የመአዛ አሸናፊ አነጋጋሪ መሆን

0
350

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ከፍትሕ ማሻሻያዎች እና ችግሮች ዙሪያ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ለተነሳ ጥያቄ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት መአዛ አሸናፊ ሰጡ የተባለው ምላሽ ሰሞኑን በሰፊው የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን አጨናንቆ ከርሟል፤ በአንዳንድ መደበኛ መገናኛ ብዙኀንም ላይ የውይይት ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል።

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ተሳታፊ፤ በኋላ ላይ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ምክትል ሊቀ መንበር ግደይ ዘርዓፂዎን መሆናቸው ታውቋል፣ ላነሱት አስተያየት አዘል ጥያቄ ፕሬዘዳንቷ ሰጡት የተባለው ምላሽ ነው የንትርኩ መንስዔ።

ግደይ በትግራይ ክልል የፖለቲካ ምኅዳሩ የጠብብ መሆኑን፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳልቻሉና ደጋፊዎቻቸው ወከባና እንግልት እንደሚደርሳቸው አንስተው፣ በዚህ ረገድ የፍትሕ አካላት በምን መልኩ ሊረዷቸው እንደሚችሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

ፕሬዘዳንቷም በውይይቱ መዝጊያ ንግግራቸው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ስለትግራይ ክልል የተጠየቀውን በማስመልከት የአሜሪካንን ተመክሮ በምላሻቸው ጠቅሰዋል። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ አሜሪካ ውስጥ ጥቁርና ነጭ ተማሪዎች በአንድ ላይ እንዲማሩ ፍርድ ቤት እንደወሰነ፤ ይሁንና አንደኛው ግዛት ሕጉን ተግባራዊ ባለማድረጉ የወቅቱ ፕሬዘዳንት የነበሩት ዲ ዋይት አይዘን አወር ወደ እምቢተኛው ግዛት ጦር ሠራዊት በማዝመት ተማሪዎቹ ተቀላቅለው እንዲማሩ አስገድደዋቸዋል። በተመሳሳይ በኢትዮጵያም በአገር ግንባታ ወቅት መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ሲሉ አክለዋል። ይህም የብዙዎች ትኩረት ስቧል፤ አነጋግሯል፤ አነታርኳልም።

የትግራይ ክልል ቢሮ ኀላፊ አማኑኤል አሰፋ የፕሬዘዳንቷን ንግግር ተገቢ አለመሆን አስምረው በአንድ መገናኛ ብዙኀን ላይ ገልጸዋል። የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባልና ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳም እንዲሁ በሌላ መገናኛ ብዙኀን ፕሬዘዳንቷ የትግራይ ክልል ማለት ስላለማለታቸው እርግጠኛ እንዳልሆኑ ጠቅሰው፤ ይሁንና ያንን የማለት መብት የላቸውም ሲሉ ተችተዋል። ጌታቸው “እኛ [ሥራ አስፈፃሚ] በፍርድ ቤት ጣልቃ እንደማንገባ ሁሉ፤ እሳቸውም በእኛ ጉዳይ ጣልቃ ባይገቡ ይመረጣል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል አንዳንዶች ፍርድ ቤት የወሰነውን አልፈጽምም ያለን አካል በኀይል እንዲፈጽም ማስገደድ ምኑ ላይ ነው ችግሩ ሲሉ የፕሬዘዳንቷን ተቺዎች መከራከሪያ ነጥብ ‘ውሃ የማያነሳ’ ነው በማለት አጣጥለውታል። እንዲያውም አገራት የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ለማስከበር አገራት እስከምን ድረስ እንደሚሔዱ ያሳያል በማለት ፕሬዘዳንቷን ምላሽ ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

ይሁንና አንዳንድ የትግራይ ‘አክቲቪስቶች’ መአዛ አሉ ከተባለበት ርዕሰ ጉዳይ ውጪ የፕሬዘዳንቷን ስብዕና በከፍተኛ ደረጃ አብጠልጥለዋል፤ ክብረ ነክ ስድብ በመጠቀም ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። ይሁንና በፕሬዘዳንት መአዛ በኩል እስካሁን ለማስተባበል፣ ለማረም ወይም ለማብራራት በሚል የተሰጠ መግለጫ የለም።
የውይይት መድረክ ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ጨምሮ ሌሎች የፍትሕ አባላት፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤት እንዲሁም የእርቀ ሰላም አባላትና የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ተሳታፊዎች መሆናቸው ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here