የኦሮሞ ባሕል ማዕከልን በጨረፍታ

0
498

ክዋኔ ጠብቆ የሚከፈትን የደረጃ ፏፏቴ ከመካከል አድርጎ በኹለት ረድፍ የሚገኘው ወደ ማዕከሉ ቅጥር ገቢ የሚያስገባው ደረጃ ያለስስት የተሠራ መሆኑ ያስታውቃል። ደረጃውን ጨርሶ ገቢ ወጪውን በትኩረት ከሚያዩት ፈታሾችና ጥበቃዎች አልፎ ወደ ውስጥ ለዘለቀ፤ የማዕከሉን ሕንጻ የሙጥኝ ብለው የሚገኙ፤ በጎበዝ ቀራጺ የተሠሩ ሃውልቶች ወደ ውስጥ መዝለቅ የላቀ ጥበብ የሚገኝበት እንደሆነ ሹክ ይሉታል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ሥማቸው በስፋት ከሚታወቁ የባሕል ማዕከላት መካከል አንዱ ነው፤ የኦሮሞ ባሕል ማዕከል። መስቀል አደባባይን ተታኮ ከአዲስ አበባ ስታድየም ፊት ለፊት የሚገኘውና በ2007 የሕንጻ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ የገባው ባሕል ማዕከሉ፤ በባሕል ዕድገትና አገልግሎት ላይ የባሕል ማዕከላት ሚና ምን ሊሆን ይገባል ለሚለው ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው።

በኦሮሞ ባሕል ማዕከል የታሪክ ጥናት ቡድን መሪ የሆኑት ዓለማየሁ ኃይሌ፤ የኦሮሞ ባሕል ማዕከል መኖሩ የባሕል ዘርፉን በጥናት ለመደገፍ ከፍ ያለ አስተዋጽዖ እንዳደረገ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል። ማዕከሉ የሕዝቡን በተለይም በኦሮሚያ ያለውን ማኅበረሰብ ሕይወትና ባሕል አጥንቶ፤ ለማወቅና ለማስተዋወቅ አልፎም አጠናክሮ ማስቀጠልን ታሳቢ በማድረግ የሚንቀሳቀስ ነው።

በባሕል ማዕከሉ አራት ዋና ክፍሎች ተከፋፍለው ሥራዎችን ይሠራሉ። ከክፍሎቹ መካከል የኦሮሞ ባሕል ጥናት አካዳሚ አንዱ ሲሆን የኦሮሞ ማኅበረሰብ ቋንቋ፣ ታሪክና ሥነ ሰብዕ (anthropology) ይጠናል። ቀሪዎቹ ሦስት ክፍሎች ደግሞ መዘክሩ (‘ሙዝየም’)፣ ቤተ መጻሕፍቱ እና የቴአትር ጥበብ ዘርፉ እያንዳንዳቸው ዘርፍ ሆነው በትኩረት የሚሠራባቸው ናቸው።

የአንድ አገር ባሕል ማዕከል ውስጥ መግባት፤ አገሩን የማየት ያህል እንደሚቆጠር ሁሉ፤ የኦሮሞ ባሕል ማዕከል ውስጥ የሚዘልቅ ተመልካች ከሞላ ጎደል ስለ ኦሮሞ ሕዝብ አውቆ እንዲወጣ ይጠበቃል። ዓለማየሁ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ሀብቶች በተለይም ተንቀሳቃሽ ቅርሶች በማዕከሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። እነዚህም ከኦሮሚያ የተለያዩ ስፍራዎችና ሕዝቦች በጥናትና ዳሰሳ የተሰበሰቡ ናቸው። ያም ሆኖ በማዕከሉ ሁሉንም የሚወክል ሀብት ይገኛል ማለት አይደለም፤ በሒደት ወደተፈለገው ደረጃ ለመድረስ እየተሠራ እንደሆነ ግን ዓለማየሁ ተናግረዋል።

“የኦሮሞ ታሪክ በተለያየ ምክንያትና አጋጣሚ ለረጅም ዘመን ታፍኖ የቆየ በመሆኑ አዲስ ነው ማለት ይቻላል” ያሉት ዓለማየሁ፤ ቋንቋውም ለሥነ ጽሑፍ ብዙ አለመዋሉ፤ በፍልስፍናው ላይ ጥናቶች አለመደረጋቸው ጋር ተያይዞ ከቋንቋው ጋር ከፍ ያለ ዝምድና ያለው ባሕልም ታፍኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል። ይህ ሁሉ መሆኑ ታድያ ለኦሮሞ ባሕል ማዕከል በተለይም ጥናትና ምርምር ላይ ያለውን የቤት ሥራ እጥፍ ድርብ ያደርገዋል።

የኦሮሞ ባሕል ማዕከል በዚህ ረገድ በርካታ ጥናቶችን በማድረግ ሚናውን እየተወጣ ያለ ማዕከል ነው። በአረዓያነት የሚከተለው ማዕከል ሳይኖር፤ የልምድ ልውውጥና መማማሪያ መድረክ ባልተፈጠረበት ሁኔታ፤ ጉዞን ሳያቋርጡ መሔድ ብርታትን የሚጠይቅ ነው። በዚህም ላይ በማዕከሉ ያሉ ባለሙያዎች እውቀታቸውን እንዲያሰፉ በማድረግ በኩል ቸል አላልም። ለጀማሪ ባለሙያዎችና ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ የትምህርት ዕድልን እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ መስጠቱ እዚህ ላይ ይጠቀሳል።

ምንም እንኳ እንደተባለው ባሕል ማዕከሉ በዕድሜ ገና ለጋ የሚባል ቢሆንም፤ በመጣበት ርቀት ሲታይ በታሪክና ባሕል ጥናት የሚፈለገውን ያህል መሔድ አልቻለም። ለዚህ ደግሞ ከዓመት በፊት ተጠቅሶ የነበረው የሰው ኀይል ችግር እና ሌሎችም ምክንያቶች ተጠያቂ ናቸው። ዓለማየሁ እንዳሉት ደግሞ በተለይ የሰው ኀይል እጥረት ሲባል በጥቅሉ ሳይሆን የምኁራንና የባለሙያዎችን እጥረት ለይቶ የሚያመላክት ነው።

ማዕከሉን ከመሠረቱ ወደ እውቀት መናኻሪያነት (Center of Excellence) ለማሳደግ ወይም የጥናት ዘርፉ ላይ አተኩሮ ወደ አካዳሚነት ለመቀየር የሚደረገውን ጥረትም ይህ የባለሙያ እጥረት ሊያደናቅፈው የሚችል መሆኑ ግልጽ ነው። በጥናት ዘርፍ ላይ የእውቀት ሰዎች መሰባሰብ ሲኖርባቸው፣ ምኁራን ቀርቶ የፖለቲካ ሰዎች በሹመት መምጣታቸውም ለዚህ ችግር መንስኤ መሆኑን ዓለማየሁ ከመግለጽ አልተቆጠቡም።

አያይዘውም ሌሎች አገራት ያላቸውን ልምድ ሲያነሱ፤ በእነዚህ ማዕከላት የሚሰባሰቡት በሚጠናው ባሕል ቋንቋና ታሪክ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ቅርበት ያላቸው ምኁራን ናቸው። ተሰባስበውም መሪያቸውን ራሳቸው መርጠው ተጠሪ ለሆኑለት አካል በማሳወቅ ያስጸድቃሉ፤ ያለ ቢሮክራሲም ምሁራዊ ሥራዎችንና ጥናቶችን በትኩረት ይሠራሉ።

በዚህ መሠረት በኦሮሞ ባሕል ማዕከልም በተመሳሳይ ብዙ ምሁራንን ማሳተፍ ሲገባ እንደዛ ግን እንዳልሆነ ነው ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት። ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናት መነሻ ሐሳቦችን በማቅረብና በማገዝ ጥላ እንዲሆን የሚጠበቀው የባሕል ማዕከሉ፤ ባለቤት ሊሆንላቸው ለሚገቡ ክዋኔዎች ሳይቀር እንግዳ ሲሆን ይስተዋላል። እናም ወደተነሳበት ዓላማ የሚያደርሰው መንገድ ላይ በኹለት እግሩ መቆሙ ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ይህ እንዳለ ሆኖ በማዕከሉ ባለው አቅም ጥናቶች መደረጋቸው አልቀረም። ይህንንም በተለያየ ጊዜ ለሕትመት የበቁ የጥናት ሥራዎች የሚያረጋግጡት ሀቅ ነው። ይሁንና እዚህ ላይ ደግሞ ተደራሽነት የሚባለው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። የሕትመት ብርሃንን ያዩ ሥራዎች ከማዕከሉ ጊቢ ውጪ በብዙ ቦታዎች የሚገኙ አይደሉም። በአንድ ጎን ማዕከሉም ሥራዎቹን በይፋ ማስተዋወቅ ላይ እጥረት እንዳለበት ያመላክታል።

የገዳ ስርዓት በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ትልቅ ሚና መወጣት ችሎ የነበረው ማዕከሉ፤ በጀመረበት አካሔድ አሁንም እየተጓዘ አለመሆኑ ከተመልካች ሊደበቅ አይችልም። “የገዳ ስርዓት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ሲመዘገብ በቀጣይነት እንዲሠራበት እንጂ እንዲቀመጥ አይደለም” የሚሉት ዓለማየሁ፤ አሁንም ከማዕከሉ የሚጠበቅ ብዙ ሥራ እንዳለ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ባሕልን ማስተዋወቅና ማበልጸግ የማዕከሉ ሥራ ሆኖ ሳለ፤ ነገር ግን የባሕልና ቱሪዝም ቢሮው እየተገበረው መሆኑንም አያይዘው ጠቅሰዋል። ምንም እንኳን ቢሮው ሥራውን እየሠራው ቢሆንም ምሁራንን ማናገር ላይ ክፍተት ያለበት በመሆኑ በርካታ ክዋኔዎች ከቀናት በዘለለና ከዜና ፍጆታነት ባለፈ ፍሬ ሲያፈሩ አይታይም። ይህ ደግሞ በዋናውና በተጠሪው ተቋም መካከል መናበብ ያለመኖሩ ማሳያ ነው።

ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምን ያህል አግዘዋል? ሌላው ቢቀር የኅትመት ሥራዎቹን ተደራሽ ማድረግ ላይ ብዙ እንደሚቀራቸው ግልጽ ነው። አዲስ ማለዳ እንደታዘበችው ማዕከሉ ተጠሪነቱ ከክልሉ ባሕልና ቱሪዘም ሳይርቅ ነገር ግን ራሱን የቻለ ተቋም ማድረግ ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ይህንንም ለማድረግ ማዕከሉ በተለይም የጥናትና ምርምር ክፍሉ የአሠራር ዕቅዶችን አዘጋጅቶ በጠሪ ተቋማት በኩል ለሚመለከተው የመንግሥት አካላት እንዲደርስ እየተጠባበቀ መሆኑን ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የባሕል ማዕከላት በእርግጥ የባሕል ዘርፍ ከመጠበቅና የአገርን መልክ ከማቆየታቸው ባሻገር ገቢ ማግኛም ናቸው። የኦሮሞ ባሕል ማዕከል በሚከራዩ አዳረሾችና ፊልም ማሳያዎች፤ የተለያዩ ክዋኔዎችንም በማስተናገድ ገቢ መሰብሰቡ አልቀረም። ምን ያህል እየተጠቀሙበት ነው የሚለው ጥያቄ ይቆየንና ከዛ አልፎ ግን ማኅበረሰብ ስለራሱ እንዲያውቅ፤ አንድ የሚያደርጉ የአንድነት ታሪክና ባሕሎች በጥናትና ምርምር ተደግፈው እንዲቀርቡ ግድ ይላልና ማዕከሉን ማጠናከር ያለ ጥርጥር አስፈላጊ ነው። ይህም ሲሆን የኦሮሞ ባሕል ማዕከል አካዳሚ የመሆን ተስፋው እውን ይሆናል፤ ለሌሎች ባሕል ማዕከላትም መንገዳቸው ይጠረጋል።

አዲስ ማለዳ ይህን ሁሉ የምትለው፤ የማዕከሉን ገና ጀማሪ መሆን ሳትዘነጋ ነው። “የሚያጠግብ እንጀራ…” እንዲሉ፤ በልደቱ ማግሥትም ቢሆን አካሔዱ ያማረ መሆኑ ለነገ የሚመነዘር ሀብት ስለሚሆን ከወዲሁ እንዲስተካከል ለማለት ነው። በዚሁ አጋጣሚም በማዕከሉ ያሉ ለእይታ የሚቀርቡ ቅርሶችን ለማየትና ጊቢውንም ለመጎብኘት ወደ ስፍራው ለሚያቀኑ ግለሰቦች፤ ከጊቢው በር ላይ ያለው አቀባበል፤ ለካሜራ የሚሰጥ ፈቃድና መሰል አሠራሮች ላይ ክለሳ እንዲያደርግ ለማዕከሉ አስተዳደር አዲስ ማለዳ አደራዋን ታስተላልፋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here