንጂ የሚፈይደው ነገር የለም፤ አንድ በቅርቡ የወጣ የጥናት ውጤት ላይ ‹አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የአደባባይና መንገድ ዳር ከሚገኙት መብራቶች መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት አይሰጡም› በማለት ቁጭቱን በሚየሳብቅበት ድምፀት ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።
የአዲስ አበባ የረዥም ጊዜ ነዋሪው ሚካኤል እና መሰሎቹ ቁጭት ይህ ይሁን እንጂ አዲስ አበባን በአደባባይ የሚያምሳት የፖለቲካ ውዝግብ ከአስተዳደር ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከታሪክ እና የፖለቲካ ትርክት ጋር የተያያዘ ጭምር ነው። ለውዝግቡ መንስዔ የሆነው ምንድን ነው? የከተማይቱ ታሪክ እና የፖለቲካ ትርክት ምን ዓይነት ስንክ ሳሮች አሉት? ለውዝግቦቹ ዘላቂ መፍትሔ እንዴት ማግኘት ይቻላል? የሚሉትን ጥያቄዎች የሐተታ ዘ ማለዳ አትኩሮት ናቸው።
የአዲስ አበባ መቆርቆር እና ዘላቂነት ዕድል
በተለያዩ የታሪክ መዛግበት ላይ ለረጅም ዘመናት ኢትዮጵያን የገዟት ነገሥታት ቋሚ መቀመጫ እንዳልነበራቸው ተጽፎ እናገኛለን፤ በተለያየ ዘመንም የተለያዩ ከተሞች ርዕሰ ከተማ በመሆን አገልግለዋል። ኢትዮጵያ የዛሬ መዲናዋን ያገኘችው በ1879፣ በእቴጌ ጣይቱ ምርጫና በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አፅዳቂነት አዲስ አበባ በዋና ከተማነት በመቆርቆሯ ነበር። ፒትር ጋረስተን የተባለ የታሪክ አጥኚ ለሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ማሟያቸው ‹የአዲስ አበባ ታሪክ ከምሥረታዋ 1879 እስከ 1902› በሚል ርዕስ ያቀረቡት የጥናት ጽሑፍ አዲስ አበባ አገር በቀል (indigenous) ከተማ እንደሆነችና ምኒልክ በወደፊቱ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባሕላዊ እና ወታደራዊ ልማት ዘላቂ ተፅእኖ ፈጣሪ (lasting effect) ከተማ ትሆናለች ብለው እንዳላቀዱ ያትታል። ይሁንና በጥናታዊ ጽሑፉ መደምደሚያ ክፍል አዲስ አበባ እንዴት በጊዜ ሒደት ለንጉሣዊው ግዛት የምጣኔ ሀብት እምብርት እየሆነች እንደመጣች ዘርዝሮ አስቀምጧል።
አዲስ አበባ እንደሌሎቹ ከተሞች ሁሉ ጊዜያዊ የንጉሥ ማረፊያ ሆና እንዳታልፍ ከታደጓት አጋጣሚዎች መካከል የባሕር ዛፍ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ዋነኛው መሆኑ ተነግሯል። ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስ ‹ሚኒልክ እና የአዲስ አበባ መቆርቆር› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1961 በጻፉት ጥናታቸው እንደሚነግሩን፥ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በማገዶ እጥረት የተጠቃችውን አዲስ አበባን በአዲስ ዓለም ሊተኳት አስበው ነበር። አዲስ ዓለም የሚለውን ሥም ለከተማዋ እቴጌ ጣይቱ ያወጡላት ሲሆን፣ የክልሉ መስተዳደር ኢጀሬ በማለት ይጠሯታል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አስፋልት መንገድ የተሠራውም በዚሁ መሥመር ነበር። ሌላው ቀርቶ፣ ዐፄው ቤተ መንግሥታቸውን በአዲስ ዓለም ማሳነፅ ሲጀምሩ፣ የጣሊያን መልዕክተኞች ለጋሲዮናቸውን “አይቀሬ” ወደምትመስለው ዋና ከተማ አዲስ ዓለም ቸኩለው አዛውረው ነበር። የሆነ ሆኖ ለማገዶ ፍጆታ የሚውል ቶሎ፣ ቶሎ የሚበቅል የባሕር ዛፍ ወደኢትዮጵያ በመግባቱ የማገዶ ችግሩ በመቀረፉ እንዲሁም ውኃ ከጉድጓድ ማውጣት እና በቧንቧ ማጓጓዝ በመቻሉ፣ እና ሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች ወደ አገር ውስጥ በፍጥነት በመግባታቸው ከተማይቱ ዘለቄታን አግኝታለች።
አዲስ አበባ እንጦጦን ጨምሮ ከሌሎች ቀደምት ከተሞች የምትለየው፥ በግንባታዋ ወቅት ዳግማዊ ምኒልክ የውጭ ዜጎችን በከፍተኛ ሁኔታ ስላሳተፉ እንደሆነ ፓንክረስት ይገልጻሉ። ዳግማዊ ምኒልክ አዲስ አበባን በቆረቆሩበት ወቅት በአካባቢው የነበሩት አርሶ አደሮች ጥቂት እንደነበሩ ተጠቅሷል። በ1900ዎቹ ገደማ የአዲስ አበባ ሕዝብ 65,000 ገደማ እንደነበር ሪቻርድ ፓንክረስት ዶክተር መረብ ‹ኢምፕሬሽን ደ ኢትዮፒ› በሚል የጻፈውን መጽሐፍ ጠቅሰው ዘግበዋል። በዶክተር መረብ ግምት መሠረት የከተማዋን መቆርቆር ተከትሎ፥ የአዲስ አበባ ነዋሪን ‹ህዝብ ብዛትና ስብጥር› የቀየረው አንደኛ የመሳፍንቱ እና አማካሪዎቻቸው “ከሰሜን-ሸዋ፣ አማራ፣ ጎጃም እና ትግሬ መምጣት”፣ የአገልጋዮች እና የአሽከሮች ከጋምቤላ፣ ቤኒ ሻንጉል፣ ወላይታ እና ጉራጌ… መምጣት፣ እንዲሁም ሦስተኛ የኦሮሞ ገበሬዎች ከአጎራባች ገጠር አካባቢዎች መምጣት ነው።

“የፊንፊኔ ኬኛ” አንብሮ
ታረቀኝ ጪምዲ የተባሉ “በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚደርሱ የመብቶች ጥሰቶችን ለዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ የማሳወቅ ሥራ” የሚሠሩ ሰው፥ በ1992 የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ከተማ መዛወሩን ተቃውመው ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (በሐምሌ ወር 1996) ደብዳቤ ጽፈው ነበር። በደብዳቤያቸው “የአዲስ አበባ ታሪክ የኦሮሞ ታሪክን የጭቆናና የዝርፊያ እንዲሁም ኢሰብዓዊ አያያዝ ታሪክ ያንፀባርቃል። አዲስ አበባ ቅኝ ከመያዟ በፊት – ፊንፊኔ የተባለ ኦሮምኛ ሥም ነበራት። ሥሙ በከተማዋ መሐል በርካታ የፍል ውኃ (በኦሮምኛ “ሆራ” ይባላል) መኖሩን ያመለክታል።… አካባቢው ጉለሌ፣ ኤካ፣ ገላን፣ አቢቹ የተባሉ ጎሳዎች የሚኖሩበት እና 12 አስተዳደራዊ ክፍፍሎች የነበሩት ነው።…” ብለዋል።
እውን አዲስ አበባ ከመቆርቆሯ በፊት ፊንፊኔ የምትባል ከተማ ነበረች? ከነበረችስ ለዛሬዪቱ አዲስ አበባ የሚኖራት አንድምታ ምንድን ነው? ታረቀኝ ጨምዲ የተቃወሙት የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ በ1998 ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ተቃውሞውን ያስታግሰዋል?
በፌዴራል መንግሥቱ አጠራር ‹አዲስ አበባ› (በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኦፊሴላዊ አጠራር ‹ፊንፊኔ›) መልሳ የኦሮሚያ ዋና ከተማ እንድትሆን በ1998 ዳግም ከተወሰነ በኋላም ቢሆን ውዝግቡ አልተቀረፈም። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው የኦሮሞ አምስት ድርጀቶች (ኦነግ፣ ኦፌኮ፣ የተባበሩት ኦነግ፣ የኦሮሚያ ነጻነት አንድነት ግንባር እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር) በጋራ መስከረም 15፣ 2011ባወጡት መግለጫ “ዛሬ አዲስ አበባ የምትገኝበት ሥፍራ የጥንት የኦሮሞ ጎሳዎች የእምነት፣ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማዕከል የነበረ መሆኑ አይካድም […] ጎሳዎቹ መሬታቸውን ተነጥቀው እንዲጠፉ ተደርገዋል” ማለታቸው ይታወሳል። በተጨማሪም፣ “እኛ የኦሮሞ ድርጅቶች አዲስ አበባ ሁሌም የኦሮሞ ሕዝብ ናት፤ ይህ ማለት ግን ከኦሮሞ ውጭ መኖር አይችልም ማለት አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል። ይህም በመግቢያችን ታሪኩን ያስነበብናችሁ ሚካኤል መላክን ጨምሮ በብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤን እና ግራ መጋባትን ፈጥሯል። ይሁን እንጂ ይህ ድምዳሜ ቀደም ሲል ታረቀኝ ጪምዲ ከጠቀሱት “ታሪካዊ ብሶት” የተነሳ የተደረሰበት መሆኑ ይታወቃል። እነዚህ ሁሉ የፖለቲካ ድርጅቶች “ፊንፊኔ የኦሮሞ ነች” ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ድርጅቶቹ የመንግሥት ሥልጣን ተቆጣጥረው ፕሮግራማቸውን ማስፈፀም ቢጀምሩ፥ ከዚህ ረገድ ምን ዓይነት አስተዳደራዊ ተፅዕኖስ ይፈጥራሉ?
በተጨማሪም በኒው ዮርክ ከተማ የስቶኒ ብሩክ ዩንቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ሽመልስ ቦንሳ (ዶ/ር) “የአዲስ አበባ ምሥረታና ዕድገት ታሪክ ባንድ በኩል የማግለልና የማፈናቀል ታሪክ እንደሆነ የሚካድ አይደለም” ይላሉ። “አሁንም ድረስ በዋነኝነት መደባዊ የሆነ ማንነትንም በተወሰነ መልኩ ይዞ የቀጠለ የፍንገላና የማግለል ታሪክ ከአዲስ አበባ እንዲሁም ከሌሎቹ የአገራችን ከተሞች ጋር ተጣብቶ ያለ እውነታ ነው። ስለዚህ ጥያቄው አለ፤ ጥያቄውም ከከተማው የፍጥረትና ዕድገት ታሪክ ጋር የተቆራኘ ነው። ነገር ግን ጥያቄው የፖለቲካ ጡዘት ሰለባ መሆኑ፣ በማንነት መነፅር ብቻ መታየቱ፣ የከተማውን በስፋትም የአገሪቱን ንብርብርና ውስብስብ ታሪክ ያላየ ወይንም ያገለለ መሆኑ እንዴት ይፈታ፣ የተሻለ አማራጭ የቱ ነው የሚሉትን ጥያቄዎች አንዳንጠይቅ እንቅፋት ሆኗል።” ይላሉ፡፡
“የበረራ የኛ” ተፃርሮ
“ፊንፊኔ ኬኛ” የሚለው ትርክት ጮሆ በሚሰማበት ወቅት በአንፃሩ “ታላቁ” የኦሮሞ ፍልሰት በ16ኛው ክፍለ-ዘመን ከመከሰቱ በፊት ‹አዲስ አበባ› በረራ የምትባል ከተማ ነበረች የሚል ትርክት ለዚህ አንብሮ (‹ቴሲስ›)፣ ተፃርሮ (‹አንታይ-ቴሲስ›) ሆኖ ቀርቧል። ለመሆኑ በረራ የምትባለዋ ከተማ የት እና “የእነማን” ነበረች?
ኢጣሊያዊው ካርቶግራፈር ፍራ ማውሮ በ15ኛው ክፍለ ዘመን እስከዛሬም ድረስ በዚያን ወቅት ከተሠሩ የተሻለ እና የጊዜውን እውነታ ደኅና አድርጎ እንደሚያሳይ የተመሠከረለትን የዓለም (የአፍሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ) ካርታን ሠርቶ ያለፈ ሰው ነው። ፍራ ማውሮ የዓለምን ካርታ አሁን ከሚሳልበት ከሰሜን ወደ ደቡብ (ወደታች) በተቃራኒ ወደላይ በመገልበጥ አፍሪካን ከላይ አድርጎ ነበር የሳለው። የፍራ ማውሮ ካርታ ላይ ታዲያ የኢትዮጵያዋ በረራ መናገሻ ከተማ ስፍራ ትገኛለች። ሪቻርድ ፓንክረስት እንደሚነግሩን ዳግማዊ ምኒልክ አዲስ አበባን ሲቆረቁሩ አያታቸው ሳሕለ-ሥላሴ ከትመውባት የነበረች በመሆኗም፣ የጠፋች ጥንታዊ ከተማ ነች የሚባለውም ስለነበር “አንቺ መሬት ሆይ፣ ዛሬ በኦሮሞዎች ተሞልተሻል፤ ነገር ግን የልጅ ልጆቼ ቤት ሠርተውብሽ ከተማ የሚያደርጉሽ ቀን ይመጣል” ብለው ነበር። ይህንን ንግግራቸውን በመጥቀስ አንዳንድ የአማራ ብሔርተኞች ይህች ከተማ የተቆረቆረችው በ16ኛው ክፍለ-ዘመን የጠፋችውን በረራ ከተማ መልሶ ለማቋቋም ነው የሚል መከራከሪያ መጥቷል።
ፊሊፕስ ብሪግስ የተባለ ጸሐፊ “ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ የጻፈው መጽሐፉ ገጽ 49 እና 50 ላይ “በ15ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ከዛሬዋ አዲስ አበባ ብዙም ሳትርቅ ሸዋ ውስጥ በረራ የምትባል ቋሚ ከተማ ነበረች” ሲል ጽፏል። ይህም በፍራ ማውሮ ካርታ ከመመልከቱም በተጨማሪ አካባቢውን እ.ኤ.አ. በ1531 የጎበኘው የመናዊ አራብ-ፋቂህ ማስታወሻ መገለጹን ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ ይህች ከተማ በሙስሊሙ ጦረኛ አሚር አሕመድ ኢብን ኢብራሒም (“ግራኝ አሕመድ”) እንደተደመሰሰች የተለያዩ መዛግብት ይጠቅሳሉ።
ሽመልስ ቦንሳ (ዶ/ር) በረራ የአሁኗ አዲስ አበባ ላይ የነበረች ከተማ መሆኗን ለመጥቀስ ምርምር እንደሚጠይቅ ተናግረው፥ ነገር ግን የዛሬዋ አዲስ አበባ ላይ ጥንታዊ ከተማ መኖሩን የሚያመላክቱ ቅርሶች መኖራቸውን ማስረጃ ጠቅሰው ይናገራሉ። “የአሁኑ እንጦጦ ያለበት ቦታ፣ የወጨጫና ፉሪ ኮረብታዎች የሚገኙበት አካባቢ በመካከለኛው ዘመን የመንግሥቱ መቀመጫ የነበረ ከተማ ወይንም የነበሩ ከተሞች አንዳንድ ፍርስራሾች በቁፋሮ መገኘታቸው ይታወቃል። ቢርብርሳ ይባል የነበረው ወይንም አሁን አራዳ ጊዮርጊስ ያለበት አካባቢ በመካከለኛው ዘመን የተመሠረተ ቤተክርስቲያን እንደነበረበት በኋላም በ16ኛው ክፍለዘመን በነበረው ጦርነት እንደፈረሰ እ.ኤ.አ. በ1870 የተጻፈ ደብዳቤን ጠቅሶ አባ ኤሚል ፉሸር የተባለ ጸሐፊ እ.አ.አ.1985 በታተመ የአዲስ አበባ ከተማ መቶኛ ዓመት ታሪክ ሥራ ላይ ጽፏል።” በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን እና በርካታ መቶ ዓመታት ያስቆጠረውን “ዋሻ ሚካኤልን” ጠቅሰው የአዲስ አበባን ጥንታዊነት የሚከራከሩ የታሪክ ተመራማሪዎች በርካቶች ናቸው።
የበረራ እና አዲስ አበባ ዝምድና
በአዲስ አባበ ዩኒቭርሲቲ በአለ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህሩ አበባው አያሌው፣ “በመሠረቱ በረራ የሚባለው በትክክል አዲስ አባባ ማለት አይደለም፤ ከአዲስ አበባ ወረድ ብሎ ዱከምና የረር አካባቢ የነበረች ከተማ ነች” ይላሉ። ሪቻርድ ፓንክረስትና ሀርትዊግ ብሬተርኒዝ እ.ኤ.አ. በ2009 በሠሩት አንድ ጥናታቸው በረራ የተባለችው ከተማ ሰፍራበት የነበረውን አካባቢ ጠቁመዋል። እነርሱ እንደሚሉት በረራ ከተማን በሚከተለው አካባቢ ውስጥ ነበረች ለማለት የሚያስችል በቂ መረጃ አለ፡- “ከወጨጫ እስከ አቃቂ ወንዝ በስተምዕራብ፣ በስተሰሜን ኤረር ተራራ፣ ዝቋላ ተራራ እና አዋሽ ወንዝ በስተደቡብ እንዲሁም ሞጆ ወንዝ እና ቢሾፍቱ በስተምዕራብ የሚያዋስኗት በ50 ኪሜ ስኩዌር ውስጥ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ-ምሥራቅ መሐል ለመሐል የዱከም ወንዝ የሚያቋርጣት ከተማ ነበረች” – በረራ።
የውዝግቡ እውነተኛ መንስዔዎች
የ17 ዓመታቱ የርስ በርስ ጦርነት ከተጠናቀቀና በ1983 ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ እና በ1987 ኢትዮጵያ በይፋ የፌደራል ስርዓትን በሕገ መንግሥት ደረጃ ከተቀበለች ሁለት ተኩል ዐሥርታትን አስቆጥራለች። በሕገ መንግሥት ደረጃ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ክልሎችን እንዲሁም አዲስ አበባን እና ድሬዳዋን የፌደራል ከተማ አስተዳድር በማድረግ እንደገና ተዋቅራለች። አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ከዋና ከተማነት ባለፈ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በኋላም ከተማዋን በሕግ ለማቋቋመ በወጡ ቻርተሮች የከተማዋ ሕጋዊ ሁኔታ (legal status) በግልጽ ባለመቀመጡ የከተማዋ ዕጣ ፈንታ ላይ ለውዝግብ የሚዳርጉ ክፍተቶች ተፈጥረዋል።
የሕግ ክፍተቶች
ዘላለም ክብረት የተባሉ የሕግ መምህር እና ዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቀውየጦማሪዎች እና የመብት ተሟጋቾች ስብስብ ውስጥ አባል የሆኑት ምሁር ‹አዲስ አበባ ስለምን ታወዛግባለች?› በሚል ርዕስ ታኅሣሥ ወር 2008 ጽፈው ባሰራጩት ረዘም ያለ ጥናታዊ መጣጥፍ የአዲስ አበባን ሕጋዊ ሁኔታ በተመለከተ ለውዝግብ የዳረጉ የሕግ ክፍተቶችን አመላክተዋል።
አቶ ዘላለም እንደጠቀሱት አዲስ አበባ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 49 መሠረት ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብት ስለተሰጣት ‹ራሷን የቻለች ክልል› ትመስላለች። በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አናቅፅት 3 እና 4 ደግሞ ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግሥቱ በመሆኑ ‹የፌዴራል ቀጠና› ትመስላለች። በንዑስ አንቀፅ 5 መሠረት ደግሞ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በማለት ‹በአንድ ክልል ውስጥ ያለች አንድ ከተማ› ያስመስላታል። በ1989 ታውጆ በ1995 እና በ1996 በተሻሻለው የአዲስ አበባ ቻርተር ማቋቋሚያ አዋጅ ደግሞ ከተማዋን ‹ቻርተርድ (የኮንትራት) ከተማ› ያስመስላታል። ይህ የሕግ ክፍተት አዲስ አበባን ለውዝግብ እንደዳረጋት የጠቆሙት አቶ ዘላለም፣ ምናልባትም አዲስ አበባ በኢኮኖሚያዊ አቅምም ይሁን በሕዝብ ብዛት የሚቀናቀናት የሌለ አውራ ከተማ መሆኗ ችግሩን እንዳባባሰው ያወሱና እንደመፍትሔም ሁለተኛ ከተማ መመሥረትን ይጠቁማሉ።
ጥርስ አልባው ምክር ቤት
በአሁኑ ሰዓት የኢሳት ቴሌቪዥን የፖለቲካ ተንታንኛ የቀድሞው የኮሙንኬሽን ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ‹የመለስ “ትሩፋቶች”፡ ባለቤት አልባ ከተማ› በተሰኘውና በ2006 ለአንባቢያን በቀረበው መጽሐፋቸው ስለአዲስ አበባ ቻርተር መዘጋት ያስፈለገበትን ዐብይ ምክያቶች ሲዘረዝሩ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ፣ የአዲስ አበባ ኗሪ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳር ሙሉ በሙሉ እዲጠቀም ለማስቻል እንደሆነ አብራረርተዋል፣ ይሁንና ቻርተሩ በተቃርኖ መሞላቱን ያትታሉ። የከተማዋን ነዋሪዎች መብቶች በመንጠቅ የአዲስ አበባ ምክር ቤት በፓርላማ ሊበተን እንደሚችል ይገልጻል። ምክር ቤቱ የሚፈርስበት ምክንያት ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ላይ አደጋ የሚጥል ተግባር በከተማው ምክር ቤት ሲፈፅም ወይም የከተማውን አስተዳደር ፀጥታና ድንገተኛ ሁኔታን መቆጣጠር ሲያቅተው እንደሆነ ያትታል። በቅርቡ የሥራ ዘመኑን ጨርሶ የአዲስ ምክር ቤት እስከ ሚቀጥለው አገራዊ ምርጫ ድረስ እንዲቆይ ጠቅላይ ሚስተር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡተ ጥያቄ መሠረት የተፈፀመ ሲሆን ከከተማው ምክር ቤት አባል ውጪ አዲስ ከንቲባ ሆነው ነገር ግን በምክትል ከንቲባነት ማዕረግ ታከለ ኡማ ተሾመዋል። ይሁንና ሹመቱ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
የማንነት ፖለቲካ
ሽመልስ ቦንሳ (ዶ/ር) እንደሚሉት አዲስ አበባ አገራዊም ይሁኑ ክልላዊ ትግሎች የሚካሔዱባት ዋነኛ መድረክ ናት። በመሆኑም አሁን “በማንነት የተቃኘው ፖለቲካ አገሪቷን፣ ክልሎቿንና ከተሞቿን በማንነት መነጽር ብቻ እንድናይ በማስገደድ የባለቤትነትን፣ የመጤና የነባርነት ጥያቄዎችን ወደ አደባባይ አምጥቷቸዋል።” በመቀጠልም፣ “በብሔር የተቃኘው ሕገ መንግሥት ውስብስብ የሆነውን የማንነትና የባለቤትነት ጥያቄ ሲያድበሰብስ እየመረጠ የሚረሳውና የሚያስታውሰው ትርክት ደግሞ ጉዳዩን አወሳስቦታል። ከተማውንና የከተማውን ታሪክ ካንድ ማኅበረሰብ ወይንም ስርዓት ጋር አቆራኝቶ ሌላውን ያገልላል። አንዱ የቅርቡን ወይንም ግማሽ ታሪከ እየጠቀሰ የኦሮሞ ሲያደርግ ሌላው ደግሞ የሩቁን ወይንም ሌላውን ግማሽ እያነሳ የአማራ ነው ይላል። የኅብረ-ብሔራዊነት ትርክት አራማጁ ደግሞ የከተማውን ኅብረ-ብሔራዊ ዕድገትና ብዝኃነት ተመልክቶ ከተማውን ከብሔር ባለቤትነት አላቆ የሁሉም ናት ይላል። ሁሉም ግን የጠቅላይነት ዕይታዎች ናቸውና በራሳቸው መንገድ ሌሎች ዕይታዎችን እና ተከታዮቻቸውን ያገልላሉ” ይላሉ።
መፍትሔው ምንድር ነው?
የአዲስ አበባን ነዋሪ ጥያቄ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ የሸፈነው ይመስላል። በመሆኑም የመፍትሔ ሐሳቦች እየተባሉ የሚጠቆሙት እንደጥያቄው ግራ የሚያጋቡ ሊሆኑ ይችላሉ። ከመፍትሔ ሐሳቦቹ መካከል “አዲስ አበባን ለአዲስ አበቤ” የሚለው ይገኝበታል።
“አዲስ አበባን ለአዲስ አበቤ”?
አዲስ አበባ የእከሌ ነች፣ የእነከሌ ነች የሚለው ሽሚያ ያስደነገጣቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች ‹አዲስ አበባ የአዲስ አበቤ ነች› የሚል ድምፅ እያሰሙ ነው። ይሁን እንጂ ይህም ንቅናቄ በአቀራረቡ ዘውጌ ነው እየተባለ እየተተቸ ነው። ‹አዲስ አበቤ ማነው?› ከሚለው ጥያቄ አንስቶ በሁሉም ኅብረተሰብ ሀብት የተገነባች ከተማ እንዴት በአጋጣሚ ለተወለደባት፣ ወይም ነዋሪ ለሆነባት ብቻ የግል ንብረት ትሆናለች የሚል ትችት ይሰነዘራል።
የታሪክ ተመራማሪው አበባው አያሌው ግን በዚህ አይስማሙም፤ አዲስ አበባ ለአዲስ አበቤዎች የሚለው ጥያቄ “ፖለቲካዊ ትክክል የሆነ ጥያቄ ነው” ባይ ናቸው። “ሁሉም በየብሔሩ በተደራጀበት የአዲስ አበባን ኗሪ ‹በኗሪነቱ› መደራጀት መከልከል ያስቸግራል። ሁለት ነገር በመታዘብ ያስፈልጋል፤ አንደኛ፣ ማንም መጥቶ የሚስተናገድበትና የምጣኔ ሀብት ዕድል የሚያገኝበት ከተማ ነው። አንተ ጋሞ ነህ፣ አንተ ትግሬ ነህ፣ አንተ አማራ ነህ የሚባልበት አይደለም፤ ምክንያቱም የሜትሮፖሊታን ባሕል ስላለ። ስለዚህ መሠረታዊ ጥያቄ የሚሆነው የአዲስ አበባ ጉዳይ የፖለቲካ ውክልና ያስፈልገዋል የሚለው ነው። ሁለተኛ፣ ያሉት የአስተዳደር ሥልጣኖች በመስተዳድር ደረጃ፣ በክፍለ ከተማ ደረጃ ይህንን ሥልጣን ለዚህኛው፣ ያንን ደግሞ ለዛኘው ብሔር ይሰጠው የሚባለው፣ በአራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የሚወሰነው የሕዝብ ውክልናን ፈፅሞ አያክልም” ይላሉ።
ሚካኤል መላክና ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ በተሠማሩበት የሙያ ዘርፍ ቢለያዩም የአዲስ አበባ ጉዳይ ግን አገናኝቷቸዋል። ሔኖክ የሕግ ባለሙያ ሲሆን በተለይ በፖለቲካ ሰበብ ለሚታሰሩ ታዋቂ ሰዎች በነፃ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ይታወቃል። ሁለቱ አዲስ አበቤዎች ከተማዋ ችግሮቿን ለይታ መፍትሔ የምታፈላልግበትን ዘዴ የሚቀይስ ማኅበር ለመመሥረት ቅድመ ውይይት ማድረግ ጀመሩ። ይሁን እንጂ በድንገት አዲስ አበባን ያነጋገረ እና በአገሪቷ ውስጥ እየታየ ያለውን የውጥ መንፈስ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ክስተት ተፈጠረ። ማክሰኞ ቀን ጥቅምት 7፣ 2011 ሔኖክና ሚካኤል በቁጥጥር ሥር ዋሉ። የእስራቸው ሰበብ የነበረው ይኸው እንደአዲስ አበቤ ለመደራጀት የማሰባቸው ጉዳይ ነበር። ሔኖክ እና ሚካኤል ከጥቂት ቀናት በኋላ ከእስር ቢፈቱም፣ መንግሥት ግን የአዲስ አበቤዎችን መደራጀት የሚመለከትበትን ዓይን አጠራጣሪ አድርጎታል። “የአዲስ አበባ ጉዳይ ምንም አያሻማም”
የአዲስ አበባ ጉዳይ ምንም አጨቃጫቂ እንዳልሆነ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር መረራ ጉዲና (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አገር-ዐቀፍ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ይልቃል ጌትነት ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ቃል በአንድ አፍ ይናገራሉ።
አቶ ይልቃል “ምንም በማያጣለው ነው የምንጣላው፤ በማያነጋግረው ነገር ነው እየተነጋገርን ያለነው። አዲስ አባባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነች። ምንም አጨቃጫቂ ነገር የለውም፤ ሕገ መንግሥቱ ላይም ግልጽ ነው” ብለው ውዝግቡን የአክራሪ ብሔርተኞች ለመደራደሪያ ሰማይ የሰቀሉት ነገር እንደሆነ በመግለጽ ያጣጥሉታል። መረራ ጉዲናም (ዶ/ር) ከዚህ ያልራቀ አስተያየት ነው ያላቸው። በአዲስ አበባ ጉዳይ “የሚፋጁበት ምንም ነገር የለም” ይላሉ። አዲስ አባባ በታሪክ አጋጣሚ ለቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ይሁን ለኦሮሞ ሕዝቦች መኖሪያ ሆኗል። ስለዚህ ሁለቱም ሕዝቦች አብረው ሲኖሩ ነበር፤ አሁንም አብረው እየኖሩ ነው” ብለዋል። እንደ መረራ ጉዲና “ዞሮ ዞሮ ዋናው ጉዳይ የሚፋጁበት ወይም የሚጣሉበት ምንም ነገር የለም፤ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተና ለወደፊትም ሊኖር ከሚችለው አብሮ መኖርም ሆነ የተፈጥሮና ሌሎች ሀብቶችን እየተካፈሉ የመኖርም ነገሮችን አንስቶ መደራደርና መነጋጋር ይቻላል፤ ይገባል” በማለት በፖለቲከኞች ውዝግቡ ከሚገባው በላይ መለጠጡን እንደታዘቡ ይናገራሉ።
“መሬቱን ጠፍጥፎ የሠራ የለም”
አዲስ አበባ ስትቆረቆር የኦሮሞ ገበሬዎች እንደነበሩባት ለሚቀርበው ትርክት፣ ከዚያ ጥቂት መቶ ዓመታት በፊት ደግሞ የእነዐፄ ዳዊት መቀመጫ ነበረች የሚል መከራከሪያ ይቀርባል። በዚህ ዓይነት የዘመን ገጾች ከተገለጹ በ11ኛው ክፍለ ዘመን ሸዋን ይገዙ የነበሩት የኢፋት ሡልጣኔቶችን እና ከዚያ በፊት የነበሩትንም መጥቀስ ሊያስፈልግ ነው።
“አገር ስትመሰርት መዲና ይኖርሃል። ከታሪክ አኳያ ይህንን መሬት ይኼንኛው ሕዝብ ረግጦታልና የዚህ ነው፣ የዛኛው ነው ማለት አይቻልም” ይላሉ የታሪክ ምሁሩ አበባው አያሌው። “አንደኛ፣ ከታሪክ አንፃር እዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት እነማን ናቸው ከተባለ ወደ ሌላ አጨቃጫቂ ጉዳይ እንገባለለን፤ በ14ኛው እና 15ኛው ክፍለ ዘመን ወርጂዎች ናቸው እዚህ አካባቢ የሚኖሩት።… ሁለተኛ፣ አዲስ አበባን የሚያክል ከተማ የተገነባው እያንዳንዱ ሰው ግብር በሚገብረው እንጂ አንድ ዘውግ ተነስቶ እኔ ነኝ ያለማሁት፣እኔነኝ የተለየ ጥቅም የሚባለው ሁሉ የተሳሳተ ነው፤ አይሠራም። ነጋዴውም፣ አስተማሪውም፣ ለማኙም፣ ሹፌሩም እየመጣ አስተዋጽዖ አድርጓል።”
አቶ አበባው በመቀጠልም “አዲስ አባበ ላይ የተለየ መብት የሚባል ነገር የለም” ይላሉ። ይህንን ድምዳሜያቸውን የሚያጠናክሩት “ማነው ራሱ የሚኖርበትን መሬት ጠፍጥፎ የሠራ ብሔር?” በሚል ጥያቄ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here